ሲአይኤ መረጃ አቀባዮችን ከሰሜን ኮሪያ፣ ከኢራን እና ከቻይና ለመቅጠር ማስታወቂያ አወጣ

የፎቶው ባለመብት, AP
የአሜሪካው የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ከቻይና፣ ከኢራን እና ከሰሜን ኮሪያ መረጃ አቀባዮችን ለመመልመል አዲስ እንቅስቃሴ መጀመሩ ታወቀ።
ድርጅቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎቹን ተጠቅሞ ረቡዕ ዕለት በማንዳሪን (የቻይና)፣ በፋርስ (ኢራን) እና በኮሪያ ቋንቋዎች ባሠራጨው መልዕክት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ ሊያገኙት እንደሚችሉ ገልጿል።
የዩክሬንን ወረራ ተከትሎ ሩሲያውያንን ለመመዝገብ ተመሳሳይ ቅጥር የተካሄደ ሲሆን፣ ሲአይኤ የምልመላ ሂደቱ የተሳካ እንደነበርም ገልጿል።
የሲአይኤ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ “በአምባገነን መንግሥታት ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች ለሥራ ክፍት መሆናችንን እንዲያውቁ እንፈልጋለን” ብለዋል።
እንደ ኤክስ፣ ፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም እና ሊንክዲንን በመሳሰሉ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረኮች ላይ በወጡት የምልመላ መልዕክቶች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ስማቸውን፣ አድራሻቸውን እና ስልካቸውን አንዲያሰፍሩ ተጠይቀዋል።
ለመረጃ አቀባይነት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አስተማማኝ የሆኑትን ኢንክሪፕትድድ ቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትወርኮች (ቪፒኤን) ወይም ድብቅ ሆኑ ድረ ገጾችን (ዳርክ ዌብ) በመጠቀም በይፋዊው የሲአይኤ ድረ-ገጽ በኩል ግንኙነት እንዲፈጥሩ መክሯል።

የፎቶው ባለመብት, CIA/Facebook
“ቢያንስ ኮሪያ ውስጥ ዩቲዩብ ወይም ማኅበራዊ ሚዲያን በዚህ መንገድ በመጠቀም ተመሳሳይ ምልመላ ሲደረግ አላስታውስም” ሲሉ በሴዑል በሚገኘው የሃንኩክ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሜሰን ሪቼ ተናግረዋል።
“በሩሲያ ያገኙትን ስኬት መሠረት ያደረጉ ይመስላል። አብዛኞቹ ሰሜን ኮሪያውያን የኢንተርኔት አገልግሎት ስለሌላቸው በውጤታማነቱ ላይ ጥያቄ ይኖረኛል” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ሪቼ አክለውም ከቻይና ጋር መደበኛ ባልሆነ መንገድ ድንበር አቋርጠው በሚነግዱ እና ቪፒኤን ማግኘት በሚችሉ የሰሜን ኮሪያ ነጋዴዎች ላይ ያነጣጠረ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ከስለላ ጋር በተያያዘ አገራቱ በሚያደርጉት ጥብቅ ክትትል ምክንያት ሲአይኤ ሰሜን ኮሪያን፣ ኢራንን እና ቻይናን “ከባድ ዒላማዎች” አድርጎ ይመለከታቸዋል።
“ይህ ጥረት ሲአይኤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ጥብቅ ክትትል እየተላመደ የሚገኝበትን መንገድ ብቻ ይወክላል" ሲል የስለላ ድርጅቱ መግለጫ ገልጿል።
ፕሮፌሰር ሪቼ ግን በዚህ መንገድ ሊሰበሰብ በሚችል መረጃ ላይ ጥርጣሬ አላቸው።
“ሲአይኤ የሚሠራውን እንደሚያውቅ መገመት አለባችሁ ብዬ አስባለሁ። እነዚህ ምልምሎች ግን ምን ያህል ለሥልጣን እና ለውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ቅርብ ናቸው የሚለውን ስታስቡ ልትገረሙ ትችላላችሁ” ብለዋል።
“በፀረ ስለላ ሥራዎች ላይ ግን የተወሰነ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል” ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, CIA/YouTube
በሩሲያ በተገኘው ውጤት የተበረታቱ የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ኃላፊዎች፤ ደስተኛ ካልሆኑ ዜጎች ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ መረጃዎችን ሊያገኙ እንደሚችሉ እርግጠኞች ናቸው።
“መረጃ የሚያገኙ እና በቻይና ባለው የፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አስተዳደር ያልተደሰቱ ብዙ ሰዎች አሉ” ሲሉ የሲአይኤ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ኮኸን ለብሉምበርግ ተናግረዋል።
“በተለያዩ ምክንያቶች ዢ አገሪቱን እየወሰዱ ያሉበትን አቅጣጫ የማይወዱ እና ከእኛ ጋር በመተባበር አገራቸውን የሚረዱበት መንገድ እንዳለ የሚረዱ በርካታ ውስጥ አዋቂዎች አሉ” ብለዋል።
የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ሊዩ ፔንግዩ በበኩላቸው አሜሪካ በቻይና ላይ “የተደራጀ እና ስልታዊ” የሐሰት ዘመቻ እያካሄደች ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“በቻይና ሕዝብ እና በሲሲፒ (የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ) መካከል ልዩነት ለመፍጠር ወይም የቅርብ ግንኙነታቸውን ለማዳከም የሚደረጉ ማናቸውም ሙከራዎች አይሳኩም” ሲሉ አክለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ይህን የመሰለ ዘመቻ በተለያዩ አገራት ማካሄዷ የብሔራዊ ደኅንነት ተግዳሮቶቿን እንዴት እንደምትመለከት ጥሩ ማሳያ እየሰጠች ነው ብለዋል ዶ/ር ሪቼ።
“ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና፣ ከሩሲያ፣ ከኢራን እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር በተከታታይ የሁለትዮሽ ፍጥጫ ውስጥ መግባት ብቻ ሳይሆን፣ ብቅ ከሚሉ ጥምረቶች ጋርም እንደምትጋጭ እርግጠኛ ነች” ብለዋል ፕሮፌሰር ሪቼ።
“ይህም የቀዝቃዛውን ጦርነት ስሜት በግልጽ የሚፈጥር ነው” ሲሉ ይህ የአሜሪካ እንቅስቃሴ ሊያስከትል የሚችለውን ሁኔታ ገልጸዋል።












