ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እግር ኳስ ተጫዋቾች ሲያጠፉ ‘ለ10 ደቂቃ የሚገለሉበት’ ሕግ ተግባራዊ ሊሆን ነው
ተጫዋቾች መካከለኛ ጥፋት ሲያጠፉ ለ10 ደቂቃ ከሜዳ እንዲወገዱ የሚያስገድድ ሕግ በፕሮፌሽናል ጨዋታዎች ተግባራዊ ሊሆን ነው።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ሕግ አውጭ ቦርድ [ኢፋብ] የትኞቹ ውድድሮች “ለሕጉ እንደሚመጥኑ” ይፋ አደርጋለሁ ብሏል።
ለሙከራ የታጨው አዲሱ ሕግ፤ ዳኛን ቀርቦ ማናገር የሚችለው አምበል ብቻ ነው የሚል አንቀፅም አዝሏል።
በእንግሊዝኛው ‘ሲን-ቢን’ የሚል መጠሪያ ያለው ሕግ ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ በታዳጊዎች ውድድር ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል።
ዓለም አቀፉ ቦርድ ማክሰኞ ዕለት ለንደን ውስጥ ስብሰባ ሲያደርግ ነው ሕጉ ለመኩራ እንዲቀርብ ሐሳብ የቀረበው።
አዲሱ ሕግ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2024 በሚደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የሙከራው ውጤት ታይቶ ሊፀድቅ ይችላል።
የፊፋ ዳኞች ኮሚቴ ሊቀ-መንበር የሆኑት ጣሊያናዊው የቀድሞው አርቢትር ፒየርሉዊጂ ኮሊና የዚህ ቦርድ ቴክኒካል ኮሚቴ አባል ናቸው።
“ሙከራው ፕሮፌሽናል ውድድሮችን ሊያሳትፍ የመቻል ዕድሉ ሰፊ ነው” ይላሉ ኮሊና።
የኢፋብ ፀሐፊ ሉካስ ብሩድ ደግሞ ቀጣዩ እርምጃ ሙከራው በየትኞቹ ውድድሮች ላይ ይደረግ የሚለውን መለየት ይሆናል ብለዋል።
ለቢቢሲ ስፖርት ሐሳባቸውን የሰጡት ፀሐፊው “ስብሰባው ‘አዎንታዊ’ ነው” ይላሉ።
“በሚቀጥሉት ሳምንታት እና ወራት በየትኞቹ ውድድሮች እንጀምር የሚለውን እናጣራለን። የውድድሩ አዘጋጆች ይሁንታ ይወስነዋል። ሙከራውን ማድረግ ይፈልጋሉ፤ አይፈልጉም የሚለውን ራሳቸው ናቸው የሚወስኑት።”
“ሲን-ቢን”
በአውሮፓውያኑ 2018-19 የእንግሊዝ እግር ኳስ ማሕበር ‘ሲን-ቢን’ የተባለው ሕግ ሞክሮ ሜዳ ላይ የሚታዩ አላስፈላጊ ባሕርያት 38 በመቶ ቀንሰዋል ይላል።
ማሕበሩ ሙከራውን ያደረገው በ31 የሊግ ውድድሮች ላይ ነበር።
በ2019-20 የውድድር ዘመን ደግሞ በሁሉም ታዳጊ እግር ኳስ ውድድሮች ላይ ሙከራ አድርጎ ፍትሐዊነት ለጨዋታ የሚሰጥ ክብር ከፍ ብሏል ይላል።
የእንግሊዝ እግር ኳስ ማሕበር ሙከራውን ቀጥሎ በብሔራዊ ሊግና በሴቶች ውድድሮች ላይ ተግባራዊ አድርጎታል።
የሕግ አውጭው ቦርድ አባል የሆኑት የማሕበሩ ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ባሊንግሐም ለፀባይ ብቻ ሳይሆን ለታክቲካል ጥፋትም ‘ሲን-ቢን’ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የቀድሞው የቼልሲ እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ጆን ቴሪ በአዲሱ ሕግ እንደማይስማማ በኤክስ ገፁ ገልጧል።
የሲን-ቢን ሐሳብ ያልተመቸው ቴሪ “ይህ ማለት ዳኞች ያላቸው ትዕግስትና ተመሳሳይ ውሳኔ የመወሰን አቅም ከሳምንት ሳምንት የተለያየ ይሆናል ማለት ነው” ይላል።
የቀድሞው የሊቨርፑልና የእንግሊዝ ተከላካይ ጄሚ ካራገር ደግሞ የሲን-ቢን ሐሳብ አድናቂ ባይሆንም አላስፈላጊ ቀይ ካርዶች በመብዛታቸው አዲሱ ሕግ መፍትሔ ሊሆን ይችላል ይላል።
የራሽፈርድና የከርቲስ ጆንስን ክስተት የሚያወሳው ካራገር “አንዳንድ ጊዜ ተጫዋቾች የሚፈፅሙት ጥፋት ከቢጫ ያለፈ ነገር ግን ቀይ የማይገባው ሲሆን አይተናል” ሲል ፅፏል።
የቪኤአር ነገር
ኢፋብ ስብሰባውን ሲያደርግ አወዛጋቢውን የቪድዮ ረዳት ዳኛ [ቪኤአር] ጉዳይንም አንስቶ ውይይት አድርጓል።
ቦርዱ ቪኤአርን በተመለከተ የሚቀርቡ አዳዲስ ሐሳቦች “ጨዋታው የበለጠ እንዲጓተት የሚያደርጉ መሆን በፍፁም የለባቸውም” በሚለው ተስማምቷል።
ሰሚ-አውቶሜትድ በመባል የሚታወቀው ቴክኖሎጂ ሜዳ ውስጥ የሚገኙ ዳኞችን ለማገዝ ጥቅም ላይ መዋሉን እንደሚቀጥል ቦርዱ ገልጧል።
ፊፋ በ2022 የካታር ዓለም ዋንጫ እጅግ ዘመናዊና የበለጠገ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ከጨዋታ ውጭ የሆኑ ውሳኔዎችን መስጠቱ ይታወሳል።
ባለፈው ሐምሌ በተካሄደው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ላይ ደግሞ ዳኞች ቪኤኤር ከተመለከቱ በኋላ ውሳኔያቸውን በማይክ ለተመልካቹ ይፋ ሲያደርጉ ነበር።
ዳኞች ውሳኔያቸውን ሜዳ ውስጥ እንዲሁም በቴሌቪዥን ለሚከታተል ተመልካች ይፋ ያደረጉበት ትልቁ ውድድርም ሆኗል።
ባለፈው መስከረም የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ዳኛው ሳይመን ሁፐር እና የቪኤአር ዳኛው ዳረን ኢንግላንድ ሳይግባቡ በመቅረታቸው ሉዊስ ዲያዝ ለሊቨርፑል ያስቆጠረው ጎል መሰረዙ ይታወሳል።
ሕግ አውጭው ቦርድ ዳኞች ውሳኔ ሲወስኑ ማይክ ተጠቅመው ለሕዝቡ ይፋ ማድረግ አለባቸው የሚል ሕግ በሁሉም ውድድሮች ይፋ እንዲሆን ይፈልጋል።