ለሜቻ ግርማ ሆስፒታል የገባበት የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል

ለሜቻ በቃሬዛ ከሜዳ ሲወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፓሪስ ኦሎምፒክ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር በሞሮኮው ሶፊያን ኤል ባኻሊ አሸናፊነት ተጠናቋል።

አትሌቱ እአአ በ1936 ከተካሄደው ኦሎምፒክ ወዲህ በተከታታይ ሁለት ኦሎምፒኮች ላይ አሸናፊ ለመሆን ቅቷል።

ከውድድሩ በፊት ሲጠበቅ የነበረው ፉክክር በኤል ባኻሊ እና በኢትዮጵያዊው የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ለሜቻ ግርማ መካከል ይሆናል የሚል ነበር።

ለሜቻ ፍጥነት መጨመር በጀመረበት መጨረሻዎቹ ጥቂት ሜትሮች ላይ መሰናክሉን ዘሎ ለማለፍ ባደረገው ጥረት ወድቆ ወደ ሆስፒታል በመወሰዱ የተጠበቀው ፉክክር ሳይታይ ቀርቷል።

ለሜቻ በደረቱ በወደቀበት የህክምና ባለሙያዎች ደርሰው በቃሬዛ ይዘውት ወጥተዋል።

“ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ መሰናክል ከደረሰበት ጉዳት በኋላ ሜዳ ውስጥ በነበሩ የህክምና ባለሙያዎች ዕርዳታ ተደርጎለታል። በፍጥነት እንዲያገግም ምኞታችን ልንገልጽ እንወዳለን” ሲል የፓሪስ ኦሎምፒክ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

“የአትሌቱን ሁኔታ ለመከታተል ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ባለስልጣናት ጋር እየተገናኘን ነው” ሲልም መግለጫው አክሏል።

ለሜቻ የዓለም የ3 ሺህ ክብረ ወሰንን ባለፈው ዓመት ፓሪስ ላይ ነበር የሰበረው።

በቶኪዮ ኦሎምፒክ እና በሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ ከኤል ባኻሊ ጋር የነበረውን ፉክክርም በሽንፈት አጠናቋል።

በውድድሩ ወቅት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች የቡድን ሥራ በማከናወን ወርቁን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነበር። ሳሙኤል ፍሬው፣ ጌትነት ዋለ እና ለሜቻ መጀመሪያ ላይ ከፊት ሆነው በፍጥነት ለመሄድ ሞክረዋል።

ውድድሩ ፈጣን ሰዓት ይመዘገብብታል ሲባል ደግሞ ሦስቱም ፍጥነቱን ቀንሰው ሲሮጡም ታይተዋል።

ኤል ባኻሊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዩጋንዳው ሊዮናርድ ቹሜታይ ከኋላቸው ሆኖ አጋጣሚውን ለመጠቀም ሙከራ ቢያደርግም እሱም በውድድሩ ወቅት በመውደቁ ህልሙ ተጨናግፏል።

ከሊዮናርድ መውደቅ በኋላ ውድድሩ በትክክልም የለሜቻ እና የኤል ባኻሊ መስሎ ነበር። ሁለቱም በጥሩ አቋም ላይ ይመስሉም ነበር።

የለሜቻ አወዳደቅ ስታደ ፍራንስ ሆነው ከስታዲየም ውድድሩን ከሚከታተሉ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውድድሩን በቴሌቭዥን መስኮት እስከሚከታተሉት ድረስ ድንጋጤን ፈጥሯል።

ኤል ባኻሊ ረዣዥም ቅልጥሞቹን እና አጋጣሚውን ተጠቅሞ ለሞሮኮ ወርቅ አስገኝቷል።

አትሌቱ ባለቀ ሰዓት ወደፊት መስመር ከመጣ በኋላ ውድድሩን በዚያው ለማጠናቀቅ ችሏል።

አሜሪካዊው ኬኔት ሩክስ ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቋል።

ኤል ባኻሊ ውድድሩን 8 ደቂቃ 6.05 ሰከንድ በመግባት ነው የወርቅ ሜዳሊያውን ማሳካት የቻለው።

በዚህም እአአ በ1932 እና 1936 የፊንላንዱ ቮልማሪ ኢሶ-ሆሎ በተከታታይ ሁለት ጊዜ ውድድሩን ካሸነፈ በኋላ መጀመሪያው ሯጭ ለመሆን በቅቷል።

ኬንያዊው አብረሃም ኪብዎት ደግሞ ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያውን ለማሸነፍ በቅቷል።