ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና መስጊዶችን እየዘጋችና እያፈረሰች ነው ሲል ሂውማን ራይትስ ዋች ከሰሰ
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች ቻይና “በስልታዊ መንገድ” የእስልምና ተግባርን ለመግታት እየሰራች ነው አለ።
በቻይና ከ20 ሚሊዮን በላይ ሙስሊሞች ይገኛሉ። “ሃይማኖት አልባ” የሆነው የቻይና መንግሥት የሃይማኖት ነጻነት እፈቅዳለሁ ይላል።
ሆኖም ጉዳዩን የሚከታተሉ ይህ እውነት አይደለም ይላሉ።በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቻይና መንግሥት የተደራጀ የሃይማኖት እንቅስቃሴን ለመግታት የሚያደርገው ጥረት መጠናከሩን እና ሃይማኖቶቹን በጥብቅ ቁጥጥር ሥር ለመያዝ እንደሚሞክርም ያስረዳሉ።
ሂውማን ራይትስ ዋች የቻይና መንግሥት ሃይማኖት ላይ ይወስዳል ያለውን እርምጃ ይፋ ከማድረጉ አስቀድሞ ሪፖርቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርን እና የሥነ ምግባር ጉዳዮች ኮሚሽንን ቢቢሲ ጠይቆ ነበር፥
የሂውማን ራይትስ ዋች የቻይና ዳይሬክተር ተወካይ የሆኑት ማያ ዋንጋ “መስጊዶችን መዝጋት፣ ማፍረስና ለሌላ ዓላማ ማዋል የቻይና መንግሥት የእስልምና እምነትን ለመግታት የሚያደርገው ስልታዊ ጥረት አካል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ሪፖርቱ በቻይና ሰሜናዊ ዢንጃንግ ክልል በኡጋሀር ሙስሊሞች ላይ ይፈጸማል ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አለኝ ካለው ማስረጃ ጋር አቅርቧል። የቻይና መንግሥት ግን ይህ ሀሰት ነው ሲል አስተባብሏል።
በቻይና የሚገኙ አብዛኞቹ ሙስሊሞች በአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል ይኖራሉ።
ሪፖርቱ ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበትና ራስ ገዝ በሆነችው ሊያዋኪዎ አካባቢ ከ6 መስጊዶች ሦስቱ ሚናራቸው (መስጊዶች ላይ የሚገነባው ከፍ ብሎ የሚታየው ክፍል) እና የመስጊዶች መገለጫ የሆነው ክብ ጣሪያ እንዲነሳ ተደርጓል ብሏል።
የተቀሩት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ሲልም አክሏል።
ሂውማን ራይትስ ዋች ይፋ ባደረገው የሳተላይት ምስል ከአውሮፓውያኑ 2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ሙስሊሞች በሚበዙበት አንድ አካባቢ ያለ አንድ መስጊድ ክቡ ጣሪያ በቻይና ባህላዊ የጣሪያ አሰራር እንዲቀየር መደረጉን አመላክቷል።
ኒዥያ በምትባል አንድ የቻይና ግዛት 1 ሺህ 300 መስጊዶች እንደተዘጉ ወይም ለሌላ ዓላማ እንደዋሉ በቻይና ሙስሊሞች ላይ ጥናት የሚያደርጉት ሃናሃ ቲሂከር ለቢቢሲ ገልጸዋል። ይህ የመስጊድ ቁጥር በግዛቱ ካሉት ጠቅላላ መስጊዶች አንድ ሦስተኛውን የሚሸፍን ነው።
አሁን በሥልጣን ላይ ባሉት የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ ዘመን ኮሚኒስት ፓርቲው ሃይማኖት ከፖለቲካዊው ርዕዮተ ዓለምና ከቻይና ባህል ጋር እንዲጣጣም ይፈልጋል።
በአውሮፓውያኑ 2018 የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ባወጣው አንድ ሰነድ መስጊዶች በጥብቅ ቁጥጥር ሥር ሊታዩ እንደሚገባ ጠቁሟል።
ሰነዱ መንግሥት በርካታ መስጊዶችን እያፈረሰ ጥቂት እንዲገነባ እንዲሁም መሰል ግንባታዎች በጥቅሉ በቁጥር እንዲያንሱ ያሳስባል።
ጨምሮም የመስጊዶች ገጽታና የገንዘብ ምንጭ “በጥብቅ ክትትል” ውስጥ መሆን እንደሚገባውም ያትታል።
ይህ እርምጃ እስልምና በሚበዛባቸው አካባቢዎች ተጠናክሮ ይታይ እንጂ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየተስፋፋ ነው።
በቻይና ሁለት የሙስሊም ሃይማኖት የሚከተሉ ዋና ዋና የዘር ሀረጎች አሉ። የመጀመሪያው ሁይስ የተሰኘው ሲሆን በ8ተኛው ክፍለ ዘመን በታንግ ስረው መንግሥት ቻይና የገቡ ናቸው።
ሁለተኛው ደግሞ ኡይጋርስ ሲሆን በአብዛኞቹ የሚኖሩት በዢንጃንግ ነው። በዢንጃንግ ሁለት ሦስተኛው የሚሆነው መስጊድ ከአውሮፓውያኑ 2017 ወዲህ መፍረሱን የአውስትራሊያ የፖሊስ ጥናት ተቋም ገልጿል።
አንዳንድ ነዋሪዎች ይህንን እንቅቃሴ ቢቃወሙም ጥረታቸው መስጊዶችን ከመፍረስ እንዳላዳነ ተነግሯል።