ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእስራኤል መንግሥት የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ስርጭት የሚያግደውን ሕግ ቆይታ አራዘመ
የእስራኤል ፓርላማ፤ መንግሥት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የውጭ አገር መገናኛ ብዙኃንን ስርጭትን እንዲዘጋ የሚፈቅደውን ሕግ ቆይታ ጊዜ አራዘመ።
በ22 ድጋፍ እና በ10 ተቃውሞ የጸደቀው ይህ ሕግ፤ በጋዛ ጦርነት ወቅት የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ተደርገው የታዩ መገናኛ ብዙኃንን ለመዝጋት ሥልጣን የሰጠ ነው። አሁን የጸደቀው ማሻሻያ የዚህን ጊዜያዊ ሥልጣን የቆይታ ጊዜ ያራዝማል።
በፓርላማው ውሳኔ መሠረት፤ የአገሪቱ መንግሥት ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት፤ በሰላም ጊዜ እንኳ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የውጭ መገናኛ ብዙኃን እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ ይችላል።
መጀመሪያ ላይ "የአልጀዚራ ሕግ" የሚል ስያሜ ይዞ የወጣው ይህ ሕግ፤ በግንቦት 2024 ባለቤትነቱ የኳታር የሆነውን የቴሌቪዥን ቻናል ቢሮዎች እና ስርጭት ለመዝጋት ጥቅም ላይ ውሏል።
አልጀዚራ በዘገባዎቹ፤ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በጋዛ የሚያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ጠንካራ ትችቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል። እስራኤል በበኩሏ አልጀዚራ ጸረ እስራኤል የሆኑ አድሎአዊ እንዲሁም ለሀማስ ድጋፍ የሚሰጡ ዘገባዎችን ያቀርባል በማለት ትከስሳለች።
የቀረቡበትን ክሶች ውድቅ ያደረገው አልጀዚራ ደግሞ የእስራኤልን እርምጃ "የወንጀል ድርጊት" እንዲሁም በፕሬስ ነጻነት ላይ የተከፈተ ጥቃት እንደሆነ በመግለጽ የአገሪቱን መንግሥት ውሳኔ አውግዟል።
'ዘ አሶሴሽን ፎር ሲቪል ራይትስ ኢን እስራኤል' የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድንም በበኩሉ ባለፈው ዓመት የአገሪቱ መንግሥትን ውሳኔ ተቃውሟል።
ጊዜያዊ እግዱ፤ "ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን፣ መረጃ የማግኘት መብትን እንዲሁም የፕሬስ ነጻነትን" እንደሚጥስ ገልጿል።
እርምጃው፤ "ዜጎች እና ነዋሪዎች ከእስራኤል ትርክት ጋር የማይጣጣሙ ወይም በእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ቻናሎች የማይተላፉ የተለያዩ መረጃዎችን እንዳያገኙ ይከለክላል" በማለትም ትችቱን አሰምቷል።
የዚህን ውሳኔ የቆይታ ጊዜ የሚያራዝመው ሕግ የጸደቀው፤ የእስራኤል ካቢኔ የሠራዊቱ የራዲዮ ጣቢያ እንዲዘጋ የቀረበውን ውሳኔ ካጸደቀ ከሰዓታት በኋላ ነው። በመንግሥት ገንዘብ የሚንቀሳቀሰው የራዲዮ ጣቢያ በእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የሚመራ ቢሆንም የኤዲቶሪያል ነጻነት አለው።
በመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ የቀረበው እቅድ ከመጋቢት 2026 ጀምሮ ጣቢያው ስራውን እንዲያቆም ያደርጋል።
ሚኒስትሩ ካትዝ፤ በስራ ላይ ያሉ ወታደሮችን እና ሲቪሊያን ሰዎችን የሚቀጥረው ይህ ራዲዮ ጣቢያ፤ "የወታደሮች አፍ እና ጆሮ ሆኖ ማገልገል አቁሟል" በማለት ይከራከራሉ። "ከመከላከያ ሠራዊቱ እሴቶች ጋር የማይጣጣሙ ፖለቲካዊ እና ከፋፋይ ይዘቶችን ያሰራጫል" ሲሉም ክስሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው በሠራዊቱ ስር የሚተዳደር የራዲዮ ጣቢያ እጅጉን ያልተለመደ አሰራር እንደሆነ በካቤኒው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
"ሰሜን ኮርያ ውስጥ እና ምንአልባት ጥቂት አገራት ውስጥ ያለ ይመስለኛል። ከእነዚህ አገራት አንዱ ተደርገን መቆጠር አንፈልግም" ብለዋል።
የጋዜጠኖች ማህበር እና የጋዜጠኞች ድርጅቶች ግን ውሳኔውን የሚቃወም ፊርማ አሰባስበው ለአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል። ድርጊቱንም "ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እና የፕሬስ ነጻነት ላይ የተፈጸመ ከፍተኛ እና ሕገ ወጥ ጥሰት" በማለት ጠርተውታል።
'ዘ እስራኤል ዴሞክራሲ ኢንስቲትዩት' የተባለው ቲንክ ታንክ በበኩ የሠራዊቱ ራዲዮ ጣቢያ መዘጋቱ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የተፈጸመ ከፍተኛ ጥሰት እንደሆነ ገልጿል። እርምጃው በእስራኤል ከሚገኙ ገለልተኛ የሕዝብ ራዲዮ ስርጭቶች ውስጥ ግማሽ ያህሉን ወዲያውኑ የሚዘጋ እንደሆነም አክሏል።
የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ድርጅቱን ለመዝጋት የተላለፈው ውሳኔ "ራሱን የቻለ ብቸኛ እርምጃ አይደለም። የእስራኤል ዴሞክራሲ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሰፊ እና አሳሳቢ አካሄዶች አካል ነው" ሲልም አስጠንቅቋል።