ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ60,000 በላይ ሰዎች ኤል-ፋሸር ከተማን ጥለው እንደወጡ ተመድ አስታወቀ
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ኤል-ፋሸርን ከተቆጣጠረ በኋላ ከ60,000 በላይ ሰዎች ከተማዋን ጥለው እንደሸሹ የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ።
ከሱዳን ቁልፍ ከተሞች አንዷ የሆነችው ኤል-ፋሸር በፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ቁጥጥር ሥር መዋሏን ተከትሎ የጅምላ ግድያ እና ረሃብ መስፋፋቱ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት "የዘፈቀደ ግድያ" እየተፈጸመ መሆኑን ገልጿል። የዬል ዩኒቨርስቲ ሰብአዊ ጉዳዮች ጥናት ክፍልም የሳተላይት ምሥል በመጠቀም ባደረገው ዳሰሳ "በዘፈቀደ የተገደሉ ሰዎች አስክሬን" መመልከቱን አስታውቋል።
በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) የሚሠሩት ዩጂን ቢዮን ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ የኤል-ፋሸር ነዋሪዎች ከከተማዋ በ80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ታዊላ ከተማ ሸሽተዋል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት ከተማዋን ጥለው የሚወጡ ነዋሪዎች ቁጥር መጨመሩንም ገልጸዋል።
ዩኤንኤችሲአር ለተፈናቃዮቹ መጠለያ እና ምግብ ለማዳረስ መቸገሩን የተቋሙ ሠራተኛ ተናግረዋል።
በከበባ ውስጥ ካለችው ኤል-ፋሸር የሸሹ ነዋሪዎች መደፈርን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙባቸው ገልጸዋል።
"ሁሉም ሕጻናት በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው" ብለዋል።
በኤል-ፋሸር 130 ሺህ ሕጻናትን ጨምሮ 250 ሺህ ሰላማዊ ሰዎች ይኖራሉ። ከተማዋ ከበባ ውስጥ ከገባች ወዲህ ሰብአዊ እርዳታ እያገኙ አይደለም።
አርኤስኤፍ በምዕራብ ዳርፉር የምትገኘውን ኤል-ፋሽር ከተቆጣጠረ በኋላ ከ150,000 በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች አሁንም ድረስ መውጣት አልቻሉም።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዋነኛነት አረብ ያልሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ይከሰሳል። አርኤስኤፍ በበኩሉ ንጹኃንን መግደሉን እና አረብ ያልሆኑ ነዋሪዎችን ዒላማ ማድረጉን አስተባብሏል።
በሌላ በኩል ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ 'አቡ ሉሉ' በሚል ስም የሚጠራውን ወታደሩን በጅምላ ግድያ ክስ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ይፋ አድርጓል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ ባደረው የመረጃ ማመሳከር ሥራ፤ አቡ ሉሉ በኤል-ፋሸር አቅራቢያ ያልታጠቁ ሰዎችን እንደገደለ ተጋልጧል። የቢቢሲን ዘገባ ተከትሎ ታጣቂው በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ቲክቶክ ከታጣቂው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ገጾች ማገዱን ለቢቢሲ ገልጿል።
በዳርፉር ግዛት የምትገኘው ኤል-ፋሸር ከተማ በአርኤስኤፍ ሥር መውደቋ የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት አካሄድ ለውጧል።
የሳተላይት ምሥሎት እንደሚያሳዩት በሆስፒታሎች ውስጥ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል። በከተማዋ ምሥራቃዊ ክፍል በኩል ለመውጣት ሲሞክሩ የነበሩ ነዋሪዎችም ተገድለዋል።
በእርስ በርስ ጦርነቱ በመላው ሱዳን ከ150,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ዩኒሴፍ እንዳለው ኤል-ፋሸር የሕጻናት ሰቆቃ፣ ሕመም፣ እንግልት እና ረሃብ ማዕከል ሆናለች።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ቢያንስ 600 ሺህ ሰዎች ከከተማዋ እና በአቅራቢያዋ ካሉ መጠለያዎች መፈናቀላቸውን ተቋሙ ገልጿል።
የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከሁለት ዓመት በፊት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሁለቱ ተገዳዳሪ ኃይሎች ኤል-ፋሸርን ለመቆጣጠር ተዋግተዋል።
የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብደል ፋታሕ አል-ቡርሐን አብዛኛውን ሰሜናዊ የሱዳን ክፍል ይቆጣጠራሉ።
ከካርቱም ወጥተው ፖርት ሱዳንን እንደ ዋና መቀመጫ እየተጠቀሙ ይገኛሉ። መንግሥታቸውን የተበባሩት መንግሥታት ዕውቅና ይሰጠዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጄነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) አብዛኛውን የዳርፉር ግዛት እና ኮርዶፋን ከተማን ጨምሮ ምዕራቡን የሱዳን ክፍል ይቆጣጠራሉ።