ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አውስትራሊያ ፡ ኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት አስተዳደርን ለሁለት የከፈለው የዱር እንስሳ
የአውስትራሊያዋ ኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት መንግሥት 'ኮዋላ' የተባሉትን የዱር እስሳት እንዴት እንጠብቅ በሚለው ፖሊሲ ላይ መስማማት አቅቷት ኃላፊዎቿ በሁለት ጎራ ተከፍለው እየተጨቃጨቁ ነው።
ወደ መንግሥት መዋቅር በቅርቡ የተቀላቀለው ብሔራዊ ፓርቲ ከዚህ በኋላ መንግሥት የሚያቀርባቸውን ፖሊሲዎች እንደማይደግፍ ያስታወቀ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ለኮዋላዎች የተዘጋጀውን ፖሊሲ ስለሚቃወም ነው ብሏል።
ነገር ግን የፓርቲው ምክትል ኃላፊ ጆን ባሪላሮ ''እኛ ኮዋላዎችን አንጠላም'' ብለዋል።
አክለውም በፓርቲያቸው ውስጥ የሚገኙ ሕግ አውጪዎች ከዚህ በኋላ ከሊብራል ፓርቲ አባላት ጋር ፓርላማ ውስጥ መቀመጥ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
በሲድኒ ሄራልድ ''የኮዋላ ጦርነት'' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ አለመግባባት ከመንግሥት የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ እቅድ ጋር የተገናኘ ሲሆን ፖሊሲው ባለፈው ዓመት ታህሳስ ላይ ሕግ ሆኖ ጸድቋል።
የሕጉ ዋና አላማም ኮዋላዎችን መጠበቅና መንከባከብ እንዲሁም መኖሪያ አካባቢያቸውን ምቹ ማድረግ ነው።
ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ደግሞ አፋጣኝ እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ኮዋላዎች በአውሮፓውያኑ 2050 ከምድረ ገጽ ሊጠፉ እንደሚችሉ ተገልጾ ነበር።
ባለፈው የፈረንጆቹ የበጋ ወቅት ተከስቶ በነበረው የዱር ሰደድ እሳት ደግሞ ሦስት ቢሊየን እንስሳትን ጎድቷል አልያም ገድሏል የሚል ግምት ተቀምጦ ነበር።
ነገር ግን የፓርቲው ምክትል ኃላፊ ጆን ባሪላሮ ፖሊሲው ኮዋላዎችን ከመታደግ ባለፈ ዜጎችን ለሌሎች ችግሮች የሚያጋልጥና ሰፋፊ መሬት ያላቸውን ሰዎች መሬታቸውን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባቸው ለመንገር የሚሞክር ነው በማለት ተችተዋል።
''እኛ እንደሚመስለን ፖሊሲው አካባቢውን ለመጽዳትና በክልሉ የሚገኙ የመሬት ባለቤቶችን ለማጥቃት የታሰበና ከኮዋላዎች ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ነገር ነው'' ብለዋል።
አክለውም ''ብሄራዊ ፓርቲው የኮዋላዎች ብዛት እንዲጨምር ይፈልጋል። እንደውም ኮዋላዎች አሁን ካላቸው ቁጥር በእጥፍ እንዲያድጉ እንፈልጋለን። እኛ ጸረ ኮዋላዎች አይደለንም'' ሲሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን የሊብራል ፓርቲው ፖለቲከኞች "እርምጃው ተገቢና የአካባቢውን ማሕበረሰብ የሚደግፍ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
የፌደራል ግሪንስ ፓርቲ መሪው አዳም ባንዲት በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክትም '' እነሱ የመንግሥትን የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ የማይቀበሉት ሕግ የማያከብሩ የመሬት ባለቤቶች ተጨማሪ ኮዋላዎችን መግደል እንዲችሉ ነው'' ብለዋል።
አንዳንድ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ደግሞ እንደውም አሁን ያለው የመንግሥት ፖሊሲ እንስሳትን ከጉዳት ለመከላከል በቂ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ።