ደቡብ አፍሪካ ከቡድን 20 እንድትወጣ እንደሚፈልጉ ትራምፕ ገለጹ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ ከቡድን 20 መውጣት አለባት ብለው እንደሚያምኑ ገለጹ።

ደቡብ አፍሪካ የቡድን 20 ጉባዔን ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች ባለችበት ወቅት ነው ትራምፕ ይህን ያሉት።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ ቪንሰንት ማግዋንያ በበኩላቸው አገራቸው የቡድን 20 (G20) ጉባዔን በተሳካ ሁኔታ እንደምታስተናግድ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ የዓለም ትልልቅ ምጣኔ ሃብት ያላቸው አገራት በጆሀንስበርግ ይገናኛሉ።

ደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ መድልዎ ታደርሳለች ብለው በተደጋጋሚ የከሰሱት ትራምፕ፤ በጉባዔው እንደማይገኙና በምትካቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስን እንደሚልኩ ገልጸዋል።

ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ጉባዔውን የምታዘጋጀው አሜሪካ ናት።

"ደቡብ አፍሪካ የቡድኑ አባል መሆን የለባትም። በአገሪቱ አስከፊ ነገር እየሆነ ነው። አገሬን ወክዬ እዛ አልገኝም" ብለዋል ትራምፕ።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለትራምፕ አስተያየት በይፋ ምላሽ አልሰጠም።

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ከነጭ አፍሪካነሮች ለሚቀርቡ የስደተኝነት ጥያቄዎች ቅድሚያ ለመስጠት መወሰኗን ደቡብ አፍሪካ መቃወሟ ይታወሳል።

በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ "የዘር ማጥፋት" ተፈጽሟል የሚለው የአሜሪካ ክስ በሰፊው ውድቅ የተደረገ እና ተአማኒ ማስረጃ የሚጎድለው መሆኑንም መንግሥት ገልጿል።

የደቡብ አፍሪካ የወንጀል አሐዝ ነጮች ከሌሎች ደቡብ አፍሪካውያን በተለየ ዒላማ መደረጋቸውን አያሳይም።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ ልዩ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ መንግሥት ያለ ካሳ መሬት መውሰድ እንዲችል የሚፈቅድ ሕግ አጽድቀው ነበር።

ይህንን ተከትሎም ትራምፕ በ2025 መባቻ ላይ በብዛት የደች እና የፈረንሳይ ዝርያ ላላቸው የደቡብ አፍሪካ ነጮች የስደተኝነት መብት አቅርበው ነበር።

የእስያን የፋይናንስ ቀውስ ተከትሎ እአአ በ1999 የተመሠረተው ቡድን 20 የመጀመሪያ ጉባዔውን ያደረገው በ2008 ነው።

የቡድን 20 አባል አገራት መሪዎች በየዓመቱ ጉባዔ ያካሂዳሉ። በጉባዔው የአውሮፓ ኅብረት እና የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮችም ይገኛሉ።

በዓለም ላይ ያለው የምጣኔ ሃብት ችግር እና አገራቱ የገጠማቸውን ፈተና በተመለከተ ውይይት ያደርጋሉ።

አንድን አገር ከቡድን 20 ማስወጣት የሚቻልበት መደበኛ አሠራር የለም። ቡድኑ ሕጋዊ ወዋቅር ወይም የአገራት የፊርማ ስምምነትም የለውም። የቡድኑ አባላት የተሰባሰቡት ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ተስማምተው ነው።

'ፎሬን ፖሊሲ ሴንተር' በተባለው ቲንክ ታንክ የሚሠሩት ዶ/ር አንድሪው ጋዋትሮፕ እንዳሉት፤ አንድ አገር ከቡድን 20 ተባሯል የሚባለው በጉባዔዎች እንዳይሳተፍ ሲደረግ ነው።

"የቡድን 20 ጉባዔን የሚያዘጋጅ አገር አንድን አገር ካልጋበዘ፤ ያልተጋበዘው አገር ተባሯል ብለን እንወስዳለን" ሲሉ አብራርተዋል።

የቡድኑ አባል አገራት እንዲህ ያለ ውሳኔ ላይ የሚደርሱበት ዕድል ጠባብ እንደሆነ ባለሙያው አስረድተዋል።

በቻተም ሀውስ ተመራማሪ የሆኑት ክሪስ ቫንዶም በበኩላቸው አሜሪካ በቡድን 20 "እንደ አዋኪ" የተቆጠረችባቸው አጋጣሚዎች አሉ ብለዋል።

አሜሪካ የቡድኑ አባል መሆኗ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋትም ይገልጻሉ።

"የአውሮፓ ኅብረት ለደቡብ አፍሪካ የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣል። ቻይናም የደቡብ አፍሪካን ከቡድኑ መውጣት አትደግፍም" ብለዋል።

ቡድኑ ስምንት አባል አገራት ባሉት ወቅት እአአ በ2014 ሩሲያ ክሬሚያን በመጠቅለሏ ምክንያት ከአባልነት ማስወጣቱ ይታወሳል። አሁን ግን ሩሲያ የቡድን 20 አባል አገር ናት።

ጉባዔውን የሚያስተናግድ አገር የውይይት ነጥቦችን የማዘጋጀት ሚና አለው።

ደቡብ አፍሪካ ዘንድሮ የጉባዔው መሪ ቃል ያደረገችው "ትብብር፣ እኩልነት እና ዘላቂነት" መሆኑን የመንግሥት ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

"ከዘር መድልዎ እና ክፍፍል በመውጣት ወደ ዴሞክራሲ ያደረግነውን ሽግግር መነሻ አድርገን የቡድን 20ን ጉባዔ ላይ ስለ ትብብር እና እኩልነት እንወያያለን" ብለዋል።