የሶማሊያውን ፕሬዚዳንት ዘልፈዋል የተባሉ ቲክቶከሮች በቁጥጥር ስር ዋሉ

እአአ በ2022 ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ምርጫን በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠዋል

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እአአ በ2022 ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ምርጫን በማሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠዋል

የሶማሊያ ፖሊስ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድን በዳንስ ቪዲዮቸው ላይ ዘልፈዋል ያላቸውን አራት ቲክቶከሮች በቁጥጥር ስር አዋለ።

በርካታ ወጣት ሶማሊያውያን እአአ በ2022 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ለቅስቀሳ የዋለን ሙዚቃ በመጠቀም እና ግጥሙ ላይ ዘለፋ በማካተት ሲደንሱ ታይተዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በማረሚያ ቤት እንደሚገኙ በመግለጫው ላይ ገልጾ ክስ ይመሰረትባቸዋል ብሏል።

ቲክቶከሮቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ጀምሮ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የአገሪቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጎሳ ተኮር ስድብ በማሰራጨት፣ በቲክቶክ ላይ ቅስቀሳ በማድረግ ወይም "ኢ ሥነምግባራዊ" የሆኑ ይዘቶችን በማሰራጨት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህ ግን ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ካለ ፖለቲከኛ ጋር የተያያዘ የመጀመርያው እስር ነው።

በ2016 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ላይ ሕዝባዊ አመጽ በመቀስቀስ እና ኢ ሥነ ምግባራዊ የሆነ ድርጊቶች በማሰራጨት በሚል ክስ ሰባት ቲክቶከሮች ሞቃዲሾ የሚገኝ ፍርድ ቤት የስድስት ወራት እስር ፈርዶባቸዋል።

ባለሥልጣናት በቅርቡ በተለቀቁ ቪዲዮዎች ላይ የታየው ባህሪ በሶማሊያ የወንጀል ሕግ መሠረት ጥፋት ነው ብለዋል።

የመጀመርያው ቪዲዮ ከቲክቶክ ላይ የተሰረዘ ቢሆንም ቲክቶክን ጨምሮ በሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሰፊው ተሰራጭቷል።

የፖሊስ ቃል አቀባይ ጄነራል አብዲፋታህ አደን በተመሳሳይ ብሔራዊ ተቋማት ወይም መሪዎችን በሚያዋርድ ተግባር ላይ የሚሰማራ ማንኛውም አካል "ሕግ ፊት ይቀርባል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የቲክቶከሮቹ መታሰር ማኅበራዊ ሚዲያ በተለይ ደግሞ ቲክቶክ በሶማሊያ ስላለው ሚና ዳግም ክርክር ቀስቅሷል።

ከዚህ ቀደም ይህ ማኅበራዊ ሚዲያ በሶማሊያ ፖለቲካ እና የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ስላለው ሚና ሰፊ ክርክር ተካሄዶ ነበር።

ቲክቶክ በወጣት የሶማሊያ ዲያስፖራ ዘንድ በስፋት ፖለቲካ ላይ አስተያየት ለመስጠት እና ትችት ለማቅረብ ጥቅም ላይ ይውላል።

በርካታ ሰዎች የንግድ ስራቸውን ለማቀላጠፍ እንዲሁም ለመዝናኛነት ይገለገሉበታል።

እአአ በ2023 መንግሥት ማኅበራዊ ሚዲያው ለብሔራዊ ደህንንት ስጋት መሆኑን፣ ሐሰተኛ መረጃ ያሰራጫል እንዲሁም ማኅበራዊ እና ሥነ ምግባራዊ ዕሴቶችን ይሸረሽራል በሚል ይታገዳል ብሎ ነበር።

በወቅቱ ከሕዝቡ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ በመቀስቀሱ እገዳው ሊጣል አልቻለም።

ነገር ግን ባለሥልጣናት ማኅበራዊ ሚዲያው ጎጂ ይዘት ያላቸው በተለይ ደግሞ ዋልታ ረገጥ የሆኑ ፕሮፓጋንዳዎችን ይሰራጩበታል፤ እንዲሁም ስም የሚያጠለሹ ይዘቶች ይሰራጩበታል ሲሉ ይኮንናሉ።