የኢትዮጵያ ፓስፖርት ዋጋ ከሌሎች አገራት ጋር እንዴት ይነጻጸራል?

ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በፓስፖርት ዋጋ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ አድርጓል።

ቀደም ሲል 2 ሺህ ብር ይጠየቅበት የነበረው የአዲስ ፓስፖርት ክፍያ በአዲሱ የዋጋ ማሻሻያ 5 ሺህ ብር (50 የአሜሪካ ዶላር) መሆኑን አስታውቋል።

በአስቸኳይ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ይጠየቅ የነበረው 5 ሺህ ብር ደግሞ ወደ 20 ሺህ ብር (200 ዶላር ገደማ) ከፍ ማለቱን አገልግሎቱ አስታውቋል።

እንደ አገልግሎቱ መረጃ ከሆነ ፓስፖርቱ ዕድሜ ኖሮት እርማት ለማግኘት ለፈጣን አገልግሎት 40 ሺህ 500 ብር ያስከፍላል።

በተመሳሳይ ለጠፋ ፓስፖርት በሁለት ቀን እርማት ለማድረግ የአገልግሎት እስከ 40 ሺህ 500 ብር (450 ዶላር) እንደሚያስከፍል አስታውቋል።

በውጭ አገር ሆነው መደበኛ ፓስፖርት በኤምባሲ በመደበኛ ጊዜ የሚጠይቁ ኢትዮጵያዊያን 200 ዶላር ይከፍላሉ። በአስቸኳይ (በ15 ቀናት) ለማግኘት ደግሞ 350 ዶላር ይጠየቃሊ።

ቢቢሲ የፓስፖርቱን ክፍያ መጨመር ምክንያት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የሌሎች አገራት የፓስፖርት ክፍያ

ቢቢሲ የተለያዩ አገራት ለዜጎቻቸው ፓስፖርት የሚያቀርቡበትን ዋጋ ለማጣራት ሞክሯል።

በጎረቤት አገር ኬንያ መደበኛ (ባለ 34 ገጽ) ፓስፖርት ለማውጣት 4 ሺህ 550 ሽልንግ (35 የአሜሪካ ዶላር) ገደማ ይከፈላል።

የኬንያ ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ደግሞ 7 ሺህ 550 ሽልንግ መሆኑን የኬንያ አገር ውስጥ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ለተበላሸ ፓስፖርት 10 ሺህ 50 ሽልንግ (70 ዶላር) ዋጋ የወጣለት ሲሆን ለጠፋ ፓስፖርት ደግሞ 12 ሺህ 50 ሽልንግ (96 ዶላር) ይከፈላል።

የደቡብ አፍሪካ ፓስፖርት በመደበኛ ለማግኘት 600 ራንድ (33 ዶላር) እንደሚከፈል በአገሪቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ድረ ገጽ ላይ ሰፍሯል።

አገሪቱን ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለማግኘትም በተመሳሳይ 600 ራንድ መክፈል ያስፈልጋል።

ትልቁን ባለ 48 ገጽ ፓስፖርት ለማግኘት ደግሞ 1 ሺህ 200 ራንድ ይከፈላል።

መደበኛውን ባለ 24 ገጽ የዩናይትድ ኪንግደም ፓስፖርት ለማግኘት ሁለት አማራጭ ያለ ሲሆን በበይነመረብ ለሚያመለክቱ 88.50 ፓውንድ (112 ዶላር) በወረቀት ለሚመለክቱ ደግሞ 100 ፓውንድ ይከፍላሉ።

ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ሰዎች ደግሞ በበይነ መረብ 57.50 ፓውንድ በወረቅት ለሚያመለክቱ ደግሞ 69 ፓውንድ መሆኑን አገሪቱ መንግስት ድረገጽ ያሳያል።

እአአ ከ1929 በፊት ለተወለዱ ሰዎች የዩናይትድ ኪንግደም ፓስፖርት በነጻ ይሰጣል።