ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከሩሲያ ነጻ የወጣችውን ኼርሶን ከተማን ጎበኙ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜሌንስኪ በቅርቡ ከሩሲያ ጦር ነጻ በወጣችው ኼርሶን ከተማ ተገኙ።

ፕሬዝዳንቱ በከተማዋ ለተሰበሰቡ የዩክሬን ወታደሮች “ወደፊት መገስገሳችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ በንግግራቸው ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የሩሲያ ጦር በዩክሬን ላይ ወረራ በተከፈተ በጥቂት ቀናት ልዩነት ነበር ኼርሶን ከተማን በቁጥጥሩ ስር ያዋላት።

አሁን ላይ ሩሲያ ከተማዋን ለቃ መውጣቷ ለኪዬቭ ድል፤ ለሞሰኮ ደግሞ ሽንፈት ተደርጎ ተወስዷል።

ከመጋቢት 2014 ወዲህ የዩክሬን ጦር አባላት ኼርሶን ከተማ ሲገቡ ዩክሬናውያን ደስታቸውን በአደባባይ ሲገልጹ ታይተዋል።

ዜሌንስኪ ለወታደሮቻቸው ንግግር ሲያደርጉ ዩክሬን “ለሰላም ዝግጁ ናት” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የዩክሬን ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ ለነበሩ ወታደሮቻቸው “ሰላም ለመላው አገራችን” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ዜሌንስኪ ከሩሲያ ጋር ለገቡት ጦርነት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ድጋፍን አመስግነዋል።

ዜሌንስኪ አሜሪካ ለጦራቸው ያቀረበችው በቀላሉ መንቀሳቀስ የሚችለው መድፍ [ሃይ ሞቢሊቲ አርቲለሪ ሮኬት ሲስተም፣ ሂምራስ] ከሩሲያ ጋር ለነበረው ጦርነት ልዩነት ፈጣሪ ሆኗል ብለዋል።

ኼርሶን ነጻ በመውጣቷ እንደ የዩክሬን ሕዝብ ሁሉ እኔም እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

የዩክሬን ጦር ቀጣይ ግስጋሴው ወዴት እንደሆነ የተጠየቁት ዜሌንስኪ፤ “ሞስኮ አይደለም . . . በሌላ አገር ግዛት ላይ ፍላጎት የለንም” ብለዋል።

ዜሌንስኪ ቀደም ሲል የዩክሬን መርማሪዎች የሩሲያ ወታደሮች ሸሽተው በወጡባቸው ቦታዎች የፈጸሟቸውን ከ400 በላይ የጦር ወንጀሎችን አግኝተዋል ብለው ነበር።

ቢቢሲ በሩሲያ ወታደሮች ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎችን ማረጋገጥ አልቻለም። ሩሲያም ወታደሮቼ ሆነ ብለው ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አያደርጉም ትላለች።