የኢትዮጵያ ብድር መክፈል አለመቻል እና የሚያስከትለው ዳፋ

የዶላር ኖቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያ ያጋጠማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዕዳዋን እንዳትከፍል ጫና ፈጥሯል

ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ለሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ መክፍል የሚጠበቅባትን የ33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ የመክፈያ ጊዜ ቀነ ገደብ አራት ቀን አልፎታል።

ኢትዮጵያ በታኅሣሥ 2007 ዓ.ም. የ1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ሽያጭ አድርጋ ላገኘችው ብድር የወለድ መክፈያ ጊዜያው ባለፈው ሰኞ ታኅሣሥ 1/2016 ዓ.ም. ሲያበቃ መንግሥት ወለዱን በቀነ ገደቡ መክፈል እንደማይችል አስታውቋል።

የቦንድ ሽያጭ ብድር የ6.625 % ዓመታዊ ወለድ የሚከፈልበት ሲሆን፣ የወለድ መጠን ዓመታዊ ይሁን እንጂ የአከፋፈል ሂደቱ በዓመት ሁለት ጊዜ ወይም በየስድስት ወሩ የሚፈጸም ነው።

ይህ አስር ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የአገሪቱ የቦንድ ሽያጭ ዕዳ በሚቀጥለው ዓመት ታኅሣሥ 2017 ዓ.ም. መከፈል ይኖርበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ዋናው ብድር እስከሚከፈል ባሉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓመታዊ ወለድ ለአበዳሪዎቹ ይከፍላል። እናም ይህንን የወለድ ክፍያ ነው የገንዘብ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ መክፈል እንደማትችል ያስታወቀው።

ነገር ግን ኢትዮጵያ ወለዱ መከፈል ባለበት ጊዜ መክፈል እንደማትችል ካሳወቀች በኋላ ከቦንድ ባለቤቶቹ ጋር ውይይት ለማድረግ ትናንት ሐሙስ ታኅሣሥ 4/2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞ ሌሎች አማራጮችን ለመፈለግ መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የቦንድ ባለቤቶች ኮሚቴ ይህን የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ “አላስፈላጊ እና አሳዛኝ” አድርጎ እንደሚመለከተው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ውሳኔውን የማያጥፍ ከሆነ ግን ከፍ ያለ ዳፋ ይኖረዋል ማለታቸው ተነግሯል።

የኢኮኖሚ እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ከቦንድ ባለቤቶች ጋር በገባችው ስምምነት መሠረት ወለዱን በመክፈያ ቀነ ገደቡ ላትከፍል ትችላለች ወይም (technically default) ልታደርግ ትችላለች ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ወለዱን ለመክፈል 14 ቀናት የዕፎይታ ጊዜ እንደተሰጣት ያስታወሱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ በዚህ ጊዜ ውስጥ ገንዘቡ የማይከፈል ከሆነ ውልን አለማክበር (technical default) ያጋጥማታል ይላሉ።

ብድር መክፈል አለመቻል (default) ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓመታት በፊት ቦንድ ለሽያጭ አቀርቦ የ1 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሲያገኝ ብድሩን በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመመለስ ከአበዳሪዎቿ ጋር ውል አስሯል። የዚህ ውል አንድ አካል የሆነው የብድሩ የወለድ ምጣኔ እና የአከፋፈል ሁኔታ ነው።

ብድሩ 6.625 % ዓመታዊ የወለድ ምጣኔ ሲኖረው አከፋፈሉም በዓመት ሁለት ጊዜ በየስድስት ወሩ ነው። ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ይህን የወለድ መጠን ስትከፍል ብትቆይም፤ አሁን ግን ይህን ወለድ መክፈል እንደማትችል የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በብድር ስምምነቱ መሠረት ዕዳን አለመክፈል “technical default” (ውልን አለማክበር) ሊባል እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ዶ/ር አብዱልመናን “በውሉ መሠረት ወለድ መክፈል አለመቻል [ውይም] በውሉ መሠረት ዋናውን ብድር ለመክፈል አለመቻል” ውልን አለማክበር እንደሚባል ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በውሉ መሠረት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ወለዱን አለመክፈሉ ውሉን እንዳያከብር እንደሚያደርገውም ያክላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ “አጠቃላይ የቦንድ ዕዳን [መክፈል] አልችልም ማለት” አጠቃላይ ብድርን መክፍል አለመቻል መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከቦንድ ባለቤቶቹ ጋር ከሚያደርጉት የሐሙስ ውይይት በኋላ የኢትዮጵያ ብድር የመክፈል አቅም ቁርጡ ይታወቃል።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን መንግሥት ይህን ውይይት “ሰፋ ባለ አውድ ውስጥ ነው የወሰደው” ይላሉ። መንግሥት “የውጭ ዕዳውን ለመክፈል ስለተቸገረ” ከሌሎች አበዳሪዎችም ጋር አየተደራደረ መሆኑን በማስታወስም፤ እንደ ሌሎች ብድሮች ሁሉ ይህኛውም የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግለት ይፈልጋል ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሐሙሱ ውይይት ካቀረባቸው ነጥቦች መካከል የብድሩን የወለድ ምጣኔ ከ6.625 % ወደ 5.5 % ዝቅ ማድረግ አንደኛው ነው። ሌላኛው ነጥብ የዋናወን የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲሸጋሸግም የሚጠይቅ ነው።

ዶ/ር አብዱልመናን የኢትዮጵያ መንግሥት ከቦንድ ባለቤቶቹ ጋር ከስምምነት ይደርሳል የሚል እምነት እንደላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “ሁለቱንም በሚጠቅም መልኩ ወደ ሆነ ስምምነት መምጣታቸው አይቀርም ብዬ እገምታለሁ” ይላሉ።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያም በተመሳሳይ፤ በመንግሥት እና በአበዳሪዎች መካከል የሚካሄደው ንግግር “ቀላል ውይይት አይደለም የሚሆነው፤ በኢትዮጵያ በኩል ግን ተስፋ አለኝ የሚሳካ ይመስለኛል” ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የዩሮ ገንዘብ ኖቶች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ውይይቱ ካልተሳካ ዳፋው ምን ይሆናል?

ቢቢሲ ያነገገራቸው ሁለቱም ባለሙያዎች በውይይቱ ከስምምነት ይደረሳል ይበሉ እንንጂ “ውይይቱ ባይሳካ” የሚኖረው ተጽዕኖ ቀላል አለመሆኑን ይናገራሉ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሙያ “ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታ አንጻር ይህኛው ብድር ላይ ብቻ ነው ወይ የሚከናወነው? ሌሎችን ብድሮችንስ የመክፈል አቅም አላት ወይ?” በማለት የሚከተሉትን ውጤቶች ይጠቅሳሉ።

“ነገሮች ካልተመቻቹ የመከፍል አቅሟ ጫና ውስጥ ስለሆነ ያገጠማት ውልን አለማክበር (technical default) ወደ ዕዳን መክፈል አለመቻል (sovereign default) ሊቀየር ይችላል” ሲሉ የአገሪቱ ወቅታዊ የኢኮኖሙ ሁኔታ እና የብድር መክፈል አቅም ላይ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

ዶ/ር አብዱልመናን በበኩላቸው ውይይቱ ያለ ስምምነት ተቋጭቶ ኢትዮጵያ ወለዱን እንዲሁም ብድሯን መክፈል ባትችል፤ “ከሌሎች አበዳሪዎች ጋር የጀመረችውን ድርድር ይጎዳዋል” ይላሉ።

ከአጠቃላይ ኢትዮጵያ የውጭ ብድር ግማሽ ያህሉን የምተሽፍነው ቻይና ለኢትዮጵያ የአንድ ዓመት የዕዳ ሽግሽግ አድርጋለች። በተጨማሪም በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ ውይይት እያካሄደች ነው።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ብድር ለመክፈል አለመቻል ሌሎች ድርድሮችን በመጎዳት ብቻ አያበቃም። ዶ/ር አብዱል መናን ይከሰታል የሚሉትን ዳፋ እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል፤ “ከአይኤምኤፍ እናገኛለን ብለን ተስፋ የምናደረግው ገንዘብ ካለ በጣም ሊንጓተት ይችላል። ኢንቨስትሮች ካሉበት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በተወሰነ ሊያሻክርው ይችላል። የሚሰጡት እርዳታ ላይም ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል።”

ዶ/ር አብዱልመናን አክለውም ከእርዳታ መጓተት ጋር በተያያዘ መንግሥት የሚኖርበትን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ገንዘብ ወደማትም ሊገባ እንደሚቸል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ይህ በበኩሉ በአገሪቱ ያለውን ከባድ “የዋጋ ግሽበት ሊያባብሰው ይችላል” ይላሉ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ባለሙያ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ብድር ለመክፈል አለመቻል፤ “የወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ ብዙ ጫና ይኖረዋል” በማለት ውጤቱ መጠነ ሰፊ መሆኑን ያስቀምጣሉ።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በቅርብ የሚከታተሉት ባለሙያው አክለውም፤ “ብዙ የመተማመኛ ሰነዶች ተቀባይነት ያጣሉ። ወደፊት እንደዚህ እናደርጋለን፣ ክፍያ እንፈጽማለን፣ መተማመኛ እንሰጣለን፣ ወደፊት ለምከፍለው ክፍያ ዛሬ ላይ አገልግሎት እናግኝ ዛሬ ላይ ዕቃ ይላክ ተበሎ የሚደረጉ የክፍያ ሰነዶች በአጠቃላይ እምነት ያጣሉ። ስለዚህ እሱ ትልቅ ኪሳራ ነው፞።”

ይህ በበኩሉ የግል ኩባንያዎችን የንግድ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳይችሉ ሊያደርጋቸው ከፍ ሲልም ሠራተኛ እንዲቀንሱ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል ባለሙያው ጨመረው ጠቁመዋል።

“ዕቃዎችን በገበያ ውስጥ ማግኘት አለመቻል” እና “የዕቃዎች ዋጋ በጣም መናር” በተመሳሳይ ሊከሰት የሚችል ሌላኛው ጉዳይ መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል።

እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ማብራሪያ የአገሪቱ ኢንቨስትመንትም በኢትዮጵያ መንግሥት ዕዳን አለመክፈል ምክንያት የሚጎዳው ሌላኛው ዘርፍ ነው።

የኢኮኖሚ ባለሙያው ይህን ሲያብራሩ፤ “ኢንቨስተሮች በኢኮኖሚው ላይ ማታመን ያጣሉ፤ ስለዚህ ወደፊት ኢንቨስት አድርጌ ገንዘቤን አገኛለሁ የሚል ኢንቨስተር ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል። ያሉ ኢንቨስተሮች የመስፋፊያ ዕቅዳቸውን ሊሰርዙ ይችላሉ። ወደፊት ኢንቨስት እናደርጋለን ብለው ያሰቡ ሰዎችም ፕሮጀክቶቻቸውን የመሰረዝ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ከዚያ በመለስም ኢትዮጵያ እንደ ኢኮኖሚ ተወዳዳሪ መሆን ያቅታታል” ይላሉ።