ከመፀዳጃ ቤት መቀመጫዎች በሽታ ሊይዘን ይችላል? ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ አለብን?

በሶፍት የተሸፈነ የመፀዳጃ ቤት መቀመጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የመፀዳጃ ቤት መቀመጫን በሶፍት መሸፈን ጀርሞችን አይከላከልም

በአንድ ቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተጠቀሙበት የመፀዳጃ ቤት መቀመጫ ስንጠቀም በሽታ አምጪ ተህዋስያን በመታጠቢያ ቤቶች ለምን ያህል ጊዜ ይቆያሉ? ብላችሁ ልታስቡ ትችላላችሁ።

ለሕዝብ ክፍት በሆኑ መፀዳጃ ቤቶች እግራችሁ ከረገጠ በሚያፀይፍ ስሜት ልትዋጡ ትችላላችሁ። በመፀዳጃ ቤቱ ወለል እና መቀመጫ ላይ የፈሰሰ ሽንት ማየት ስሜትን ሸንቆጥ ሊያደርግ ይችላል።

መፀዳጃ ቤቱን ከእጅ ንክኪ ለማራቅ ልትፍጨረጨሩም ትችላላችሁ። መቀመጫውን በሶፍት ንጣፍ በማዘጋጀት ለመፀዳዳት መሞከር ወይንም ቁጢጥ ማለት ለብዙዎች አዲስ አይደለም።

ለጥቂት ደቂቃዎች አረፍ ያላችሁበት የመፀዳጃ ቤት መቀመጫ በሽታ ሊያስይዘን ይችላል? አሊያም ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ሲፀዳዱ ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚያደርጓቸው ዘዴዎችስ አላስፈላጊ ናቸው?

የዘርፉ ባለሙያዎች ተከታዩን ይላሉ።

ሊያስጨንቀን የሚገባ ነገር ነው?

በደቡብ ፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ የሕብረተሰብ ጤና እና ማይክሮ ባዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ጂል ሮበርትስ "በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ አዎ፤ [ከመፀዳጃ ቤት መቀመጫዎች በበሽታ ልንያዝ ይችላል] ነገር ግን አደጋው በጣም ዝቅተኛ ነው" ይላሉ።

ለአብነት የአባላዘር በሽታዎችን እናንሳ። ጨብጥ እና ሌሎች የአባላዘር በሽታዎችን የሚያሲዙ አብዛኞቹ ባክቴሪያዎች እና ቫይረሶች አይደለም፤ በቅዝቃዜ እና እንደ መፀዳጃ ቤት ባሉ ጠንካራ ወለል ላይ ይቅር እና እስትንፋስ በሌላቸው አካላት ላይ ለረዥም ጊዜ ሊቆዩ አይችሉም።

ለዚህም ነው አብዛኞቹ የአባላዘር በሽታዎች በቀጥታ የብልት ግንኙነት እና በፈሳሽ ልውውጥ ብቻ ይተላለፋሉ ተብሎ የሚታሰበው።

ፕሮፌሰር ሮበርትስ አንድ ሰው የሌላን ሰው ፈሳሽ ወዲያው ከሽንት ቤት መቀመጫው ወደ ብልት በእጅ አሊያም በሶፍት በማስገባት አደጋ ላይ ለመውደቅ ዕድለ ቢስ መሆን አለበት ይላሉ።

ስለዚህ ጥንቃቄ ማድረግ እና የተበከሉ መፀዳጃ ቤቶችን ባለመጠቀም ንፅህናን መጠበቅ መልካም ቢሆንም ጉዳዩ እንቅልፍ ሊነሳን አይገባም።

የመፀዳጃ ቤት መቀመጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"የመፀዳጃ ቤቶች መቀመጫዎች [በቀላሉ] የአባላዘር በሽታዎችን ቢያስተላልፉ፤ በሁሉም የዕድሜ ክልል እና ፆታዊ ግንኙነት ባልጀመሩ ሰዎች አዘውትረን እናየው ነበር" ይላሉ ሮበርትስ።

በተመሳሳይም ከመፀዳጃ ቤት መቀመጫዎች በደም የሚተላለፉ በሽታዎች የመያዝ ዕድልም ዝቅተኛ ነው።

ከሁሉም በፊት የፈሰሰ ደም ካለ በማየት ራስን መከላከል የሚቻል ሲሆን፤ ወሲባዊ ግንኙነት እና የተበከለ መርፌ በሌለበት ሁኔታ በሽታዎች በቀላሉ በደም አይተላለፉም ሲሉም ያክላሉ።

በተመሳሳይ ሁኔታ በመፀዳጃ ቤት መቀመጫ ከሌላ ሰው የሽንት ኢንፌክሽን የመያዝ ዕድል ዝቅተኛ መሆኑን ፕሮፌሰር ሮበርትስ ይናገራሉ።

ከመቀመጫው ሰገራ በሽንት ቱቦ በኩል ከገባ ብቻ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የመያዝ ዕድል ቢኖርም፤ ይህም ሊሆን የሚችለው በዚያ ያለ ዓይነ ምድር ሲሆን ብቻ ነው።

ፕሮፌሰር ሮበርትስ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የራስን ዓይነ ምድር ወደ ብልት በማቅረብ የመያዝ ዕድሉ ከዚህ የበለጠ ከፍ ያለ መሆኑንም ያክላሉ።

ምን ዓይነት በሽታ ሊይዘን ይችላል?

በወሲባዊ ግንኙነት ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ በሽታዎች ሁኔታ ግን ሌላ ነው።

'ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ'ን (ኤችፒቪ) የሚያስነሳው የብልት ኪንታሮት ለአንድ ሳምንት ያህል ቁሳቁስ ላይ መቆየት ይችላል። ይሁን እንጂ በርካታ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው።

ኔቫዳ የሚገኘው ቱሮ ዩኒቨርስቲ የማይክሮባዮሎጂ እና ኢሚኖሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ካረን ዱስ፤ "እነዚህ ቫይረሶች በጣም ረቂቅ በመሆናቸው በከባቢ ላይ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ የሚያደርጋቸው ሽፋን አላቸው" ይላሉ።

የሕዝብ መፀዳጃ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ውስጥ በጣም ቆሻሻው ክፍል ወለሉ ነው

'ኤችፒቪ' የእጅ ማፅጃ ፈሳሾችን የመቋቋም አዝማሚያ ያለው እና ጠንካራውን የሽፋን ክፍል ለማፅዳት 10 በመቶ በረኪና ያስፈልጋል ይላሉ።

እንዲህም ሆኖ እነዚህ ቫይረሶች ወደ ሰውነታችን ሊገቡ የሚችሉት የብልት ቆዳ አካባቢ ክፍተት ካለ እንደሆነም ያክላሉ። ለምሳሌ መፀዳጃ ቤት ስትቀመጡ ሽፍታ ወይም ቁስል ካለ ማለት ነው።

'ኤችፒቪ' በዋናነት በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት በቆዳ ንክኪ የሚተላለፍ ነው።

ምን ዓይነት ጥንቃቄ እናድርግ?

የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን ስንጠቀም ከመቀመጣችን በፊት መቀመጫውን መጠቅለል ወይም የመቀመጫ መሸፈኛ መጠቀም የተሻለው የንፅህና መንገድ ሆኖ ሊሰማን ይችላል።

'ዩገቭ' የተባለው የምርምር ቡድን በ2023 የሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመለክተው፤ 63 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካዊያን መፀዳጃ ቤት ያለ ሽፋን የሚቀመጡ ሲሆን፤ ግማሽ የሚሆኑት ደግሞ ከመቀመጣቸው በፊት መቀመጫውን ይሸፍናሉ።

ይህ የሕዝብ አስተያየት እንደጠቆመው 20 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ከመቀመጥ ይልቅ ቁጢጥ ማለትን ይመርጣሉ።

ነገር ግን የሶፍት ሽፋን አሊያም የመቀመጫ መሸፈኛ ከበሽታ አምጪ ተህዋሲያን አይከላከሉም።

ለዚህም ምክንያቱ ቁሳቁሶቹ ቀዳዳ ያላቸው መሆኑ ነው። ስለዚህ ጀርሞች ብልትን እንዳይነኩ መከላከል አይችሉም።

እንደ ኦሃዮ ግዛት ዌክስነር ሜዲካል ማዕከል የዳሌ ጤና ባለሙያ ስቴፈኒ ቦቢነገር ቁጢጥ ማለት ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል።

ሴቶች ሽንታቸውን ለመሽናት ወደ መፀዳጃ ቤቱ ሲያጎነብሱ በዳሌ ግድግዳ እና ጡንቻ መካከል መጨናነቅ ይፈጠራል። ይህም ከፊኛ የሚነሳውን የሽንት ፍሳሽን ያስተጓጉላል። በጡንቻ ላይ የበለጠ መገፋፋት እና ዳሌ ላይ አላስፈላጊ ጫናም ይፈጠራል።

በሌላ መልኩ ሴቶች በሂደቱ ሙሉ ፊኛቸው ውስጥ ያለውን ሽንት አይሸኑም ማለት ሲሆን፤ ይህም አልፎ አልፎ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እንዲፈጠር ያደርጋል።

ትክክለኛው ችግር

በመፀዳጃ ቤቶች በሽታ የመያዝ አደጋ በአጠቃላይ በመፀዳጃ ቤት መቀመጫ እና በብልት መካከል በሚፈጠር ንክኪ ብቻ የሚከሰት አይደለም።

ይልቁንም አደጋው እጃችን የመፀዳጃ ቤት መቀመጫውን ሲነካ እና በባክቴሪያ እና ቫይረስ ሲበከል ነው። ከዚያም በቆሻሻ እጃችን ፊታችንን እና አፋችንን እንነካለን።

አንድ ሰው ወደ መፀዳጃ ቤት ሲገባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች መቀመጫዎች ብቻ ሳይሆኑ የበር እጀታዎችም ንጽህናቸው የተጠበቀ አይደሉም

በመፀዳጃ ቤት መቀመጫ አካባቢ የሚታዩ የሰገራ ነጠብጣቦች የተለያዩ ዓይነት በሽታ አምጪ ተህዋሲያንን ሊያስይዙ ይችላሉ።

ወደ ሰውነት ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ እንደ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና ተቅማጥ የመሳሰሉ የጨጓራ በሽታ ምልክቶች ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ዓይነ ምድር 'ኖሮቫይረስ' ሊያስይዝ ይችላል። ይህ በጣም ተላላፊ በሽታ አምጭ ተህዋስ ሲሆን ከተበከሉ ቦታዎች እንዲሁም በምግብ እና መጠጥ አሊያም ከታመመ ሰው ጋር በሚኖር ቀጥታ ንክኪ በቀላሉ ይሠራጫል።

በተበከለ ስፍራ እስከ ሁለት ወር ድረስ ሊቀመጥ ይችላል። እናም አንድ ሰው በአነስተኛ መንገድ ሊታመም ይችላል።

አንድ ጥናት እንዳመለከተው በመታጠቢያ ቤት ውስጥ የተበከሉ ቁሶችን መንካት ከኮቪድ-19 እና ከ'አዲኖቫይረስ' ጋር ሲነፃፀር በ'ኖሮቫይረስ' የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

እንዲህም ሆኖ በበሽታው የመታመም ስጋት ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል። ፕሮፌሰር ሮበርትስ "መታጠቢያ ቤት ከጥንት ጀምሮ በዓይነ ምድር የተበከለ አይደለም፤ በየቀኑ ይፀዳል" ይላሉ።

ፕሮፌሰር ሮበርትስ ተማሪዎቻቸው ከኮምፒተውር ክፍል የወሰዱት የማይክሮብ ናሙና ከመፀዳጃ ቤቶች ጋር ሲነፃፀር የበለጠ የተበከለ ነው ብለዋል።

በአሪዞና ዩኒቨርስቲ 'የቪሮሎጂ' ፕሮፌሰር የሆኑት ቻርለስ ጀርባ "በዩኒቨርስቲያችን እንዳጠናነው በአሜሪካ ቤት ውስጥ ካሉ መፀዳጃ ቤቶች ይልቅ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች በጀርም የተበከሉ ናቸው" ይላሉ።

መፀዳጃ ቤት ከማስነጠስ ተጠንቀቁ

መፀዳጃ ቤት ከተጠቀምን በኋላ በተበከለ እጃችን አፋችን ከመንካት ባሻገር ሌላ በሽታ የምንያዝበት ሌላ መንገድ አለ።

መፀዳጃ ቤት ተጠቅመን ውሃ በምንለቅበት ቅፅበት ሳህኑ ላይ ያሉ ጀርሞች በአየር ተነስተው እጅ መታጠቢያ ገንዳው ላይ ያርፋሉ። እናም ገንዳው አጠገብ ላይ ከሆንን እኛ ላይ ያርፋሉ።

በመፀዳጃ ቤት ካሉ ከ40 እስከ 60 በመቶ የሚሆኑ ቅንጣቶች የመፀዳጃ ቤቱን ገንዳ ለቀው ሊጓዙ እንደሚችል ይገመታል።

ፕሮፌሰር ገርበር "ይህንም አንዳንድ ሰዎች 'የመፀዳጃ ቤት ንጥሻ' ይሉታል" ይላሉ።

ይህ ስጋት ከመፀዳጃ ቤት መቀመጫ ባለፈ በእጅ በቀጥታ የሚነኩ የመፀዳጃ ቤት ክዳን፣ የውሃ መልቀቂያ ቁልፍ፣ የበር እጀታ፣ የመታጠቢያ ሲንክ መክፈቻ እና መዝጊያ፣ የፎጣ ማስቀመጫ ስጋት አላቸው ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

በጀርም የተሞላው አካባቢ ግን ወለሉ ነው ይላሉ።

በመፀዳጃ ቤት ራሳችንን እንዴት እንጠብቅ?

በዩናይትድ ኪንግደም ሎግቦሮ ዩኒቨርስቲ የውሃ ንፅህና ኢንጂነር የሆኑት ኤልዛቤት ፓዲ በተቻለ መጠን ትንሽ ቁሶችን ብቻ መንካትን ይመክራሉ።

የመፀዳጃ ቤት እቃ አምራቾች ሰዎች በእጃቸው በተደጋጋሚ እንዳይነኩ የመፀዳጃ ቤት ክዳኖችን መተው አለባቸውም ይላሉ።

ሌላው መንገድ ሥራችን ካጠናቀቅን በኋላ ውሃ ለቀን ወዲያው መፀዳጃ ቤቱን ለቆ መውጣት ነው።

ፕሮፌሰሩ ምንም እንኳ ገቢራዊነቱ እውን ባይመስልም በሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች አንድ ሰው ተጠቅሞ ከወጣ በኋላ ለ10 ደቂቃ መቆየትን ይመክራሉ።

ፕሮፌሰር ሮበርትስ መፀዳጃ ቤት እየተጠቀምን ስልክ መጠቀምን የማይመክሩ ሲሆን፤ ለዚህ የሚሰጡት ማብራሪያ እጃችንን ብንታጠብ እንኳ ስልካችን በመበከል ተህዋሶችንን ይዘን እንዞራለን የሚል ነው።

በሕዝባዊ መፀዳጃ ቤቶች እጅን በደንብ በሳሙና በማሸት መታጠብ በሽታ ለመከላከል ይረዳል።