ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራዩ ጦርነት የኢትዮጵያን የኦሊምፒክ ተስፋ ጎድቶታል?
ረዳኢ ገብረእየሱስ በኦሊምፒክ መድረክ ኢትዮጵያን ወክሎ ሊወዳደር ይችል ነበር። ነገር ግን በጦርነት ምክንያት ሕይወቱ በአጭሩ ተቀጨ።
ጥቅምት 2013 የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተቀሰቀሰ። ይህ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከወራት በኋላ ነው የመካከለኛ ርቀት ሯጭ የሆነው ረዳኢ የተገደለው።
ትግራይ ክልል ለኢትዮጵያ በርካታ ራጮችን አበርክቷል። በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው ከሚወዳደሩ አትሌቶች መካከል አንድ ሶስተኛ ከትግራይ ክልል የተገኙ ናቸው።
የረዳኢ አሰልጣኝ የነበረው ጌትዬ መኩሪያ እንደሚለው ወጣቱ ሯጭ የኦሊምፒክ አባል የመሆን ተስፋ ነበረው። ነገር ግን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በኢትዮጵያ መንግሥት እና በክልሉ ኃይሎች መካከል የተነሳው ጦርነት የረዳኢን ሕይወት ቀጠፋት።
“ያለምንም ጥርጥር ረዳኢ ከመመረጥ አልፎ ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ ይችል ነበር” ሲል ጌትዬ ለቢቢሲ ይናገራል።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ጦርነት የተቋጨው ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት ነው።
ጌንት ዩኒቨርሲቲ ያስጠናው ጥናት እንደሚጠቁመው በጦርነቱ ምክንያት እስከ 600 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል። 900 ሺህ ገደማ ሰዎች ደግሞ ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል።
ከኤርትራ ድንበር 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው እዳጋ አርቢ የሚገኙት የረዳኢ እናት አሁንም የልጃቸውን ሞት በማስታመም ላይ ናቸው።
“ልጄን ብቻ ሳይሆን ሁሉ ነገሬን ነው ያጣሁት” ይላል ሀደራ ስዩም።
“ቢሆንም ልጆቹን ጥሎልኝ አልፏል። ባይወልድ ኖሮ በጣም ይቆጨኝ ነበር። ምንም የለኝም እል ነበር።”
“የታላቅነት” ተስፋ የነበረው
ረዳኢ ትግራይ ክልል ማይጨው በሚገኘው የአትሌቲክስ መንደር ነበር ስልጠና የሚያደርገው። በክልሉ በተካሄዱ ውድድሮች ተሳትፎ በርካታ ሜዳሊያዎች ማግኘት ችሏል።
በኦሊምፒክስ ተሳትፈው በ5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያገኙት ሀጎስ ገብረሒወት እና ጉዳፍ ፀጋይን በመመልከት ነው ልቡ ለአትሌቲክስ የተሸነፈችው።
“በ2006 ነበር ልምምድ የጀመረው” ይላሉ የረዳኢ እናት እንባ እየተናነቃቸው።
“ከትምህርት ወጥቶ ቤቱ ከመምጣቱ በፊት ይሮጥ ነበር። ጥዋት ጥዋት ደግሞ ተነስቶ ልምምድ ያደርግ ነበር።”
የቤተሰብ ሰው እንደነበር የሚነገርለት ረዳኢ ከሩጫው በተጨማሪ በሕንፃ ግንባታ እና የእርሻ መሣሪያ በማምረት ይተዳደር ነበር። ነገር ግን ጥቅምት 2020 ቤቱ ሳለ ነው ወታደሮች የሚኖርበት መንደር ላይ ጥቃት የከፈቱት።
እናቱ እና እሕቱ ቤታቸውን ጥለው ሲጠፉ እሱ ግን ወደኋላ ቀርቶ የትግራይ ኃይሎችን ደግፎ ለመዋጋት ወሰነ።
ቤተሰቡ ለመጨረሻ ጊዜ ያየው የዛኔ ነው።
ገና ሁለቱም ታዳጊ ሳሉ ከረዳኢ ጋር በአትሌቲክስ ምክንያት የተዋወቀችው ሚስቱ ትምኒት አረጋዊ ልጆቿን እና የረዳኢ እናት እያገዘች ትኖራለች።
“ለሀገሩ ታላቅ ሯጭ የመሆን ተስፋ የነበረው አትሌት ነው” ትላለች ትምኒት።
“በጣም ጀግና ነበር። ለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም። ሁሉ ነገሬ ነበር። ከሞቱ በኋላ እኔም በድን ሆኛለሁ። በሽታ እያሰቃየኝ ነው። ሥነ-ልቡናዬ ተቃውሷል። በሆነው ነገር አሁንም ተረብሻሀሉ።”
ወታደራዊ ሰለባዎች
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተገባደደ ሁለት ዓመት ሊሞሉት የወራት ዕድሜ ቢቀረውም ግጭቱ ጥሏቸው ያለፋቸው እንደ ረሀብ ያሉ አደጋዎች አሁንም በግልፅ ይታያሉ።
ልክ እንደየትኛውም የሕይወት ክፍል የስፖርቱ ዘርፍም ተጎድቷል። በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የመለማመጃ ሥፍራዎች ዋጋ 1.7 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል።
የክልሉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊ እንደሚሉት በጦርነቱ ምክንያት ከ100 በላይ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች እና አስተዳዳሪዎች ተገድለዋል።
“አብዛኛዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የሚችሉ ነበሩ” ሲሉ የፌዴሬሽኑ ኃላፊ ኪዳኔ ተኽለኃይማኖት ለቢቢሲ ይናገራሉ።
“ለቤተሰቦቻቸው፤ ለሀገራቸውም ጨምር የገንዘብ ምንጭ መሆን የሚችሉ ነበሩ።”
ሌላኛዋ ብሩህ መፃዒ ተስፋ የነበራት ታዳጊዋ ሯጭ በላይነሽ ያያ በትራክ [መም] ውድድሮች ድንቅ ብቃት ነበራት።
እንዳመኾኒ የሚኖረው ወንድሟ ሀብታሙ ያያ እንደሚለው አትሌቲክስን በአካባቢው “የባሕል ስፖርት” ሲሆን በላይነሽም ይህን ስፖርት የወረሰችው ከታላላቆቿ ነው።
“አንድ ቀን ሀገሯን ትወክላለች ብዬ አምን ነበር” ይላል ወንድሟ ሀብታሙ።
“በዚህኛው ኦሊምፒክ [ፓሪስ 2024] የቡድኑ አባል ትሆናለች ብዬ አስብ ነበር። ሕልሜ እሷን በዓለም አቀፍ መድረክ ማየት ነበር።”
የ18 ዓመቷ አትሌት ተስፋዋ የነበረው ልክ እንደ መሠረት ደፋር እና ኃይሌ ገብረስላሴ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን መሆን ነበር። ነገር ግን ዕጣ ፈንታ
ምንም እንኳ አባቷ በሐሳቧ ባይስማም ገንዘብ ለማግኘት ስትል ከጦርነቱ በፊት ነው የክልሉን ኃይል የተቀላቀለችው።
“በወቅቱ ደስተኛ አልነበርኩም” ይላሉ ያያ ገብረሳሙኤል።
“እንዴት አንድ አባት ልጁ እሳት ውስጥ ስትገባ ዝም ብሎ ይመለከታል? ልጄ ወታደር ሆና ከማያት በአትሌቲክስ ስትሳተፍ ባያት ሺህ ጊዜ እመርጥ ነበር።”
በምትኖርበት አካባቢ በነበረው ግጭት ጓደኞቿን ካጣች በኋላ ለአባቷ ጓደኞቿ እንደሞቱ ነገረችው።
“ጦርነቱን ጥላ እንድትመጣ በጣም ተማፅኛት ነበር። ነገር ግን ሸሽቼ ከምመጣ ሞቴን እመርጣለሁ አለችኝ። ሁሉም የቤተሰብ አባል ተማፅኗት ነበር ግን አሻፈረኝ አለች” ይላሉ አባቷ ያያ።
ሯጯ የትግራይ ኃይሎችን ተቀላቅላ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እየተሳተፈች ሳለች ተገደለች።
ቤተሰቦቿ እስካሁን የተቀበrችበትን ቦት ማወቅ አልቻሉም።
ወደ መሮጫው መም
አሰልጣኝ ጌትዬ ረዳኢን ብቻ ሳይሆን በላይነሽ ያያንም አሰልጥኗል።
“ልክ እንደ ልጄ ነበር የማያት። በጣም ዲሲፕሊን ያላት፤ ጠባየ መልካም ነበረች። አብዛኛዎቹ ደከመኝ ሳይሉ ቀንና ሌሊት ነበር የሚሰለጥኑት። በጣም ጠንካራ ሰራተኞች ነበሩ። ጦርነት ይነሳል ብለን አልጠበቅንም። ወታደራዊ ኃይሎችንም ይቀላቀላሉ የሚል ግምት አልነበረንም።”
የማይጨው የመለማመጃ ሜዳ የኦሊምፒክ ሜዳሊያ ባለቤቶችን አፍርቷል። በ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ የ5 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ በ10 ሺህ ሜትር ደግሞ ወርቅ ያመጣችው ጉዳፍ ፀጋይ አንዷ ናት።
የትግራይ ቀጣዩ ትውልድ አትሌቶች ማይጨው ስልጠና ላይ ናቸው። ነገር ግን የማሰልጣኛ ሥፍራው አብዛኛው ንብረት ጥቅም እየሰጠ አይደለም።
ከጦርነቱ በኋላ ወደ ሩጫ የተመለሰው እና ወደፊት በዓለም አቀፍ መድረክ መሳተፍ የሚፈልገው ፍቅር ሰለሞን ጓደኛው ረዳኢን ያስታውሳል።
“ጥዋት ጥዋት ተነስተን ልምምድ ስናደርግ በቀልድ ነበር የምንጀምረው። ይህ ባሕሪው ለየት ያደርገዋል” ይላል።
ምንም እንኳ በረዥም ጊዜ ጦርነቱ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ለጊዜው ግልፅ ባይሆንም በትግራይ የነበረው ጦርነት ያስከፈለው ዋጋ ግን የሚካድ አይደለም።