ፈረንሳይ ወታደሮቿንና አምባሳደሯን ከኒጀር ልታስወጣ መሆኑን ፕሬዚደንት ማክሮን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኒጀር የተከሰተውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ፈረንሳይ አምባሳደሯን እንደምታስወጣ እና ከአገሪቷ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር እንደምታቆም ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ።
ማክሮን “ ፈረንሳይ ከኒጀር አምባሳደሯን ለማስወጣት ወስናለች። በሚቀጥሉት ሰዓታት አምባሳደራችን እና በርካታ ዲፕሎማቶች ወደ ፈረንሳይ ይመለሳሉ “ ብለዋል።
ፕሬዚደንቱ ጨምረውም ከአገሪቷ ጋር የሚኖረው ወታደራዊ ትብብር ማብቃቱንና የፈረንሳይ ወታደሮች በሚቀጥሉት ወራት ከአገሪቷ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ሐምሌ ወር ላይ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ኃይል ውሳኔው ተቀብሎታል።
የወታደራዊ ኃይሉ መሪ በሰጡት መግለጫም “ በአሁኑ እሑድ ኒጀር ወደ ሉዓላዊነቷ እያመራች ያለችበትን አዲስ እርምጃ እናከብራለን” ማለታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የባህር በር በሌላት የምዕራብ አፍሪካዋ አገር ከ1 ሺህ 500 በላይ የፈረንሳይ ወታደሮች ይገኛሉ።
ይህ የፓሪስ ውሳኔ የተሰማው በአገሪቷ የፈረንሳይ መገኘትን በመቃወም ለወራት በዋና መዲናዋ ኒያሚ በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፎች ከተካሄዱ፣ ግጭትና ተቃውሞ ከተከሰተ በኋላ ነው።
ፈረንሳይ ወታደሮቿን ከአገሪቷ የማስወጣት ውሳኔዋ በሳህል ቀጠና በእስላማዊ ታጣቂዎች ላይ እየወሰደች ያለችው እርምጃ ላይ እንዲሁም ፓሪስ በአገሪቷ ያላት ሚና ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሏል።
ሆኖም ማክሮን ለአገራቸው መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ "ፈረንሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ፈጻሚዎች አትታገትም" ብለዋል።
ማክሮን ጨምረውም ከሥልጣን የተወገዱትንና በመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ የታሰሩትን ፕሬዚደንት መሃመድ ባዙምን የኒጀር ሕጋዊ ባለሥልጣን አድርገው እንደሚመለከቷቸው ገልጸው፣ ውሳኔውንም እንዳሳወቋቸው ተናግረዋል።
ፕሬዚደንት ማክሮን ከሥልጣን የተወገዱትን ፕሬዚደንት " ታጋች" ሲሉም ገልጸዋቸዋል።
“ በመፈንቅለ መንግሥቱ ኢላማ የተደረጉት በአገሪቷ አበረታች ለውጦችን በማምጣታቸውና በፖለቲካዊ ሴራ ምክንያት ነው” ብለዋል።
ኒጀር በቅርቡ መፈንቅለ መንግሥት ከተፈፀመባቸው በምዕራብ አፍሪካ ከሚገኙ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ከነበሩ አገራት መካከል አንዷናት።
ቀደም ብሎ በቡርኪና ፋሶ፣ በጊኒ፣ በማሊ እና በቻድ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደ ሲሆን ወታደራዊ ኃይሎች ሥልጣን ተቆጣጥረዋል። ነሐሴ ወር ላይም በተመሳሳይ በጋቦን መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በቀጠናው ፀረ ፈረንሳይ ተቃውሞዎች በርትተዋል።
በርካታ የአገራቱ ፖለቲከኞች ፓሪስ የድህረ ቅኝ ግዛት ፖሊሲዎችን ትተገብራለች ሲሉ ይከሳሉ።ፈረንሳይ ግን ክሱን ውድቅ አድርገዋለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሳህል ቀጠና የሩሲያ ቫግነር ቅጥረኛ ቡድን ያለው ሚና እያደገ በመምጣቱ በምዕራብ አፍሪካ ስጋቶች አሉ።
ቅጥረኛ ቡድኑ የሰብዓዊ መብቶችን በመጣስ እና አዲስ ወታደራዊ መንግሥቶችን በመደገፍ ይከሰሳል።
በፈረንሳይ የሚደገፈው የምዕራብ አፈሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ( ኢኮዋስ)፣ ፕሬዚደንት መሃመድ ባዙምን ወደ ሥልጣን ለመመለስ በኒጀር ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ ዝቶ ነበር። ይሁን እንጅ እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም።
የኒጀር ጦር መሪዎች ለፈረንሳይ አምባሳደር ስይልቬን ኢቴ፣ ፕሬዚደንቱ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ አገሪቷን ለቀው መውጣት እንደነበረባቸው ተናግረዋል።
ሆኖም ነሐሴ ወር ላይ አገሪቷን ለቀው እንዲወጡ ተሰጥቷቸው የነበረው 48 ሰዓታት የፈረንሳይ መንግሥት “ሥልጣንን በኃይል የተቆጣጠሩ ግለሰቦች” እንዲህ ያለውን ማባረር ለማዘዝ “ሥልጣን የላቸውም” በማለቱ እና ለወታደራዊ ኃይሉ ሕጋዊ እውቅና አልሰጥም በማለቱ አልፏል።
ፕሬዚደንት ማክሮን የሰጡት መግለጫ የተሰማው የኒጀር መፈንቅለ ወታደራዊ መሪ የፈረንሳይ አውሮፕላን በአገሪቷ የአየር ክልል እንዳይበር ካገደ ከሰዓታት በኋላ ነው።
የቀጠናው የአየር ደኅንነት ድርጅት የኒጀር አየር ክልል ከፈረንሳይ አወሮፕላኖች አሊያም በፈረንሳይ ከሚላኩ አውሮፕላኖች በስተቀር ለአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ በረራዎች ክፍት ነው ብሏል።
ቀደም ብሎ ፈቃድ ካልተሰጠ በስተቀር የአየር ክልሉ ለሁሉም ወታደራዊ በረራዎች፣ ኦፕሬሽኖች እና ሌሎች ልዩ በረራዎች ዝግ ሆኖ እንደሚቆይም አስታውቋል።
ኤር ፍራንስ በበኩሉ በኒጀር የአየር ክልል እየበረረ እንዳልሆነ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ገልጿል።












