ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአማራ ክልል ያለውን የዘፈቀደ ጅምላ እስር ለማስቆም ዓለም አቀፍ ጫና እንዲደረግ አምነስቲ ጠየቀ
በአማራ ክልል ወራት ያስቆጠረውን መንግሥት እያካሄደ ያለውን 'የዘፈቀደ የጅምላ እስር ዘመቻ' ለማስቆም ዓለም አቀፍ ጫና እንዲደረግ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።
ድርጅቱ መንግሥት እያካሄደው ያለው የዘፈቀደ የጅምላ እስር አራት ወራትን እንዳስቆጠረ በገለጸበት በጥር 20/ 2017 ዓ.ም. መግለጫው በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በእስር ላይ እንዳሉ አስታውሷል።
"በአማራ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በዘፈቀደ በጅምላ ታስረው ዓለም አቀፉ ዝምታን መምረጡ ከማሳፈር በላይ ነው። የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች እንዲሁም የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በዘፈቀደ የታሰሩ ዜጎች በሙሉ እንዲፈቱ ያላቸውን ተጽዕኖ በመጠቀም በይፋ ጥሪ ሊያደርጉ ይገባል" ሲሉ የአምነስቲ የምሥራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ቲገሬ ቻጉታህ ጥሪ አቅርበዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም "የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እየተላለፈ ባለበት በዚህ ወቅት ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ቀውስን በቸልታ ሊመለከተው አይገባም" ብለዋል።
ቻጉታህ አክለውም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ያለ ክስ እና ያለ ፍርድ ቤት እውቅና ለወራት ታስረው መቆየታቸው ተቀባይነት እንደሌለው በዚሁ መግለጫቸው ጠቅሰዋል።
"በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ክስ ሳይመሰረትባቸው እንዲሁም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለወራት አስሮ ማቆየት የፍትህ መጓደል እንዲሁም ግልጽ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው" ሲሉ ዳይሬክተሩ ተችተዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለምንም ሕጋዊ መሠረት መታሰራቸው ብቻ ሳይሆን ባለሥልጣናቱ በአማራ ክልል በዘፈቀደ የሚያደርጉትን እስር መቀጠላቸውንም አመልክተዋል።
ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እነዚህ "በዘፈቀደ ታስረው ያሉትን ሁሉ" በአስቸኳይ እንዲለቁ ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው ወንጀሎች ክስ እንዲመሠሰርቱ በዚሁ መግለጫ ላይ ጠይቀዋል።
አምነስቲ በዚህ ዓመት መስከረም አጋማሽ ገደማ የኢትዮጵያ ጦር እና የአማራ የፀጥታ ኃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በዘፈቀደ አስረው በአራት ጊዜያዊ የእስር ካምፖች ውስጥ እንዳስገባቸው አስታውሷል።
ለአንድ ወር በዘለቀው "የዘፈቀደ እስር" የተያዙ "በሺዎች የሚቆጠሩ" ነዋሪዎች በዳንግላ፣ በኮምቦልቻ እና በሸዋ ሮቢት ከተሞች እንዲሁም በጭልጋ ወረዳ በሚገኙ ጊዜያዊ የእስር ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ አምነስቲ ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ አስታውሶ ነበር።
ዒላማ ከተደረጉት ሰዎች መካከል ዳኞች እና ዐቃቢያነ ሕግ የተካተቱበት የፍትህ አካላት እንዲሁም ምሁራን ይገኙበታል ተብሏል።
በጥር ወር ባለሥልጣናቱ ሦስት ዳኞች፣ ሴቶች፣ በዕድሜ የገፉ እንዲሁም ስር የሰደደ ጤና ችግር ያለባቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ቢፈቱም በሺዎች የሚቆጠሩ በዘፈቀደ በእስር ላይ እንደሚገኙ አምነስቲ በዚህ መግለጫው ጠቅሷል።
መግለጫው ባለሥልጣናቱ ከእስር በተጨማሪ የሲቪክ ምህዳሩን በማጥበብ አራት የሲቪል ድርጅቶችን ባገዱበት ሁኔታ "በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃ ጫና ማድረግ አስፈላጊ" እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ "ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መሥራት ሲገባቸው ከዓላማቸው ውጭ በመንቀሳቀስ የሀገርን ጥቅም የሚጎዳ ተግባራት ላይ መሰማራታቸው" በሚል መታገዳቸው ይታወሳል።
ይህንንም አስመልክቶ ሂውማን ራይትስ ዋች ረቡዕ፣ ጥር 21/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ባለሥልጣናት ይህንን የእግድ ውሳኔ በመሻር በገለልተኛ ድምጾች ላይ የማነጣጠር እርምጃዎችን እንዲያቆሙ ጠይቋል።
"ባለፈው አንድ ዓመት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅቶች ላይ ተከታታይ ትንኮሳ አካሂደዋል። መሠረታዊ የሚባሉ ሰብዓዊ መብቶችን የሚሰንዱ እንዲሁም ቅስቀሳ ላይ የተሰማሩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን ማገዳቸው መንግሥት ገለልተኛ የሆነ ክትትልን እንደማይቀበል አመልካች ነው" ሲሉ የሂውማን ራይት ዋች የአፍሪካ ዳይሬክተር ማውሲ ሰጉን መናገራቸው በድርጅቱ መግለጫ ላይ ተካቷል።
ኢትዮጵያ፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የተሰኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ማገዷ ይታወሳል።