የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር ይችሉ እንደሆነ ብይን ሊሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዶናልድ ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር ይችሉ እንደሆነ ብይን ሊሰጥ ነው።
ትራምፕ በኮሎራዶ ግዛት በቀጣዩ ምርጫ እንዳይሳተፉ የተላለፈውን ውሳኔ ተቃውመው ይግባኝ ያሉ ሲሆን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ውሳኔ ያሳልፋል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በመላው አሜሪካ የሚተገበር ይሆናል።
በተለያዩ ግዛቶች ትራምፕ እንዳይወዳደሩ የሚጠይቁ አቤቱታዎች ለፍርድ ቤቶች ቀርበዋል።
ትራምፕ ከሦስት ዓመት በፊት በካፒቶል ሂል ከተነሳው ሁከት ጋር በተያያዘ ለመንግሥት ግልበጣ አሲረዋል በሚል ነው ለግዛቶች ፍርድ ቤቶች ቅሬታ የቀረበው።
ለፕሬዝዳንትነት እንዳይወዳደሩ በተጠየቀባቸው ሁኔታዎች የተጠቀሰው የሕገ መንግሥተ አንቀጽ በአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ማሻሻያ የተደረገበት ነው።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የትራምፕን አቤቱታ ለመስማት የወሰነው የ27 ግዛቶች ዐቃቤ ሕጎች የኮሎራዶን የዕግድ ውሳኔ ፍርድ ቤት ውድቅ እንዲያደርግ ከወሰኑ በኋላ ነው።
“ትራምፕን ከምርጫው ማገድ ቀውስ ያስከትላል። ጥቂት ጊዜ በቀሩት ምርጫ ውዝግብ ያስነሳል” የሚል ቅሬታ ቀርቧል።
በተጨማሪም የኮንግረስ፣ የግዛቶችና ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ የሚያጣጥል ነው ተብሏል።
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት 14ኛው አንቀስ ማሻሻያ ማንኛውም አመጽና የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ያደረገን ሰው የፌደራል ሥልጣን ከመያዝ ያግዳል።
የትራምፕ ጠበቆች ይህ አንቀጽ ለፕሬዝዳንቶች አይሠራም ብለው ተከራክረዋል።
“የኮሎራዶ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚሊዮኖች መራጮችን መብት የሚጥስ ነው” ሲሉ ጠበቆቹ ተከራክረዋል።
ኮሎራዶን ተከትሎ የዕግድ ውሳኔ በሜይን ግዛትም ዕግድ ተላልፎባቸው ትራምፕ ይግባኝ አስገብተዋል።
በኮሎራዶ ግዛት የመጀመሪያ ዙር የፕሬዝዳንት እጩ ድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የትራምፕ ስም እንዳለ ተገልጿል።
ይሄ የመጀመሪያ ዙር ድምጽ መስጫ ሲሆን ማን ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደር ይጠቁማል።
የኮሎራዶን ውሳኔ ተከትሎ በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአንድ እጩ የመወዳደር ጉዳይ ሲታይ ይህ የመጀመሪያው ይሆናል።
ሚኒሶታ እና ሚችገን ግዛቶች ትራምፕን ከምርጫው ለማስወገድ የቀረበ ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።
በኦሪገን ደግሞ ጥያቄው ገና ውሳኔ አልተሰጠውም።
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ወግ አጥባቂዎች ናቸው። ሦስቱ ዳኞች የተሾሙት በትራምፕ ነው።
ሆኖም ግን እአአ በ2020 ጆ ባይደን በምርጫው አላሸነፉም ብለው ትራምፕ ሲከራከሩ ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕ ጠበቆችና ከምርጫው እንዲታገዱ የሚከራከሩ አካላት ጉዳያቸውን ያቀርባሉ።
የሪችመንድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ካረት ቶቢያስ እንደሚሉት፣ ይህ ጉዳይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የደረሰው በተለያዩ ግዛቶች እየቀረቡ ባሉ ክሶች መብዛት ነው።
በዚህ ፍርድ ቤት ጉዳዮች ሲቀርቡ ብይን ለማግኘት እስከ 12 ወራት ይወስድባቸዋል። ይሄኛው ጉዳይ ግን በጥቂት ሳምንታት ነው ውሳኔ የሚሰጥበት ተብሏል።
በካፒቶል ሂል ሁከት ላይ ትራምፕ ኮንግረስ ገብተው ባይደንን አሸናፊ ያደረገውን ምርጫ ለመቀልበስ ሞክረዋል።
ደጋፊዎቻቸውንም “በደንብ ታገሉ” ብለዋል።
የትራምፕ ተቃዋሚዎች በዚህ ምክንያት ከቀጣዩ ምርጫ እንዲታገዱ ይጠይቃሉ።
ሆኖም ግን ትራምፕ በፌደራል ፍርድ ቤትና በጆርጅያ ግዛት የምርጫውን ውጤት ለመለወጥ በመሞከር የቀረቡባቸው ክሶች እስካሁን በወንጀል ተጠያቂ አላደረጓቸውም።












