ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስጦታ የሚለዋወጡት እንሰሳት
ስጦታ የሚለዋወጡት የሰው ልጆች ብቻ አይደሉም። በእንሰሳት ዓለምም የተለመደ ነው።
ስኮርፒዮንፍላይ የተባለችው በራሪ ነፍሳት ከፍቅረኛዋ የሚሰጣት ስጦታ ምራቅ ነው። ይህም ለስሪያ የሚጋብዝበት መንገድ ነው።
ሌሎች እንደ ቀንድ አውጣና የአፈር ትል ባሉ ነፍሳትና ትላትሎች ዘንድም የተለመደ ነው። በአብዛኛው ከስሪያ ጋር የተያያዘ የስጦታ ልውውጥ ያከናውናሉ። በአእዋፍት ዘንድም ይስተዋላል።
ግሬት ግሬይ ሽሪክስ የተባሉት የወፍ ዝርያዎች ወንዶች ሴቶችን ለማማለል እሾሃማ የዛፍ ቅርጫፍ በስጦታ ያቀርባሉ።
በሳይንሳዊ ስሙ አራክኒድ የሚባለው የሸረሪት ዓይትም ስጦታ በመስጠት ይታወቃል።
ነርሰሪ ዌብ ስፓይደር የሚባለው ሸረሪት ለምግብነት የሚውሉ ነፍሳት የበለጠ ማራኪ እንዲሆኑ ኬሚካል አርከፍክፈው ለሴቷ ሸረሪት በስጦታ ያቀርባሉ።
አንዳንድ ሸረሪቶች ጥራቱ የወረደ ወይም በከፊል የተበላ ምግብ በስጦታ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ሴቷ ሸረሪት ስጦታውን ለማየት ጥቅልሉን እስከምትፈታ ድረስ ወንዱ ሸረሪት ስሪያውን አከናውኖ ሮጦ ይጠፋል።
አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ወደ 70 በመቶ የወንድ ሸረሪት ስጦታዎች ሐሰተኛ ናቸው።
ብል የተባለው ነፍሳት በወንድ የዘር ፈሳሽ ውስጥ ለሴቷ ሲያናይድ የተባለውን ንጥረ ነገር ያስተላልፋል።
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ቶሮንቶ፣ ካናዳ የእንሰሳት ባህሪ አጥኚ ደሪል ግዌን "የሚያጭበረብሩ ወንዶች ማግኘት የተለመደ ነው። ያረጀ ነፍሳት ጠቅልለው ስጦታ ለመስጠት ይሞክራሉ" ሲል ያስረዳል።
"ዳንስ ፍላይስ የተባለው ነፍሳት የባሕር ነፍሳት አድኖ ይይዛል። ሴቶቹ ያደነውን ለመውሰድ ይፎካከራሉ። ምክንያቱም ራሳቸውን መመገብ አይችሉም። እንቁላል ለማምረት ደግሞ መመገብ አለባቸው" ይላል።
ስጦታ የሚያጭበረብሩ ወንዶች በድጋሚ ከሴት ነፍሳት ጋር ስሪያ መፈጸም አይችሉም።
ሴቷ ስጦታው ሐሰተኛ እንደሆነ ካወቀች በኋላ ከወንዱ ጋር ግንኙነት እንዲኖራት አትፈልግም። የወንድ የዘር ፍፌው ከእንቁላሏ ጋር የመዋሀድ ዕድሉም ጠባብ ይሆናል።
አንዳንድ ነፍሳት ስጦታ የሚያቀርቡት ራሳቸውን ነው።
ሳገርቡሽ ክሪኬት ክንፉን ሴቷ እንድትበሳውና ደሙን እንድትመጠው ይፈቅዳል።
አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ አንድ ወንድ ነፍሳት ይህንን ካደረገ በኋላ ከሌላ ሴት ነፍሳት ጋር ግንኙነት የመፍጠር ዕድሉ ይጠባል።
ሌላ የፍቅር ግንኙነት ለመፍጠር ዐቅም ያጥራቸዋል።
ሬድ ብላክ የተባለው የሸረሪት ዓይነት በስሪያ ወቅት የሴቷ አፍ ውስጥ ይገባል። በዚህ ሂደት ሴቷ ትውጠዋለች።
"ሕይወቱን ነው አሳልፎ የሚሰጠው። በዳርዊንያን ዕሳቤ እነዚህ የሸረሪት ዓይነቶች ሴት ሸረሪት ሁሌም አያገኙም። ራሳቸውን እንደ ምግብ በማቅረብ በሴቷ ሲዋጡ ብዙ የዘር ፍሬ ወደ ሴቷ ሰውነት ያስገባሉ። በዚህ መንገድ ራሳቸውንም ይተካሉ" ይላል ባለሙያው።
የነፍሳት ተመራማሪዋ ሹፍሪ ታንግ እንደምትለው፣ 99 ሚሊዮን ዓመታት በኖረ የደረቀ ዛፍ ፍሬ ውስጥ አልቬሳ የተባለው በራሪ ነፍሳት በእግሮቹ መካከል ከምራቅ የተሠራ ፊኛ ይዞ ተገኝቷል።
እንሰሳት በብዛት ስጦታ የሚሰጡት ለስሪያ ቢሆንም፣ አንዳንዴም ስጦታ በመስጠት ደስታን ለመፍጠር ይሞክራሉ።
ምግብ በስጦታ ሲሰጡ በውስጡ ያለው ንጥረ ነገር ለሴቶች ጠቃሚ ይሆናል።
ዶልፊን የተባለው የዓሣ ዝርያ ለሰዎች ቱና፣ ኢልና ሌሎችም የዓሣ ዝርያዎችን በስጦታ ይሰጣል። ቁራም ለሰዎች ስጦታ ይሰጣል።
በዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካምብሪጅ የእንሰሳት ባህሪ አጥኚ የሆነችው ኒኮላ ክሌይተን "ላሞች ስጦታ ሰጥተውኝ ያውቃሉ። ለውዝ፣ የወይን ዛፍ፣ የቢራ ጠንሙስ የመሳሰሉ ስጦታዎች ሰጥተውኛል" ትላለች።
የቁራ ዓይነት የሆው ዩሬዥያን ጄይ ወንዶች ለሴቶች ስጦታ ይሰጣሉ። የሚሰጡት መስጠት ደስ ስለሚላቸው ነው።
ኒኮላ በሠራችው ጥናት ወንድ እንሰሳት ስጦታ ከሰጡ በኋላ ሴቶቹ እንሰሳት የተሰጣቸውን ትል ወይም ብል ሲመገቡ ይመለከታሉ።
ወንዶቹ እንሰሳት በተለያየ ጊዜ የተለያየ ነፍሳት በስጦታ ይሰጣሉ።
"ፓስታ እራት የበላ ሰው መልሶ ፓስታ መብላት እንደማይፈልገው ነው" ትላለች አጥኚዋ።
ቦኖቦ የተባሉት የዝንጀሮ ዝርያዎችም ስጦታ በመለዋወጥ ይታወቃሉ።
ከሰዎች ጋር 99% ዘረ መል ይጋራሉ።
እአአ በ2013 በተሠራ ጥናት መሠረት፣ በእርዳታ መልክ ስጦታ ሲሰጡም ይስተዋላሉ። በሌላ ቡድን ውስጥ ላሉ ቦኖቦዎች ሙዝና ሌላም ፍራፍሬ ይለግሳሉ።
እንሰሳት በዝግመተ ለውጥ ሒደት ውስጥ ስጦታ መለዋወጥን ዘር ከመተካት አንጻር ይከውኑታል።
የእንሰሳት ባህሪ አጥኚው ደሪል ግዌን ነፍሳትና ሸረሪት ወንዶች ለሴቶች "ምግብ በስጦታ በመስጠት ስሪያ ይፈጽማሉ" ይላል።
የእንሰሳት ባህሪ አጥኚ የሆነችው ኒኮላ ክሌይተን "ነፍሳት ስጦታ ሲሰጡ ለስሪያ ነው። እንደ ጄይ ያሉ አእዋፍ ግን ስጦታ ሲሰጡ ለጉቦ ሳይሆን ለሕይወት አጋርነት መምረጥን ለማሳየት ነው" ትላለች።
እነዚን አእዋፍ በማሰላሰል የላቀ ደረጃ ላይ ያሉና ዕድሜ ልካቸውን ከፍቅር አጋራቸው ጋር የሚኖሩ ናቸው።
እንደ ቁራ ያሉ ወፎች እንደ ሰው ልጆች ስጦታ መስጠት ደስ ስለሚላቸው ነው የሚሰጡት።