ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያን ውጥረት ለማርገብ ኬንያ የባሕር ጠረፍ ስምምነት ሃሳብ አቀረበች
ኬንያ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ለማርገብ ያስችላል ያለችውን ቀጠናዊ የባሕር ጠረፍ አገልግሎት አጠቃቀም ስምምነት አማራጭ አቀረበች።
ይህ ኬንያ ያቀረበችው አማራጭ በቀጠናው የሚገኙ የባሕር በር የሌላቸው አገራት በንግድ ስምምነት መሠረት የባሕር መተላለፊያ አገልግሎት እና ጥቅም የሚያገኙበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሏል።
ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የመግባቢያ ሠነደ መፈረሟ በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ መካከል ከፍተኛ ውጥረትን ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ በመሪዎቻቸው መካከል የተፈራረሙት የመግባቢያ ሠነድ ኢትዮጵያ ነጻ አገር መሆኗን ላወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅናን ለመስጠት፣ ሶማሊላንድ በምላሹ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ለመፍቀድ ከስምምነት መድረሳቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ይህንንም ሶማሊላንድን የግዛቱ አንድ አካል እንደሆነች የሚገልጸው የሶማሊያ መንግሥት ስምምነቱን አጥብቆ በመቃወም፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ ድርጊት ነው በማለት አጥብቆ ተቃውሞታል።
ይህን ተከትሎ ሶማሊያ በሞቃዲሾ የሚገኘቱን የኢትዮጵያን አምባሳደር ከአገር አስወጥታ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን ባለፈው ሳምንት ጠርታለች።
በሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለማርገብ ኬንያ አሁን አማራጭ ያለችውን ሐሳብ ወደ ጠረጴዛ አምጥታለች።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በቀጠናው ያሉ የባሕር በር የሌላቸው አገራት በንግድ ስምምነት መሠረት የባሕር በር የሚያገኙበትን አማራጭ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ኮሪር ሲንጋኦኢ እንደሚሉት ከጂቡቲ እና ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በሚደረገው ምክክር ቀጠናዊ የባሕር አገልግሎት አጠቃቀም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል ብለዋል።
“ኢጋድ የባሕር በር አገልግሎት አጠቃቀም የሚደነግግ ሕግ ማርቀቅ ይችላል” ያሉት ባለሥልጣኑ፣ ናይሮቢ የምታቀርበው አማራጭ ተቀባይነትን የሚያገኝ ከሆነ ኢትዮጵያ “አስተማማኝ የባሕር በር አማራጭ ይኖራታል” ሲሉ ኮሪር ተናግረዋል።
እኒህ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ባለሥልጣን ኬንያ ያቀረበችው አማራጭ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የሶማሊያን ሉዓላዊ አንድነት የሚያረጋግጥ ይሆናል ብለዋል።
ኬንያ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ከመጋረጃ ጀርባ ሁለቱን አገራት ስታደራድር ስለመቆየቷ ሲገለጽ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአንድ ወር በፊት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝነት ወደ ናይሮቢ ተጉዘው ከፕሬዝዳን ዊሊያም ሩቶ ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ኬንያ ያመሩት በሁለቱ አገራት ግንኙነት እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋጋር እና በዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ መሆኑ ተገልጾ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከትናንት ሐሙስ ጀምሮ የሶማሊያው ፕሬዝዳን ሐሰን ሼክ መሐሙድ ለሥራ ጉብኝነት ናይሮቢ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ከኬንያቸው አቻቸው ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች እና ቅጠናዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት፣ ቪላ ሶማሊያ ገልጿል።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ኮሪር ኬንያ ያቀረበችውን አማራጭ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እያጤኑት መሆኑን ገልጸው የቀረበውን አማራጭ ወደፊት ለመውሰድ የሁለቱ አገራት መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲነጋገሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል ብለዋል።