ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፊፋ ብዙ ጸያፍ ስድቦችን በማኅበራዊ ሚዲያ ያስተናገዱ ሁለት ተጫዋቾችን ይፋ አደረገ
የዓለም እግር ኳስን የሚያስተዳድረው አካል ፊፋ ከፍተኛ ዘለፋን እንዲሁም ጸያፍ ስድብን በማኅበራዊ ሚዲያ ያስተናገዱ ተጫዋቾችን ለየ።
ፊፋ ይህን የለየው ከተጨዋቾች ኅብረት ‘ፊፍፕሮ’ ጋር በጥምረት በሠራው አንድ ጥናት ነው፡፡
ጥናቱ ግብ ያደረገው እግር ኳስ ተጨዋቾች ላይ ከፍተኛ ዘለፋን እና መረን የለቀቁ ስድቦችን የሚያደርሱ የማኅበራዊ ትስስር መልዕክቶችን በመከታተል ላይ ነበር።
በዚህም ጥናቱ 400 ሺህ በማኅበራዊ ትስስር መድረክ የተለጠፉ መልዕክቶችን በናሙናነት ወስዷል።
ናሙናዎቹ የተወሰዱት በ2020 የአውሮፓ ዋንጫ እና የአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ላይ በተሰነዘሩ የማኅበራዊ ሚዲያ መስተጋብሮች ነበር።
የጥናቱ ውጤት እንዳመላከተው ከጠቅላላ በውድድሩ ከተሰለፉ ተጫዋቾች 50 ከመቶ የሚሆኑት ይነስም ይብዛ አንዳች ዘለፋና ስድብ ተሰንዝሮባቸዋል።
ይህ ጥናት ሌላ ደረስኩበት ያለው ለከፍተኛ ዘለፋ ከሚጋለጡት ሁሉ የከፋ ዘለፋ የሚደርስባቸው ጥቁር ተጫዋቾች እና ፍጹም ቅጣት ምት የሳቱ ተጨዋቾች መሆናቸው ነው።
ቢቢሲ ስፖርት ጥናቱን መሠረት አድርጎ በሠራው ትንታኔ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች፣ ማርከስ ራሽፎርድ እና ቡካዮ ሳካ አገራቸው በፈረንጆቹ 2020 በአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ በጣሊያን ስትረታ ፍጹም ቅጣት ምት የሳቱ ተጫዋቾች መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛውን የማኅበራዊ ሚዲያ ዘለፋ ያስተናገዱ ተጨዋቾች እንደሆኑ ደርሶበታል።
የጥናቱን ውጤት ይፋ መሆን ተከትሎ የፊፋው ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ “ዓላማችን በእግር ኳስ ትልቅ ፈንጠዚያን የሚያመጡልንን ውድ ተጨዋቾች ከተራ ዘለፋና ከቆሻሻ የማኅበራዊ ሚዲያ ጥቃት መከላከል ነው” ብለዋል።
ይህ ጥናት በደረሰበት ድምዳሜ መሠረት በሁለቱ የዋንጫ ውድድሮች ዛቻና ዘለፋን በማኅበራዊ ሚዲያ ያደረሱት በዋናነት ከባለጋራ ቡድን ደጋፊዎች ይልቅ የተጫዋቾቹ የገዛ አገር ዜጎች መሆናቸው ነው።
ከዘለፋዎቹና ጸያፍ ስድቦች ውስጥ 40 ከመቶ ድርሻን የያዙት የተመሳሳይ ጾታ ምርጫ ላይ ያነጣጠሩ ሲሆን፣ 38 ከመቶ ደግሞ ቆዳ ቀለም ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ።
ይህን ጥናት መሠረት በማድረግ ፊፋ እና ፊፍፕሮ ከዚህ ወዲህ ውድድሮች ሲካሄዱ ግጥሚያዎቹ ላይ ትኩረት ያደረጉ ጸያፍ ስድቦችን የሚለዩ የክትትል ሥራዎችን ለማድረግ አቅደዋል።
ይህም ጸያፍ ስድቦች በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች በተጻፉበት ቅጽበት ሌሎች በርካታ ሰዎች ሳይመለከቷቸው ወዲያውኑ ከገጽ እንዲጠፉ የሚያደርግ ሙከራ ይሆናል።