በስዊትዘርላንድ መዝናኛ ስፍራ በደረሰ የእሳት አደጋ 40 ያሀል ሰዎች ሞቱ

በአደጋው ለሞቱ ሰዎች ሻማ የሚያበሩ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በደቡባዊ ስዊትዘርላንድ በሚገኝ የበረዶ ሸርተቴ መጫወቻ ስፍራ ውስጥ በሚገኝ የመዝናኛ ስፍራ በተነሳ እሳት 40 ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

በእሳት አደጋው115 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ብዙዎቹም "በከባድ ሁኔታ" ቆስለዋል ተብሏል።

እሳቱ የተከሰተው በክራንስ-ሞንታና በሚገኘው ሌ ኮንስቴሌሽን በተባለ ባር ውስጥ የአዲስ ዓመት ዋዜማ እየተከበረ ባለበት ወቅት ነው።

አደጋውን እየመረመሩ የሚገኙት ፖሊሶች እሳቱ የተነሳበትን መንስዔ ያላሳወቁ ሲሆን ጥቃት ደርሶ እንዳልሆነ ግን አረጋግጠዋል።

ከተለያዩ አገራት የመጡ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።

የአካባቢው የፖሊስ አዛዥ ፍሬድሪክ ጊስለር በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የሞቱትን ሰዎች መለየት እና "አስከሬናቸው በፍጥነት ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ" ነው ብለዋል።

አስራ ሦስት ሄሊኮፕተሮች፣ 42 አምቡላንሶች እና 150 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቱሪስቶች በሚዘወተረው አካባቢ ተሰማርተው እንደነበር ማወቅ ተችሏል።

አብዛኛዎቹ በአደጋው የተጎዱ ሰዎች ከባድ ቃጠሎ እንደደረሰባቸው የተገለፀ ሲሆን 60 ሰዎች ደግሞ በቫሌይስ ወደሚገኘው የሲዮን ሆስፒታል ለተሻለ ሕክምና ተልከዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የክልሉ አስተዳዳሪ ማቲያስ ሬይናርድ ቁጥራቸው "ከፍተኛ" የሚሆን ሰዎች በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኘው ሆስፒታል የጽኑ ሕክምና ክፍሉ ሙሉ በሙሉ በመሙላቱ፣ ሬይናርድ የአካባቢው ማኅበረሰብ አላስፈላጊ የሆስፒታል ሕክምና እንዳይፈልግ ተማጽኖ አቅርበዋል።

"አስከሬኖቹን እንዲሁም የቆሰሉትን ሰዎች ማንነት መለየት በጣም ረዥም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል እናውቃለን" ሲሉ አስተዳዳሪው ሬይናርድ ጨምረው ተናግረዋል።

አንዳንድ ሰዎች የቃጠሎ ሕክምና ክፍል ወዳሏቸው እንደ ላውሳን እና ዙሪክ ባሉ ሌሎች የስዊትዘርላንድ ከተሞች ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ተወስደዋል።

የላውሳን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ቃል አቀባይ 22 የቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸውን ታካሚዎች እያከሙ መሆኑን ሲናገሩ፣ የዙሪክ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በበኩሉ 12 ሕሙማንን መቀበሉን አስታውቋል።

አንዳንድ ታካሚዎች ወደ ጄኔቫ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ተዛውረው ከባድ እና "የሦስተኛ ደረጃ" ቃጠሎ ሕክምና እየተደረገላቸው የነበረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ዕድሜያቸው "ከ15 እስከ 25 ዓመት እድሜ የሚሆን . . . በጣም ወጣት የሆኑ ይገኙበታል " ሲሉ ዶ/ር ሮበርት ላሪባው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እሳቱ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ቃጠሎው ወደ ውስጥ ዘልቆ ሊገባ ይችላል። ሰዎች መርዛማ ጭስ ወደ ሳንባቸው ንፈሰዋል" ሲሉ ዶ/ር ላሪባው ተናግረዋል።

የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቢቢሲ በአሁኑ ወቅት 16 የጣሊያን ዜጎች እንደጠፉ እና ከ12 እስከ 15 የሚሆኑ ሌሎች ሰዎች በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጿል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስምንት ዜጎቿ እንደጠፉ እና ከሟቾቹ መካከል የፈረንሳይ ዜጎች መኖራቸውን አስታውቋል።

የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከቆሰሉት ውስጥ ቢያንስ ሁለቱ የፈረንሳይ ዜጎች ናቸው።

ሦስት የጣሊያን ዜጎች ሚላን በሚገኘው የኒጓርዳ ሆስፒታል እየተወሰዱ መሆኑን የጣሊያን ምክር ቤት አባል ጊዶ ቤርቶላሶ ተናግረዋል።

"ከ30-40 በመቶ የሚሆነውን ሰውነታቸውን በእሳት ተቃጥሏል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ነገር ግን "መንቀሳቀስ እንደሚችሉ መረጋገጡ ጥሩ ምልክት ነው" ብለዋል።

የሟቾችና የቆሰሉት ትክክለኛ ቁጥር እስካሁን እንዲሁም ዜግነታቸው አይታወቅም፤ ነገር ግን ባለሥልጣናት የበርካታ አገራት ሰዎች በአደጋው መጎዳታቸውን አረጋግጠዋል።