ኢኳዶራውያን አሜሪካ በአገራቸው ልታቋቁመው የነበረውን የጦር ሠፈር በሕዝበ ውሳኔ ውድቅ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኢኳዶራውያን በአገሪቱ ውስጥ የውጭ ወታደራዊ ጦር ሠፈሮችን መፍቀድን በመቃወም ድምጽ የሰጡ ሲሆን ይህም አሜሪካን በምሥራቅ ፓስፊክ የጦር ሠፈሯን ለማስፋት ያላትን ተስፋ አጨልሟል።
የሕዝበ ውሳኔው ውጤት በአውሮፓውያኑ 2008 የአገሪቱ ሕግ አውጪ ምክር ቤት ያፀደቀውን እገዳ ለመቀልበስ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ለነበሩት የኢኳዶሩ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ኖቦአ ትልቅ ኪሳራ ነው።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የውጭ አገራት የጦር ሠፈራቸውን በአገሪቱ የባሕር ዳርቻዎች ላይ ማቋቋማቸው የተደራጁ ወንጀሎችን ለመዋጋት እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለውን ግጭት ለመቀነስ ይረዳል ሲሉ ለሕጉ ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል።
ኢኳዶር የዓለማችን ግዙፍ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች መተላለፊያ ነች።
አሜሪካ በፓስፊክ የባሕር ዳርቻ ያላት ጦር ሠፈር ከተዘጋ ከ16 ዓመታት በኋላ ሕዝበ ውሳኔው ወታደራዊ ሠፈር ለመክፈት ያስችላል የሚል ተስፋ ነበራት።
ኢኳዶር ኮኬይን ባታመርትም ብዙ አደንዛዥ ዕጽ ለሚመረትባቸው ኮሎምቢያ እና ፔሩ ግዙፍ ወደቦቿ ያላቸው ቅርበት በአዘዋዋሪዎች ቡድን ተፈላጊ እና ተመራጭ አድርጓታል።
እንደ ፕሬዝዳንት ኖቦአ ገለጻ 70 በመቶ የሚሆነው የዓለም ኮኬይን የሚያልፈው በኢኳዶር በኩል ነው።
ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ወንበዴዎች ላይ ጠንካራ ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ እና የጦር ኃይሉን በዋና ዋና መንገዶች ላይ በማሰማራት ይታወቃሉ።
ደጋፊዎቻቸው ይህ የፕሬዝዳንቱ አካሄድ ወንጀልን ለመዋጋት ረድቷል ሲሉ፣ ተቺዎቻቸው ግን መንግሥታቸው አምባገነናዊ ስልቶችን ተጠቅሟል ብለዋል።
በኢኳዶር የፓሲፊክ የባሕር ዳርቻ ላይ ይገኝ የነበረው የአሜሪካ የጦር ሠፈር የተዘጋው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ራፋኤል ኮርሪያ የሊዝ ውሉን ላለማደስ በመወሰን ሕገ መንግሥታዊ እገዳ እንዲጣል ካደረጉ በኋላ ነው።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ክሪስቲ ኖም በቅርቡ ከኖቦአ ጋር በኢኳዶር የሚገኙ ወታደራዊ ተቋማትን ጎብኝተዋል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ኖቦአ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የውጭ "ሠራዊቶች" በአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚያካሄዱትን "ጦርነት" እንዲቀላቀሉ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በቅርቡ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር በቀጠናው የፀጥታ እና የስደተኞች ትብብር ላይ ውይይት አድርገዋል።
ሕዝበ ውሳኔው በተጨማሪም መራጮች ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን የሕዝብ ገንዘብ ድጋፍ ውድቅ ሲያደርጉ፣ የኮንግረሱን መጠን እንዲቀነስ እና የኢኳዶሩን ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል ሕገ-መንግሥታዊ ጉባኤ እንዲቋቋም ድምጽ ሰጥተዋል።
ኖቦአ አዲስ ሕገ መንግሥት በወንጀለኞች ላይ ከባድ ቅጣት እና ድንበሮችን ለማስጠበቅ ጠንካራ እርምጃዎችን ይፈቅዳል ብለዋል።
ነገር ግን ተቺዎች እንደ የደኅንነት እጦት እና በአንዳንድ አካባቢዎች የትምህርት እና የጤና እንክብካቤ የመሳሰሉ ሰፊ ማኅበራዊ ችግሮችን እንደማይፈታ በመግለጽ እርምጃውን ተቃውመዋል።
ኖቦአ የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት "አከብራለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደው አሜሪካ በአስርት ዓመታት ውስጥ ትልቅ ነው የተባለውን የጦር ሠፈር፣ የዓለም ትልቁን የጦር መርከብ እና የጦር አውሮፕላን ተሸካሚን ወደ ካሪቢያን ባስጠጋችበት ወቅት ነው።
አሜሪካ በምሥራቅ ፓስፊክ እና ካሪቢያን አካባቢ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ናቸው በተባሉ መርከቦች ላይ ቢያንስ 21 ጥቃቶችን ፈጽማ በትንሹ 83 ሰዎች ተገድለዋል።
በጀልባዎቹ ውስጥ ማን እንደነበር ምንም ዓይነት ማስረጃ ያልቀረበ ሲሆን፣ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የአየር ድብደባው ዓለም አቀፍ ሕግን ሊጥስ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።
አሜሪካ በቬንዙዌላ የምድር ዒላማዎችን ላይ ጥቃት ትፈጽማለች የሚሉ ግምቶች አሉ።
ከዚህ ቀደም ዩናይትድ ስቴትስ የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ቡድን ኃላፊ ናቸው ስትል ወንጅላለች።
ይህንን ክስ ግን የአገሪቱ መንግሥት አስተባብሏል።
ብዙ ታዛቢዎች የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በአካባቢው እየጨመረ መምጣቱ ማዱሮ ከሥልጣን እንዲወርዱ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ ሙከራ ነው ብለው ያምናሉ።















