ትሬቨር ኖሀ ደቡብ አፍሪካን እንዲያስተዋውቅ ሊከፈለው የታሰበው 1.7 ሚሊዮን ዶላር ቁጣ አስነሳ

ኮሜድያን ትሬቨር ኖሀ ደቡብ አፍሪካን በቱሪዝም መዳረሻነት እንዲያስተዋውቅ 1.7 ሚሊዮን ዶላር (33 ሚሊዮን ራንድ) እንዲከፈለው የቀረበው ሐሳብ በደቡብ አፍሪካ ቁጣ አስነስቷል።

የደቡብ አፍሪካ የቱሪዝም ሚኒስትር ፓትሪሽያ ዴ ሊሌ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ትሬቨር ደቡብ አፍሪካን የሚያስተዋውቅ የአምስት ደቂቃ ቪድዮ ላይ እንዲገኝ ገንዘብ ለመክፈል መታቀዱን አሳውቀዋል።

ብዙ የሕዝብ እንደራሴዎች ዕቅዱን ተቃውመዋል። ለትሬቨር የሕዝብ ገንዘብ እንዴት ይከፈለዋል ሲሉም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ በበኩላቸው ገንዘቡ የሚከፈለው ከሕዝብ ሳይሆን ከቱሪዝም ቢሮ የግል የንግድ ካውንስል መሆኑል ገልጸዋል።

ይሄ ተቋም የአገሪቱን የጉዞና ቱሪዝም ባለድርሻዎች የሚወክል ነው።

አንዳንድ ደቡብ አፍሪካውያን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይህ ስምምነት ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል አስተያየት ሰጥተዋል።

ሌሎች ደግሞ ደቡብ አፍሪካውያን በገንዘብ እጥረት እየታገሉ ሳለ እንዲህ ያለ ስምምነት ውስጥ መግባት ተገቢ እንዳልሆነ ተችተዋል።

“መንግሥት ለእርባና ቢስ ነገር ገንዘብ እንዲያባክን አንፈልግም። ማንም ይሁን ማንም እኛ ጉዳያችን አይደለም። አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ናት። መብራት የለም። ሥራ የለም። እና እንዴት ለትሬቨር ኖሀ 33 ሚሊዮን ይሰጠዋል። ትሬቨር ኖሀ ለአገሪቱ ምን አድርጓል” ሲሉ አንድ አስተያየት ሰጭ በማኅበራዊ ሚዲያ ተቃውመዋል።

በሌላ በኩል ዝነኛው የሆሊውድ ኮከብ ትሬቨር ኖሀ ማስታወቂያ ቢሠራ ለደቡብ አፍሪካ ቱሪዝም እንደሚጠቅም ተከራክረዋል።

በያዝነው ዓመት ጥምር የደቡብ አፍሪካ እና ስዊዝ ዜግነት ያላቸው ትሬቨር ኖሀ እና ሮጀር ፌደረር በጋራ ስዊዘርላንድን እንደ ቱሪስት መዳረሻነት ሲያስተዋውቁ ነበር።