ሕንዳዊቷን ታዳጊ ከ13 ዓመቷ ጀምሮ ከደፈሩ 64 ወንዶች መካከል 28ቱ በፖሊስ ተያዙ

በሕንድ በሕጻናት ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት ጨምሯል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሕንድ በሕጻናት ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት ጨምሯል

በደቡብ ሕንድ በምትገኘው ኬራላ የምትኖረው የ18 ዓመት ታዳጊ ከ13 ዓመቷ ጀምሮ 64 ወንዶች ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሱባት ካሳወቀች በኋላ ፖሊስ ወደ 30 የሚጠጉትን ይዟል።

ታዳጊዋ በሕንድ ከተገለሉ ማኅበረሰቦች መካከል አንዱ የሆነው የዳሊት ማኅበረሰብ አባል ናት።

ከ64ቱ ወንዶች መካከል ፖሊስ 28ቱን በቁጥጥር ሥር አውሏል። እስካሁን የተያዙት ተጠርጣሪዎች በይፋ ያሉት ነገር የለም።

ተጠርጣሪዎቹ ከ17 እስከ 47 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። የ18 ዓመቷ ታዳጊ ጎረቤቶች፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አሠልጣኞች እና የአባቷ ጓደኞችም በወሲባዊ ጥቃቱ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል እንደሚገኙ ፖሊስ አስታውቋል።

መንግሥት ያሠማራቸው የሥነ ልቦና አማካሪዎች ታዳጊዋን ካነጋገሯት በኋላ ነው ስለደረሰባት የወሲብ ጥቃት የገለጸችው።

በሕንድ ሕግ ማኅበረሰቦችን 'አይነኬ' በሚል የሚያገሉ ድርጊቶችን መፈጸም ወንጀል እንደሆኑ ተደንግጓል።

በሒንዱ የጎሳ እርከን ውስጥ ዳሊት የተባለው ማኅበረሰብ በመጨረሻው ደራጃ ላይ ይገኛል።

የዚህ ማኅበረሰብ አባል የሆነችው ታዳጊ ወሲባዊ ጥቃት ይደርስባት የጀመረው ልጅ ሳለች መሆኑ የፍርድ ቤት ቅጣትን ሊያከብደው እንደሚችል ተገልጿል።

ፖሊስ 25 አባላት ያሉት ቡድን አዋቅሮ ጉዳዩን እየመረመረ ነው።

ታዳጊዋ የ13 ዓመት ልጅ ሳለች ጎረቤቷ ወሲባዊ ጥቃት ፈጽሞባታል፣ እርቃን ምሥሏንም ወስዷል።

የልጆች ጥበቃ ኮሚቴ ውስጥ የሚሠሩ የሕግ ባለሙያ ለኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣ እንደተናገሩት አትሌት የሆነችው ታዳጊዋ በተለያዩ የስፖርት ካምፖች ውስጥ ለጥቃት ተጋልጣለች።

ፖሊስ እንዳለው ባለፉት አምስት ዓመታት ታዳጊዋ ሦስት ጊዜ በቡድን ተደፍራለች።

ጥቃት የፈጸሙባት ሰዎች የደወሉላት በአባቷ ስልክ ስለነበር ፖሊስ የጥሪውን መነሻ ቁጥር ለማግኘት እየሞከረ ነው።

ቤተሰቦቿ ጥቃት እየደረሰባት እንደሆነ አያውቁም ነበር።

መንግሥት ያሠማራቸው የሥነ ልቦና አማካሪዎች ታዳጊዋን ካነጋገሯት በኋላ ጉዳዩን ለሕጻናት ጥበቃ ክፍል ጠቁመዋል።

የሕጻናት ጥበቃ ክፍል ኃላፊ ለኢንዲያን ኤክስፕሬስ ጋዜጣ "የሥነ ልቦና ድጋፍ ሲሰጣት ነው እንዴት ከ13 ዓመቷ ጀምሮ የወሲብ ጥቃት ይደርስባት እንደነበር በግልጽ የተናገረችው" ብለዋል።

ታዳጊዋ አሁን ወደ ማቆያ ማዕከል ተወስዳለች። የደረሰባትን በዝርዝር ለሴት ፖሊስ ትናገራለች ተብሎ ይጠበቃል።

የተፈጸመባት ድርጊት በሕንድ ድንጋጤና ቁጣ ፈጥሯል።