ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብፅ ከአስደንጋጩ የኢትዮጵያ ሽንፈቷ በኋላ አሰልጣኟን አሰናበተች
የግብፅ እግር ኳስ ማኅበር የብሔራዊ ቡድኑን አሰልጣኝ ኤሃብ ጋላልን ፊርማቸው ሳይደርቅ ከኃፊነት አነሳ።
ጋላል ብሔራዊ ቡድኑን ለሦስት ጨዋታዎች ብቻ ነው የመሩት።
የ54 ዓመቱ ጋላል ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ነበር ካርሎስ ኬሮዥን በመተካት ኃላፊነቱ የተሰጣቸው።
ኬሮዥ ብሔራዊ ቡድኑን ለዓለም ዋንጫ ባለማብቃተቸው ነበር ከኃላፊነት የተነሱት።
ጋላል በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በኢትዮጵያ 2 ለ 0 ተሸንፈዋል።
ከዚህ አስደንጋጭ ውጤት በተጨማሪ ቡድኑ በወዳጅነት ጨዋታ በደቡብ ኮሪያ 4 ለ 1 ተሸንፏል።
የማኅበሩ ቦርድ አባል የሆኑት ሃዜም ኤማም የውጭ አገር አሰልጣኝ እንደሚሾሙ አስታውቀዋል።
ጋላል በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ዛማሌክ፣ ኤል ማስሪ እና አልአህሊ ትሪፖሊን የመሳሰሉ ቡድኖችን አሰልጥነዋል።
ብሔራዊ ቡድኑን ከመረከባቸው በፊት የፒራሚድስ አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል።
ብሔራዊ ቡድኑን በያዙ መጀመሪያ ጨዋታቸው በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጊኒን ባለቀ ሰዓት ባስቆጠሩት ጎል 1 ለ 0 አሸንፈዋል።
በቀጣይ ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎች ባለማሸነፋቸው ሥራቸውን አሳጥቷቸዋል።
“ከበርካታ የውጭ አገር አሰልጣኞች ጋር እየተነጋገርን ነው” ያሉት ኤማም ቴክኒካል ዳይሬክተር እንደሚሾሙም ጠቁመዋል።
“ለተከበረው አሰልረጣኝ ኤሃብ ጋላል ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ሥራውን በከባድ ሁኔታ ውስጥ ሲያከናውን ነበር። ይቅርታ ልጠይቀው እወዳለሁ። አንዳንዴ ግፊቱ ከባድ ነው። ለውጡ ለሁሉም ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።
ከጋላል በፊት የግብፅ አሰልጣኝ የነበሩት ኬሮዥ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን የአሰልጣኝት ዘመን በማንቸስተር ዩናይትድ ምክትል ሆነው የሰሩ ሲሆን፣ በተጨማሪም በዋና አሰልጣኝነት ፖርቹጋል እና ኢራንን መርተዋል።
ኬሮዥ የሰባት ጊዜ የአህጉሪቱ እግር ኳስ ሻምፒዮኗን ግብፅ ለአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ቢያደርሱም በመለያ ምት በሴኔጋል ተሸንፈዋል።
ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ በተደረገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ግብፅ በተመሳሳይ በሴኔጋል በመለያ ምት ተሸንፋ ከኳታሩ ውድድር ውጪ ሆናለች።