ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፌስቡክ ባለቤት ሜታ 91 ሚሊዮን ዮሮ ተቀጣ
የፌስቡክ እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ በአይሪሽ ዳታ ፕሮቴክሽን ኮሚሽን (ዲፒሲ) ከይለፍ ቃል አያያዝ ጋር በተገናኘ በተደረገበት ምርመራ 91 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት ተጣለበት።
ምርመራው የተጀመረው እኤአ በ2019 ሚያዝያ ወር ላይ ሜታ ኮሚሽኑን የተወሰኑ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችን የይለፍ ቃል በስህተት በውስጣዊ ስርዓቱ ውሰጥ ሳይቀይራቸው ማስቀመጡን ካሳወቀ በኋላ ነው።
ኮሚሽኑም የአውሮፓን ዳታ ለሚቆጣጠረው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳቡን በሰኔ ወር ላይ አስገብቶ ነበር።
በተከሳሹ ወገን ምንም ዓይነት ቅሬታ አለመቅረቡም ተገልጿል።
ሜታ አራት የአውሮፓ የዳታ መከላከል ደንቦችን ተላልፎ ተገኝቷል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ግራሀም ዶይሌ እንዳሉት “የተጠቃሚዎች የይለፍ ቃል በሌሎች ግለሰቦች እጅ ገብተው ተጠቃሚዎችን ለጥቃት እንዳያጋልጥ ሳይቀየር እንዳለ እንዳይቀመጥ የሚለው አሰራር በስፋት ተቀባይነት ያለው ነው።
“በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረቡት የይለፍ ቃላት የተጠቃሚውን አካውንት ለመክፈት የሚያስችሉ በመሆናቸው የበለጠ አደገኛ እንደሚያደርጋቸው እሙን ነው” ብለዋል።
ውሳኔው የተላለፈው በዳታ መከላከል ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዴስ ሆጋን እና ዴል ሰንደርላንድ ሲሆን ሜታም ጉዳዩ ከማስጠንቀቅያ እና ከቅጣት ጋር ከሁለት ቀን በፊት እንዲደርሰው ተደርጓል።
ሜታ እኤአ በ2023 ግንቦት ወር ላይ ከአውሮፓ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ዳታ ሲያስተላልፍ በነበረ የአያያዝ ጉድለት የተነሳ 1.2 ቢሊዮን ዩሮ መቀጣቱ ይታወሳል።
ይህ ቅጣት በአየርላንድ የዳታ መከላከል ኮሚሽን በአውሮጳ ሕግ ትልቁ ቅጣት ተብሎ ተመዝግቧል።
እኤአ በ2022 በ106 አገራት የሚገኙ 533 ሚሊዮን ሰዎች የፌስቡክ መረጃ በመረጃ መንታፊዎች እጅ ገብቶ ከተሰራጨ በኋላ ሜታ 265 ሚሊዮን ዩሮ ተቀጥቷል።