ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አፍሪካውያን ተማሪዎች በሊባኖስ፡ "በካምፓስ ውስጥ ሁሉም ተረብሿል”
ከዚምቧቤ የመጣው የ27 ዓመቱ ፋራዒ ከዚህ ቀደም መማርያ መጻሕፍቶቹን ቤሩት በሚገኘው ቤቱ ጠረጴዛ ላይ ያስቀምጥ ነበር።
በዚህ ሳምንት ግን ጠረጴዛው ላይ የሚያስቀምጠው ለጉዞ የሚያስፈልጉትን ሰነዶች፣ ፓስፖርቱን እና ገንዘብ ጨምሮ ነው።
“ድንገት ለቅቄ መውጣት እንኳ ቢኖርብኝ በሚል ዕቅድ አውጥቻለሁ” ይላል።
ለደህነንቱ ሲባል ስሙን የቀየርነው ፋራዒ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ እየተማረ ያለውን ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ለማጠናቀቅ ወደ ሊባኖስ የተመለሰው በዚህ ወር ነው።
የክረምቱን ወራት ሐራሬ ቤተሰቦቹ ጋር ነው ያሳለፈው።
ሲመለስ ግጭቱ ይቀዛቀዛል ሲል ተስፋ አድርጎ ነበር። ነገር ግን ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት ከከፈተበት ካለፈው ዓመት አንስቶ በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ድንበር ተሻጋሪ የተኩስ ልውውጥ በየቀኑ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ሲካሄድ ቆይተዋል።
እስራኤል በሊባኖስ የሄዝቦላ ይዞታዎች ላይ የምታደርገው የአየር ድብደባ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል።
ሄዝቦላ በበኩሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ያስወነጨፈ ሲሆን፣ በጋዛ ጦርነት ምክንያት የተነሳው ይህ ግጭት ወደ ቀጣናዊ ጦርነት እንዳይሸጋገር ፍርሃት አሳድሯል።
የእስራኤል ጦር “የተጠናከረ” የአየር ጥቃት በደቡባዊ ሊባኖስ እና ቤቃ አካባቢ እንደሚያደርግ ሲገልጽ፣ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተናግሯል።
ባለፈው ሳምንት የሄዝቦላ አባላት የሚጠቀሙባቸው ለግንኙነት የሚረዱ መሳርያዎች፣ ፔጀር እና ዎኪ ቶኪዎች፣ በመላው አገሪቱ ፈንድተው በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቆስሉ 39 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።
ሄዝቦላ ከፍልስጤማውያን ጎን በመቆም እንደሚዋጋ ይናገራል።
እስራኤል በበኩሏ በሰሜን እስራኤል ድንበር አቅራብያ ይኖሩ የነበሩ እና ቤታቸውን ጥለው የሸሹ ዜጎቿ እንዲመለሱ አንደምትፈልግ ትገልጻለች።
አሜሪካ፣ ዩኬ፣ አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ እና ሕንድ ዜጎቻቸው በተቻለ መጠን ሊባኖስን ለቅቀው እንዲወጡ አስጠንቅቀዋል።
አፍሪካውያን ተማሪዎች ግን የእስራኤል ጥቃት በቀጠለ ቁጥር ሊባኖስ ቆይቶ የሚሆነውን ማየት ወይም ወደ መጡበት ኡጋንዳ፣ ዚምቧቤ እና ካሜሮን መመለስ በሚለው ላይ ግራ መጋባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፋራዒ የሚማርበት አሜሪካን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቤሩት (ኤዩቢ) ነጻ የትምህርት እድል አግኝተው የመጡ 90 አፍሪካውያን ተማሪዎች ይገኛሉ።
ፋራዒ እንደሚለው በተለይ ፔጀሮች እና ዎኪ ቶኪዎቹ ከፈነዱ ወዲህ በተማሪዎች መካከል “ከፍተኛ ፍርሃት” አለ።
“ማን በኪሱ በየትኛውም ሰዓት ሊፈነዳ የሚችል ቦምብ ይዞ እንደሚዞር አናውቅም” ይላል።
“ የታክሲ ሹፌሩ ነው? ወይስ የኡበር አሽከርካሪው? አልያስ ከአጠገቤ የሚራመደው?” ሲልም ይጠይቃል።
በካምፓስ ውስጥ የነገሰው ፍርሃት
የፋራዒ መደበኛ ቀናት በትምህርት እና ጓደኞቹን በመጠየቅ የተሞሉ ነበሩ።
አሁን ግን የመኖርያ ቤቱን ለቅቆ የሚወጣው ዩኒቨርስቲ ለመሄድ እና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለመሸመት ብቻ ነው።
በቅርቡ ክፉ ቀን ቢመጣ እና እጥረት ቢፈጠር ብሎ በማሰብ ዳቦ፣ ፓስታ እና የታሸገ ውሃ ገዝቶ አስቀምጧል።
በርካታ የሚማራቸው ትምህርቶች ወደ ኦንላየን ተቀይረዋል። ወደ ካምፓሱ በሚሄድበትም ወቅት ያለው ውጥረት እና ፍርሃት አካል ነስቶ የሚጨበጥ ይመስላል።
“ሁሉም ሰው ተሸብሯል። የምናወራበት መንገድ ሳይቀር ተለይቷል” ይላል።
“ትምህርታቸንን ስንጨርስ ፕሮፌሰራችን መልካም ቀን፤ ራሳችሁን ጠብቁ ይለናል። እኛም መልሰን ያንንኑ መልካም ምኞት እንገልጻለን። ምክንያቱም በአገሪቱ ውስጥ እየሆነ ያለውን እናውቃለን”
“ማንም ሰው ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም።”
ኤዩቢ ዩኒቨርስቲ ፔጀሮቹ የፈነዱ ዕለት ተዘግቶ ከዚያ በኋላ መልሶ ተከፍቷል። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ምንም ዓይነት ትምህርት ነክ እንቅስቀቃሴዎችን ማካሄድ አልተጀመረም።
ይህ የሆነው የሊባኖስ ትምህርት ሚኒስቴር የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ እስከ ወሩ መጨረሻ ድረስ እንዲዘጉ መወሰኑን ተከትሎ ነው።
ሚኒስትሩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በእስራኤል የአየር ድብደባ ከደቡባዊ ሊባኖስ የሚፈናቀሉ ዜጎችን ለማስጠለል ይውላሉ ብሏል።
በዚሁ ሳምንት መጀመርያ ላይ የሊባኖስ ዩኒቨርስቲ እስከዚህ ሳምንት መጨረሻ ድረስ ሁሉም ካምፓሶቹ ዝግ እንደሚሆኑ አስታውቆ ነበር።
ወደ ኦንላየን የዞሩት ትምህርቶች
ነጻ የትምህርት እድል አግኝተው በኤዩቢ የሚማሩት አፍሪካውያን ተማሪዎች ወደ አገራቸው ተመልሰው ትምህርታቸውን በኦንላየን እንዲከታተሉ አማራጭ ቀርቦላቸዋል።
ነገር ግን አንዳንድ ተማሪዎች ይህ የሚቻል አለመሆኑን ገልጸዋል።
ከሰሜናዊ ኡጋንዳ የመጣችው የ27 ዓመቷ ሻሮን አትያንግ በኤዩቢ ዩኒቨርስቲ በማኅበረሰብ ልማት የሁለተኛ ዲግሪዋን እየተማረች ነው።
ትምህርቷን ወደ አገሯ ተመልሳ ለማጠናቀቅ የኤሌክትሪክ እና የኢንተርኔት መቆራረጥ ከባድ ያደርግባታል።
“ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝቼ ነው እዚህ ያለሁት።ወደ አገሬ ተመልሼ ብሄድ ነገሮች ሲረጋጉ እንደሚመልሱኝ እርግጠኛ አይደለሁም ” ብላለች ለቢቢሲ።
ከካሜሮን ለመጣችው አዴል፣ ስሟ ለደህንነቷ ሲባል ተቀይሯል፣ ወደ አገሯ ተመልሳ የጀመረችውን የራዲዮሎጂ ትምህርት በኦንላየን ማጠናቀቅ የሚታሰብ አይደለም።
“አገር ቤት ሄጄ በሆስፒታሎች የሚኖረኝን የስራ ላይ ልምምድ ማድረግ አልችልም፤ ነገር ግን ዲግሪዬን ለማጠናቀቅ ማድረግ ካሉብኝ ነገሮች መካከል አንዱ ነው” ብላለች።
ድንገት በቤሩት ሌላ ጥቃት ከተፈጸመ በሚል ሻንጣዎቿን ሸካክፋ ተዘጋጅታ ትጠብቃለች።
“ብድግ ብዬ ለመሄድ እንድችል ሁሉም ነገሬ ተዘገጃጅቷል።”
የማስተር ካርድ ነጻ የትምህርት ዕድል ፕሮግራም በሊባኖስ የሚገኙ በርካታ አፍሪካውያን ተማሪዎችን በገንዘብ ያግዛል።
ማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ተማሪዎቹን ለመደገፍ ከዩኒቨርስቲው ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን እና ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን ይናገራል።
ቃል አቀባዩ “ኤዩቢ ከተማሪዎቹ ጋር በየጊዜው መረጃ ይለዋወጣል፤ እንዲሁም ለጤናቸው እና ለደህንነታቸው ድጋፍ ያደርጋል።”
“የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታው ካለው ሁኔታ ጋር እንዲጣጣምተደርጓል፤ እንዲሁም አስፈላጊ ነገሮች የተፈጠረውን እክል ያገናዘቡ እንዲሆኑ እና ለመማር የተመዘገቡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበትን ሁኔታ ያገናዘበ እንዲሆን ተደርጓል። ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ደግሞ ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ከሆነ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።”
ከቤሩት በአውሮፕላን ለመውጣት ለሚፈልጉ በረራ ያልተቋረጠ ቢሆንምግን ቲኬት ማግኘት እጅጉን ከብዷል።
ኤሚሬትስ፣ ኳታር ኤርዌይስ፣ ኤር ፍራንስ እንዲሁም ሉፍታንዛ ወደ ከተማዋ ወይንም ከከተማዋ ውጪ የሚደረጉ በረራዎቻቸውን ሰርዘዋል።
“ትኩረታችንን መሰብሰብ አልቻልንም”
ሻሮን የእስራኤል ተዋጊ አውሮፕላኖች ዝቅ ብለው በመብረር የሚፈጽሙት የአየር ጥቃት ፍንዳታን መኝታ ክፍሏ ሆና እንደሚሰማት ትናገራለች።
“ማንበብያ ክፍሌ ውስጥ ነበርኩኝ። የድምጽ መከላከያው ሲሰበር ስሰማ ሮጥኩኝ። ነገር ግን የምሸሽበት ስፍራ አልነበረኝም። ሽንት ቤት ውስጥ ተደብቄ ነው ራሴን አገኘሁት” ትላለች።
ሌላ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል እያሉ መጠበቁ “በስሜትም በአእምሮም እንዳልረጋጋ አድርጎኛል፤ ምንም ነገር መስራት እንዳልችል ሆኛለሁ” ስትል ታክላለች።
በመቀጠልም በርካታ ተማሪዎች ለፕሮፌሰሮቻቸው የተሰጣቸውን ስራ ማስረከብያ ቀን እንዲራዘምላቸው መጠየቃቸውን ትናገራለች።
ሻሮን የመመረቅያ ጽሑፏን እየጻፈች፣ እያጠናች በመካከል ደግሞ ኡጋንዳ ከሚገኙ ቤተሰቦቿ ያለማቋረጥ የሚደወለውን ስልክ ትመልሳለች።
“ወደ ቤት እንድመለስ ይፈልጋሉ። ከትምህርቴ ይልቅ ለሕይወቴ ቅድምያ እንድሰጥ ነው የሚፈልጉት” ትላለች።
የተወሰኑ የአፍሪካ መንግሥታት ዜጎቻቸውን ማስወጣት ጀምረዋል። የኬንያ መንግሥት ዜጎቹን ማስወጣት ከጀመሩት መካለከል አንዱ ነው።
የዲያስፖራ ጉዳዮች ተቀዳሚ ጸሀፊ የሆኑት ሮዝሊን ንጆጉ በነሐሴ ወር ዘጠኝ ኬንያውያንን ማስወጣታቸውን አረጋግጠዋል።
ሌሎች አገሪቱን ለቅቀው መውጣት የሚፈልጉ ኬንያውያን ካሉም ወደ ኤምባሲ በመሄድ እንዲመዘገቡ መክረዋል።
በአሁን ሰዓት ሊባኖስ ውስጥ 26 ሺህ ኬንያውያን ይገኛሉ።
ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የነበሩት ነብዩ ተድላ ለቢቢሲ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን አስታውቀው “አስፈላጊ ከሆነ ዜጎቻችንን ለማስወጣት እቅዶችን እያዘጋጀን ነው” ብለው ነበር።
አክለውም ሊባኖስ ውስጥ አብዛኞቹ በቤት ውስጥ ሠራተኛነት የሚያገለግሉ 150 ሺህ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ተናግዋል።
የተወሰኑት እነዚህ ሰራተኞች ለቅቀው ለመሄድ ከአሰሪዎቻቸው ይሁንታ ማግኘት ስላለባቸው፣ ሊባኖስ በምትከተለው የካፋላ ስርዓት ምክንያት፣ ለተጨማሪ ችግር ተዳርገዋል።
እንደ ፋራዒ እና ሻሮን ላሉ ተማሪዎች ደግሞ አገሪቱን ጣጥሎ ለመሄድ ቀላል ይመስላል።
ነገር ግን ትምህርታቸውን ለመጨረስ ያላቸው ብርቱ ፍላጎት ወደ ኋላ ይጎትታቸዋል። ሁለቱም በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት አንድ ውሳኔ ላይ እንደሚደርሱ ይናገራሉ።
ሻሮን አክላም ለአፍሪካውያን ተማሪዎች ከባድ ነው ትላለች።
“ለራሳችን ያለነው ራሳችን ነን፤ ራሳችንን ከአደጋ መጠበቅ ያለብን ራሳችን ነን” ስትል ታክላለች።