ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቴክሳስ የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 78 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች የደረሱበት እንዳልታወቀ ተገለጸ
በማዕከላዊ ቴክሳስ አርብ ዕለት በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢያንስ 78 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ፤ ሌሎች 41 ሰዎች ደግሞ እስካሁን እንዳልተገኙ ተገለጸ።
28 ልጆችን ጨምሮ 78 ያህል ሰዎች የሞቱት በኬር ካውንቲ በወንዝ ዳርቻ የሚገኝ የክርስቲያን ሴት ልጆች ካምፕ በጎርፍ በመጥለቅለቁ ነው።
አስር ሴት ልጆች እና አንድ የካምፑ ሠራተኛ አሁንም እንደጠፉ ነው።
ባለሥልጣናት የሟቾች ቁጥር ከዚህም እንደሚጨምር በእርግጠኝነት ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ውስጥ በአካባቢው ተጨማሪ ከባድ አውሎ ነፋስ ይከሰታል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ መሆኑ ቀድሞውኑ በጭቃ እና በፍርስራሾች ውስጥ ፍለጋ በሚያከናውኑበት ጊዜ መርዛማ እባቦችን ሲጋፈጡ የነበሩ የነፍስ አድን ቡድኖችን ፍለጋ ሊያደናቅፍ እንደሚችል ተሰግቷል።
በቅርብ ጊዜ የቴክሳስ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የተባለው የፍለጋ እና የነፍስ አድን ጥረት ከጎርፍ መጥለቅለቁ መከሰት ከሦስት ቀናት በኋላ፤ ትኩረቱን ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን አስከሬን ወደ መፈለግ ዞሯል።
በኬር ካውንቲ ከተገኙ አስከሬኖች መካከል 18 አዋቂዎች እና 10 ሕፃናት እስካሁን በይፋ ማንነታቸው አልተለየም። የቴክሳስ ገዥ ግሬግ አቦት፤ ባለሥልጣናት እያንዳንዱ የጠፉ ሰዎች መገኘታቸውን ሳያረጋግጡ "ምንም ነገር አያቆሙም" ሲሉ እሁድ ዕለት ተናግረዋል።
ገዢው፤ በአካባቢው ጉብኝት ካደረጉ አንድ ቀን በኋላ ባደረጉት ንግግር "እነዚያ ትናንሽ ልጆች ምን እንደደረሰባቸው ማየት በጣም አሰቃቂ ነበር" ብለዋል።
የፍለጋው ዋና ትኩረት በጓዳሉፔ ወንዝ ዳርቻ የሚገኘው ተቃዋቂው እና በጎርፉ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የሴት ልጆች የበጋ ካምፕ ነው።
አደጋው የተከሰተው አርብ ከንጋት በፊት ነው። ጎርፉ በተከሰተበት ሰዓት አብዛኞቹ በካምፑ የነበሩ ሰዎች ተኝተው የነበረ ሲሆን፣ በቅራቢያ የሚገኘው ወንዝ በ45 ደቂቃ ውስጥ ብቻ ከፍታው ወደ 8 ሜትር ጨምሯል።
በካምፑ ውስጥ የነበሩ በርካታ ልጆች እና የካምፑ የረጅም ጊዜ ዳይሬክተር ሪቻርድ ዲክ ኢስትላንድ ከሞቱት መካከል ናቸው።
የቀድሞው የባሕር ኃይል መኮንን እና '300 ጀስቲስ' የተባለው የነፍስ አድን ቡድን በጎ ፈቃደኛ የሆኑት ግሬግ ፎርሊክ፤ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ካሉት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ግሬግ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ተጎጂዎች ካምፑ ከሚገኝበት ስምንት ማይል ርቀት ድረስ በጎርፍ ተወስደው እንደተገኙ መስማታቸውን ተናግረዋል።
"የካምፕ ልብሶች እና መገልገያዎች ወንዙ ውስጥ በየቦታው ተበታትነው" መመልከታቸውንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በአሜሪካ የነጻነት ቀን ሐምሌ አራት በሚከበርበት የሳምንቱ መጨረሻ እንዴት በርካታ ሰዎች ካምፕ ለማድረግ እንደተጓዙ እና ምን ያህል ሰዎች በጎርፉ እንደተወሰዱ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።
የጉዋዳሉፕ ወንዝ አጠገብ የሚገኘው እና ኬርቪል ከተማን ከካምፕ ሚስቲክ ጋር የሚያገናኘው ባለ ሁለት መስመር የፍጥነት መንገድ ጎርፉ ያስከተለው ጉዳት የታየበት ሌላኛው ስፍራ ነው።
የወደሙ ቤቶች፤ በወደቁ ዛፎች ተከብበው እና የቤት ዕቃዎች ሜዳዎች በተታትነው ታይተዋል። አጥሮች የወደቁ ሲሆን እና በአንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መስመሮች ወድቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ እሁድ ዕለት በኬር ካውንቲ የሚተገበር ትልቅ የአደጋ ጊዜ አዋጅ በመፈረም፤ የፌዴራል የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ ወደ ቴክሳስ እንዲንቀሳቀስ አድርገዋል። በመጪው አርብ ግዛቱን እንደሚጎበኙም ተናግረዋል።
ትራምፕ፤ "ከቴክሳስ ተወካዮች ጋር በጣም በቅርበት እየሠራን ነው፤ የተከሰተው ነገር በጣም አስከፊ ነው" ሲሉ እሁድ ዕለት በኒው ጀርሲ ተናግረዋል።