የአሜሪካ የክትባት ኮሚቴ የኮቪድ-19 ክትባት ለአዋቂዎች እንዲሰጥ ላለማበረታታት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዋነኛው የአሜሪካ የክትባት አማካሪ ኮሚቴ፤ ከዚህ ቀደም ሁሉም አዋቂ አሜሪካዊ በዓመት አንድ ጊዜ የኮቪድ-19 ክትባትን መውሰድ አለበት በሚል የሰጠውን ምክረ ሃሳብ ተግባራዊነት ለማስቆም ድምጽ ሰጠ።
"ዘ አድቫይዘሪ ኮሚቴ ኦን ኢሚዩናይዜሽን ፕራክቲስስ" የተባለው ይህ አማካሪ ቡድን የኮቪድ ክትባት እንዲሰጥ በሚል ይዞት የነበረውን አቋሙን የቀየረው በጠባብ የድምፅ ልዩነት ነው።
ኮሚቴው ለሁለት ቀናት ካደረገው ስብሰባ በኋላ ከዚህ ቀደም "ኤምኤምአርቪ" ተብሎ የሚታወቀውን እና ኩፍኝ፣ ጆሮ ደግፍ፣ የጀርመን ኩፍኝ (rubella) እና ፈንጣጣ በሽታዎችን ለመከላከል የሚውል ክትባትን በተመለከተም ሰጣቸውን ምክረ ሃሳቦችንም ቀይሯል። በሄፒታይተስ ቢ ክትባት ላይ ድምጽ ለመስጠት ይዞት የነበረውን ዕቅድን ደግሞ አዘግይቷል።
ክትባት ላይ ጥርጣሬ ያላቸው የአሜሪካ ጤና ሚኒስትር ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ፤ የዚህን ኮሚቴ 17 አባላት በሙሉ ሰኔ ወር ላይ አባርረው፤ ራሳቸው የመረጧቸውን ሰዎች በአባልነት ተክተዋል። ይህ እርምጃ በሕክምና ማኅበረሰቡ ዘንድ ተቃውሞን አስነስቷል።
ኮሚቴው ባለፉት ዓመታት ልክ እንደ የኢንፍሉዌንዛ ክትባት ሁሉ በየጊዜው እንዲሰጥ ሲመከር በነበረው የኮቪድ-19 ክትባት ላይ አርብ ዕለት ክርክር አካሂዷል።
ከዚህ በኋላ በተከናወነው ድምጽ የመስጠት ሂደት ክትባቱን በተመለከተ ሲቀርብ የነበረው ምክረ ሃሳብ ውድቅ እንዲሆን ተወስኗል።
አሁን ውድቅ የተደረገው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸውን አዛውንቶች ጨምሮ ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ክትባቱን የመስጠት ሃሳብ በብዙዎች ዘንድ ሰፊ ድጋፍ ያለው ነው።
ኮሚቴው ሰዎች ክትባቱን መውሰድን በተመለከተ ከሕክምና ባለሙያ ጋር ከተነጋገሩ የራሳቸውን ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚችሉ ወስኗል።
ሰኔ ወር ላይ አሜሪካ ፌደራል መንግሥት የኮቪድ-19 ክትባት ለጤነኛ ነፍሰ ጡር ሴቶች እና ሕጻናት ምክረ ሃሳብ መስጠት አቁሟል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአርብ ዕለቱ ክርክር ወቅት የጤና ሚኒስትሩ አጋር የሆኑት ዶ/ር ሮበርት ማሎን፤ የኮቪድ ክትባት ከባድ በሽታዎችን ለመከላከል ስለመቻሉ ምንም ማስረጃ እንደሌለ ተሟግተዋል።
የአሜሪካ ምግብ እና መድኃኒት አስተዳዳር የክትባት ኮሚቴ አባል የነበሩት ዶ/ር ኮዲ ሜይስነር በበኩላቸው ክትባቱ በሽታን መከላከል እንደሚችል የሚያሳይ "በጥሩ ሁኔታ የተብራራ" መረጃ መኖሩን በመጥቀስ ተከራክረዋል።
በስብሰባው ወቅት ኩፍኝ፣ ጆሮ ደግፍ፣ የጀርመን ኩፍኝ እና ፈንጣጣ የሚውለውን ኤምኤምአርቪ ክትባት በተመለከተ በኮሚቴው በአባላት ዘንድ ግራ መጋባት ተፈጥሮ ነበር።
ኮሚቴው ሐሙስ ዕለት ዕድሜያቸው አራት እና ከዚያ በታች የሆኑ ሕጻናት ይህንን ክትባት እንዲወስዱ መምከርን በመቃወም ድምጽ ሰጥቶ ነበር።
አርብ ዕለት ደግሞ ሁለት የተለያዩ ክትባቶችን ደግፎ ድምጽ ሰጥቷል። የመጀመሪያው ክትባት ለኩፍኝ፣ ለጆሮ ደግፍ እና ለጀርመን ኩፍኝ የሚውል ሲሆን ሦስተኛው ክትባት ፈንጣጣን ለመከላከል የሚሰጥ ነው።
አሜሪካ ዶክተሮች እና የሕክምና ተማሪዎችን የሚወክለው የሀገሪቱ ሕክምና ማኅበር ለእነዚህ በሽታዎች የተሰጠው አዲስ ምክረ ሃሳብ "ወላጆችን ግራ የሚያጋባ ነው" በማለት ተችቷል።
በተጨማሪም ኮሚቴው፤ በእርግዝና ወቅት በተደረገ ምርመራ ከሄፒታይተስ ቢ በሽታ ነጻ መሆኗ ከተረጋገጠ እናት ለሚወለዱ አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ሕጻናት ወዲያውኑ የሚሰጠውን የጉበት በሽታ ክትባት በተመለከተ ሊያካሂድ የነበረውን ድምጽ የመስጠት ሂደት አዘግይቷል።
ተመራማሪዎች ለሂፒታይተስ ቢ የሚሰጠው ክትባት ደኅንነቱ የተጠበቀ እና በሽታን በመከላከል ረገድ ውጤታማ እንደሆነ ቢናገሩም ኮሚቴው ባለፉት ወራት ጥርጣሬውን ሲገልጽ ቆይቷል።















