ሩሲያ በሲቪል እቃ ጫኝ መርከብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽማለች ተብላ ተወቀሰች

የሩሲያ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሩሲያ በሲቪል ጭነት ተሸካሚ መርከብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽማለች ሲል የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከሰሰ።

ተደጋጋሚ የክሩዝ ሚሳኤል ጥቃት ደረሰ የተባለውም መርከቧ ባለፈው ወር በዩክሬን ኦዴሳ ወደብ ባረፈችበት ወቅት ነው።

ነሀሴ አጋማሽ ላይ ተፈጸመ የተባለው ጥቃትም በዩክሬን አየር መከላከያ መክሸፉን የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የላይቤሪያ ሰንደቅ አላማ የያዘችው መርከብ ከሩሲያ በተተሶሱ ሚሳኤሎች ኢላማ ተደርጋለች ሲልም ነው ያከለው።

ሩሲያ በሐምሌ ወር በጥቁር ባህር በኩል ወደ ዩክሬን ወደቦች የሚያመሩ መርከቦች እንደ ወታደራዊ ኢላማ ሊቆጠሩ ይችላሉ የሚል ማስጠንቀቂያ አስተላልፋለች።

ሩሲያ ይህንንም ማስጠንቀቂያ ያስተላለፈችው በተባበሩት መንግሥታት አማካኝነት እህል በጥቁር ባህር ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ከዩክሬን ወደቦች እንዲወጣ የሚያደርገውን ስምምነት መውጣቷን ካሳወቀች በኋላ ነው።

በወቅቱም የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአገሪቱ የግብርና ምርቶች ላይ በርካታ እገዳዎች እንዳሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

የሩሲያን የግብርና ባንክን ከዓለም አቀፉ የክፍያ ስርዓት ጋር ማገናኘት፣ በሩሲያ የማዳበሪያ ኩባንያዎች ላይ የሚጣሉ ገደቦች እንዲነሱ እና መርከቦቿ የውጭ ወደቦችን እና የመድን ሽፋኖችን እንዲያገኙም ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበዋል።

ሩሲያ ከስምምነቱ በወጣች በተከታዩ ቀናቶች ውስጥም በደቡባዊ ዩክሬን በሚገኙ ወደቦች ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች መፈጸሟም ተነግሯል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ሰኞ ዕለት ለፓርላማ ባደረጉት ንግግግር በእህል መርከቧ ላይ ተቃጥቶ የከሸፈው ጥቃት “ፑቲን ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጠ ማሳያ ብቻ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም “ዩክሬን ጭነቶቿን በአለም አቀፍ ውሃ ላይ የማጓጓዝ መብት አላት እንዲሁም አለምን ለመመገብ የሚረዳውን የመላክም የሞራል መብት አላትም” ሲሉም አስረድተዋል።

ሩሲያ በሲቪል እቃ ጫኝ መርከብ ላይ ተቃጥቷል ስለተባለው ጥቃት እስካሁን የሰጠችው አስተያየት የለም።

ሩሲያ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እህል ለመጓጓዝ ከሚያስችለው ስምምነት ከወጣች በኋላም የዩክሬን የወደብ መሰረተ ልማትን የበለጠ ኢላማ እንዳደረገችም ተነግሯል።