የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በግለሰቦች ስም በከፈተው የባንክ ሂሳብ የቅጣት ገንዘብ መሰብሰቡን ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ

የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት “ሥልጣን ሳይኖረው” የቅጣት የክፍያ ተመን መመሪያ በማውጣት፤ በግለሰቦች ስም በተከፈተ የባንክ ሂሳብ 17.9 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

ተቋሙ ከነሐሴ 2015 ዓ.ም እስከ ጥር 2016 ዓ.ም. ከሰበሰበው 17.9 ሚሊዮን ብር ውስጥ 9.3 ሚሊዮን ብር “ለትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ለበዓል ለሠራተኞች ስጦታ” ወጪ መደረጉን ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል።

የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ይህን ይፋ ያደረገው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት የፋይናንስ እና ሕጋዊነት ኦዲተር እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ነው።

ቢቢሲ የተመለከተው ይህ ባለ 61 ገጽ ሪፖርት የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ሂሳብ ላይ የተከናወኑ የፋይናንስ እና ሕጋዊነት ኦዲት፣ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቶችን የያዘ ነው።

ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አሰጣጥ ውጤታማነትን የተመለከተ ሪፖርትን በኦዲት ሰነዱ ውስጥ አካትቷል።

“ተቋሙ ለፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ የሚያገለግሉ የጸደቀ እና ወቅታዊ የሆነ መመሪያ፣ ስታንዳርድ እና የዜጎች ቻርተር የሌለው” በሚል በኦዲት ሪፖርቱ ትችት ቀርቦበታል።

የኢምግሬሽን ተቋሙ ገንዘብ ለመሰብሰብ መመሪያ የማውጣት ሥልጣን ሳይኖረው “የፓስፖርት ምዝገባ ቀን ቀጠሮ ያሳለፉ ግለሰቦችን በቅጣት ለማስተናገድ (የቅጣት ክፍያ ተመን) መመሪያ አዘጋጅቶ በዋና ዳይሬክተር ያጸደቀ መሆኑን” ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ይህ መምሪያ ከጸደቀ አምስት ቀናት በኋላ “የመንግሥት የባንክ ሂሳብ የመክፈት እና የመዝጋት የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሥልጣን ሆኖ ሳለ” ተቋሙ ነሐሴ 26/2015 ዓ.ም. በግለሰቦች ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ መክፈቱን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አክሏል።

የባንክ ሂሳቡ ከተከፈተ ጀምሮ እስከ ጥር 20/2016 ዓ.ም. ባሉት አምስት ወራት 17.9 ሚሊዮን ብር ወደ አካውንቱ ገቢ መደረጉን ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ 51.9 በመቶ ያህሉ “ለትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ለበዓል ሠራተኛው ስጦታ” ወጪ መደረጉን የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች በቃል መናገራቸውን ሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።

የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ይህን መመሪያ በማውጣት የተጠቀሰውን ገንዘብ የሰብሰበው ሰላማዊት ዳዊት በዋና ዳይሬክተር ተቋሙን የመምራት ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብልጽግናን ፓርቲን ወክለው የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑትን ሰላማዊ ዳዊት በዋና ዳይሬክተርነት የሾሙት ሐምሌ 26/2015 ዓ.ም. ነበር።

ሰላማዊት ዳዊት የሚመሩት የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ያለ ሥልጣኑ መመሪያ አውጥቶ ገንዘብ ከመሰብሰብ በተጨማሪ በሌሎች ጉዳዮችም ተተችቷል።

በኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት መሠረት፤ “ተቋሙ ከድንበር እና ከጎረቤት አገራት መሆናቸው አጠራጣሪ የሆኑ ተገልጋዮች ሲያጋጥሙ ዜግነታቸው የሚጣራበት መመሪያ የለውም።”

ዜግነት የማጣራት ሥራው በልምድ የሚከናወን መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ “ውሳኔው ዜግነትን በሚያጣራው ግለሰብ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ እና ወጥ የሆነ አሠራር የማይከተል” መሆኑን አስታውቋል።

“የተቋሙ ሠራተኞች ከበር ጥበቃ ጀምሮ አስተባባሪዎች እና አገልግሎት የሚሰጡ ኦፊሰሮች ተገልጋዩን የማመናጨቅ፣ አልባሌ ቃላት የመጠቀም አልፎም የመጎተት፣ የመገፍተር እና የመማታት ሁኔታዎች መኖራቸውን” ማረጋገጡን የኦዲተር መሥሪያ ቤት በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።

ከአዲስ ፓስፖርት እና ከእድሳት ጋር በተገናኘ ተገልጋዮች “አገልግሎቱን በምን ያህል ጊዜ እንደሚያገኙ የተቀመጠ መመሪያ እና የጊዜ ሰሌዳ የሌለው መሆኑ” በኦዲት ሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪ “[ተቋሙ] ፓስፖርት በቀነ ቀጠሮ የማይሰጥ፤ በቀጠሮ ያልደረሰላቸው ተገልጋዮች ማንን መጠየቅ እንዳለባቸው የሚገለጽበት አሠራር አለመኖሩ እና አገልግሎቱን በወቅቱ ማግኘታቸውን የማይከታተል መሆኑን” የኦዲተር ሪፖርቱ ያሳያል።