ከ10 ዓመት በኋላ 39 በመቶ የቤት ውስጥ ሥራዎች በሮቦቶች ሊከናወኑ ይችላል ተባለ

ከአሥርት ዓመት በኋላ ከቤት ውስጥ ሥራ 39 በመቶ የሚሆነውን ሮቦቶች እንደሚከውኑት ተመራማሪዎች ገለጹ።

የዩናይትድ ኪንግደም እና የጃፓን አጥኚዎች 65 የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) ባለሙያዎች በ10 ዓመታት ውስጥ ምን ደረጃ ላይ ሊደረስ እንደሚችል ግምታቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ባለሙያዎቹም ከ10 ዓመታት በኋላ ሰዎችን የመንከባከብ እና የቤት ውስጥ ሥራ በሮቦት ሊከወን ይችላል ብለዋል።

ለቤት ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ግብዓቶችን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ አስቤዛ የሚያደርጉት ማሽኖት ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዎቹ የገመቱ ሲሆን፤ በንጽጽሩ ለጨቅላዎች እና ለአዛውንቶች እንክብካቤ ማድረግ ላይ ግን ሮቦቶች የሚኖራቸው ኃላፊነት የጎላ አይሆንም ብለዋል።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እና የጃፓኑ ኦቻኖሚዙ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከባለሙያዎች በሰበሰቡት አስተያየት መሠረት ልጆችን ማስተማር፣ ማጫወት እንዲሁም አዛውንቶችን መንከባከብ ሮቦቶች በብዛት የሚሳተፉበት አይሆንም።

ይሁን እንጂ ከአስር ዓመታት በኋላ የሰው ልጆች በግብይት የሚያሳልፉት ሰዓት በ60 በመቶ ይቀንሳል።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ክፍያ የማይፈጸምባቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች በሮቦቶች መከናወናቸው የጾታ እኩልነትን ያመጣል ይላሉ።

በመላው ዓለም የቤት ውስጥ ሥራን የማከናወን ጫናው ሴቶች ላይ ስለሚበረታ በሴቶች ገቢ እና ቁጠባ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል። ስለዚህም በሮቦቶች የሚከናወኑ የቤት ውስጥ ሥራዎች በጨመሩ ቁጥር፤ የጾታዊ እኩልነት ይጨምራል።

ከዚህ በተጨማሪም የቤት ውስጥ ሥራን ሮቦቶች የሚያከናውኑ ከሆነ የሰው ልጆች የተሻለ ሕይወት ይኖራቸዋል።

ባለሙያዎቹ ይህን አስተያየት ይስጡ እንጂ ቴክኖሎጂ ያለበት ደረጃ በሚጠበቀው መልኩ ሮቦቶችን ብቁ ላያደርግ ይችላል የሚል አስተያየት የሚሰጡም አልጠፉም።

ለዚህም እንደምሳሌ የሚነሳው እአአ በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ቴክኖሎጂ ዘምኖ በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ ሮቦቶች ምግብ ማብሰል፣ ሕጻናትን ማጫወት እና ግብይት መፈጸምን ጨምሮ በርካታ የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራት ይችላሉ የሚል ትንበያ ቢኖርም ይህን ግን ፍሬ አላፈራም።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ኤካቴሪና ያለ አሸከርካሪ የሚሄዱ መኪኖች ጸንሰ ሐሰብ ከ10 ዓመታት በፊት የነበረ መሆኑን አስታውሰው፤ አሁንም ሮቦቶች እራሳቸው ችለው እንዲያሸከረክሩ ያስቻለ አጥጋቢ ቴክኖሎጂ የለም ይላሉ።

ይህም ብቻ አይደለም፤ የሮቦቶች ቴክኖሎጂ ወጪው ከፍተኛ ነው። ሮቦቶችን የቤት ውስጥ ሥራ ሊያሰራ የሚችሉ እጅግ ውስን የሆነው የማኅብረሰብ ክፍል ነው።