ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህወሓት ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ የሚችልበት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን እንደማያውቅ ምርጫ ቦርድ ገለጸ
ህወሓት በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበ በኋላ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ማድረግ ያለበትን ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን እንደማያውቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ ታኅሣሥ 22/2017 ዓ. ም. በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያደርግ አሳስቧል።
በመግለጫው፣ ቦርዱ ለህወሓት ደብዳቤው እስከጻፈበት ቀን ድረስ ፓርቲው ከተመዘገበ በስድስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ቦርዱ አያውቅም ተብሏል።
ቦርዱ በማኅበራዊ ገፁ የለጠፈው ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰው ቀን ታኅሣሥ 17/2017 ዓ. ም. ነው።
በልዩ ሁኔታ የተመዘገበ ፓርቲ ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ አዋጁ ያዛል።
ህወሓት በኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዘናና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1332/2016 መሠረት በልዩ ሁኔታ ነሐሴ 3/2016 ዓ. ም. መመዝገቡን ቦርዱ አስታውሷል።
መግለጫው አክሎ "በተለያየ ጊዜ ለፓርቲው በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ የተሰጡ ውሳኔዎችን በማክበር በቀረው አጭር ጊዜ የጠቅላላ ጉባዔውን እንዲያደግ ቦርዱ በጥብቅ ያሳስባል" ብሏል።
በምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ ላይ ፓርቲው በልዩ ሁኔታ ከተመዘገበ ጀምሮ ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ የሚገባው ወቅት ሊገባደድ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ የቀረው መሆኑ ተጠቅሷል።
ፓርቲው በሕግ የተጣለበትን ግዴታ በወቅቱ ሳይፈጽም ቢቀር "ቦርዱ ሕጉን መሠረት በማድረግ ተገቢ ነው የሚለውን ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን በአክብሮት ያስገነዝባል" ሲልም ደብዳቤው ያትታል።
ህወሓት በልዩ ሁኔታ መመዝገቡ የተገለጸበት ደብዳቤና የምዝገባ ሰርትፊኬት ከደረሰው አንስቶ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ አንዳለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
ፓርቲው በልዩ ሁኔታ የተመዘገበው ነሐሴ 3/ 2016 ዓ. ም. በመሆኑ ጠቅላላ ጉባዔውን እስከ የካቲት 3/ 2017 ዓ. ም. እንዲያደርግ ይጠበቃል ሲልም አክሏል።
"ለጠቅላላ ጉባዔ ዝግጅት የሚያስፈልገውን የቅድመ ጉባዔ ዝግጅት የተመለከቱ ሥራዎችን ቦርዱ መከታተል እንዲችል ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔውን ከማድረጉ 21 ቀናት በፊት ጉባዔው የሚደረግበትን ቀን ለቦርድ እንዲያሳውቅ የሚጠበቅ ነው" ይላል።
"ይሁንና ይህ ደብዳቤ አስከተጻፈበት ቀን ድረስ ፓርቲው ከተመዘገበ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔ ማድረግ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ቦርዱ አያውቅም" ሲል ገልጿል።
የህወሓት አመራሮች ለወራት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ ይገኛሉ። በህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል ካለፈው ዓመት አጋማሽ ወዲህ የተከሰተው አለመግባባት አሁንም ቀጥሏል።
ህወሓት ነሐሴ ወር ላይ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የሚሆኑ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና ከፍተኛ ካድሬዎችን ከአመራርነት ያነሳበት 14ኛ ጉባዔን ተክትሎ ሁለቱም እየተካሰሱ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጉባዔውን የህወሓት ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን ውሳኔን ወደ ጎን ብሎ የተካሄደና 'ሕጋዊነቱ' ላይ ጥያቄ የተነሳበት ነው ማለቱ ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም በደብረጽዮን የሚመራው ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ወገን ያሉትን አመራሮች በ "ብሔራዊ ክህደት" መክሰሱ ይታወሳል።
አቶ ጌታቸውም ሲቪላዊ አስተዳደሮች ላይ "መፈንቅለ መንግሥት" እየፈጸመ ነው ሲሉ በደብረጽዮን የሚመራውን ቡድን በተደጋጋሚ ወንጅለዋል።