ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሪፐብሊካኖች ‘በሚድ ተርም’ ምርጫ ውጤት ለማጣታቸው ትራምፕን ተጠያቂ አደረጉ
‘በሚድ ተርም’ (ከአጋማሽ ዘመን) ምርጫ በኋላ ዴሞክራቶች የአሜሪካ ሴኔት መቆጣጠራቸው በሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ ሽኩቻን ቀስቅሷል።
አንዳንድ ሪፓብሊካን ውጤት ለማጣታቸው ዶናልድ ትራምፕን ተጠያቂ አድርገዋል።
ሌሎች የፓርቲው አባላት ደግሞ በአጋማሽ ምርጫው ውጤት ያጣነው በሴኔት የፓርቲው መሪ ሚች ማክኮኔን ምክንያት ነው ይላሉ።
ዋይት ሃውስ በበኩሉ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ዳግም ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ጠንከር ያለ ፍንጭ ሰጥቷል።
የአሜሪካ የሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት ፉክክር ገና አልተቋጨም። ይሁን እንጂ ሪፐብሊካኖች አሁንም የፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ዕቅዶች በእጅጉ የሚያደናቅፈውን የታችኛውን የኮንግረስ ምክር ቤት እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል። ድምጾች ተቆጥረው ባይጠናቀቁም የዴሞክራቶች የበላይነት እየቀነሰ ነው።
'ውጤት ያሳጣን ትራምፕ ነው'
የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ዴሞክራቶች በአሪዞና እና በኔቫዳ ሁለት የሴኔት መቀመጫዎችን በመያዝ የላይኛውን ምክር ቤት ተቆጣጥረው እንደሚቀጥሉ ትንበያ ሰጥተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በመተችት የሚታወቁት ሪፐብሊካኑ የሜሪላንድ ገዥ ላሪ ሆጋን ለሲኤንኤን ሲናገሩ ሪፓብሊካን ፓርቲ በሴኔቱ ውጤት ያጣው በትራምፕ ምክንያት ነው ብለዋል።
"ትራምፕ ውጤቱን ሲያስከፍለን ይህ በተከታታይ ለሦስተኛ ምርጫ ነው። እሱ ማሸነፍ ሰልችቶናል ብሏል:: እኔ ደግሞ መሸነፍ ሰልችቶኛል::"
ትክክለኛው ፈተና ግን በቀጣዮቹ ቀናት እና ሳምንታት የትራምፕ አጋሮች ፊታቸውን ያዞሩባቸዋል ወይ የሚለው ነው።
ታሪክ እንደሚያመለክተው ዋይት ሃውስን የሚቆጣጠረው ፓርቲ አብዛኛውን ጊዜ ‘በሚድ ተርም’ ምርጫ ወንበሮችን እንደሚያጣ ነው። የዴሞክራቶች የዘንድሮ አፈጻጸም ደግሞ ከ20 ዓመታት ወዲህ ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ያስመዘገበው የተሻለ ውጤት ነው።
“ዋሽንግተን ያሉ ተንታኞች እንደሚሉት ማሸነፍ አንችልም። ምክንያቱስ ሲባሉ ታሪክ፣ ታሪክ፣ ታሪክ ይላሉ” ሲሉ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ለኤቢሲ ተናግረዋል።
ፔሎሲ እሑድ ዕለት ፕሬዝዳንት ባይደን እአአ በ2024 በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት እንዲወዳደሩ ከደገፉ ጥቂት የፓርቲው ባለስልጣናት መካከል አንዷ ናቸው።
የዋይት ሃውስ ከፍተኛ አማካሪ አኒታ ደን ለሲቢኤስ ዜና እንደተናገሩት ፕሬዚዳንቱ “ሌላኛው ወገን በሚያደርገው ወይም ሌላው ዕጩ በሚያደርገው ነገር” የማይወሰኑ ሲሆን ውሳኔያቸውንም በቅርቡ ያሳውቃሉ።
የሚድ ተርም ውጤቶቹ ለፓርቲው አጀንዳ “በጣም ጠቃሚ” ናቸው ያሉ ሲሆን ባይደን “የተጀመረውን ሥራ ለማስቀጠል ምርጡ ሰው” እንደሆኑም ያምናሉ ብለዋል።
ባይደን በድጋሜ የሚፎካከሩ ከሆነ በመጪው ማክሰኞ ለ 2024 ፕሬዝዳንትነት ዕጩ ስለመሆናቸው በይፋ እንደሚያሳውቁ በሰፊው ከሚጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እንደገና ሊወዳደሩ ይችላሉ።