የግብፅ መንግሥት ደጋፊ በለንደን መታሰር ምክንያት በተፈጠረ ውዝግብ ዩኬ በካይሮ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ዘጋች

የዩኬ ኤምባሲ በግብፅ

የፎቶው ባለመብት, UK embassy

የግብፅ መንግሥት ደጋፊ በለንደን በነበረ ተቃውሞ ላይ ለአጭር ጊዜ መታሰሩን ተከትሎ በተፈጠረ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ዩናይትድ ኪንግደም በካይሮ የሚገኘውን ኤምባሲዋን በጊዜያዊነት ዘጋች።

ለንደን በሚገኘው የግብጽ ኤምባሲ ከጋዛ ከበባ ጋር በተያያዘ በነበረ ተቃውሞ ቀንደኛ የግብፅ መንግሥት ደጋፊ የሆነው አብደል ቃድር ተቃዋሚዎቹን ተጋፍጧቸዋል በሚል አጠር ላለ ጊዜ ለእስር ተዳርጎ ነበር።

በዚህ የዲፕሎማሲ ውዝግብ መካከል የግብፅ ባለስልጣናት በካይሮ የሚገኘውን የዪኬ ኤምባሲ ህንጻ ውጭ ያለውን የደህንነት መከላከያ አጥሮች ማስወገዳቸውን ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲዋን በጊዜያዊነት መዝጋቷ ተገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ጽህፈት በመዲና ጋርደን ሲቲ ስፍራ የሚገኘው ኤምባሲ "እነዚህ አዳዲስ ለውጦች እስኪገመገሙ ድረስ ተዘግቶ ይቆያል" ብሏል። ሆኖም ኤምባሲው ስራውን አያቋርጥም ተብሏል።

በለንደን ከጋዛ ከበባ ጋር ተያይዞ በግብጽ ኤምባሲ ለተደረገው ተቃውሞ ዩናይትድ ኪንግደም በሰጠችው ምላሽ ጋር ተያይዞ ግብፅ አጸፋዊ ምላሽ እንድትሰጥ ጥሪዎች ተበራክተው ነበር።

እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት እና በረሃብ ቀውስ ውስጥ ያለችውን የጋዛን ሰርጥ ድንበር የምትጋራው ግብፅ ይህንን ከበባ እንዲሰበር አስተዋጽኦ እንድታደርግ ሰልፎቹ የሚጠይቁ ናቸው ተብሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በለንደን በሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ በነበረው ሰልፍ ተቃዋሚዎቹን ተጋፍጦ ነበር የተባለው ግብጻዊ ለአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ መፈታቱ ተዘግቧል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዴላቲ ባለፈው ሳምንት የዩናይትድ ኪንግደም የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጆናታን ፓውልን በመጥራት ስለ እስሩ ማብራሪያ መጠየቃቸው ተዘግቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል ግብፅ "በቪየና ስምምነት መሰረት ለግብፅ ኤምባሲዎች ጥበቃ ማድረግ ባልቻሉ " አገራት ላይ "አጸፋዊ ምላሽ የመስጠት መብት" አላት ሲሉ ተናግረው ነበር።

የግለሰቡ እስር በግብፅ ውዝግብ ያስነሳ ሲሆን አንዳንድ ፖለቲከኞች ባለስልጣናቱ በካይሮ የሚገኘውን የዩኬ ኤምባሲ የደህንነት መከላከያ አጥር እንዲያስወግዱ ጠይቀዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በካይሮ የሚገኘው ኤምባሲ ጸጥታ እንዲሁም በሰራተኞቹ ደህንነት ዙሪያ ከግብጽ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ቢቢሲ ተረድቷል።

በካይሮ በሚገኘው የዩናይትድ ኪንግደም አና የአሜሪካ ኤምባሲዎች ደጃፍ ላይ ትልልቅ የደህንነት መከላከያ አጥሮች የቆሙ ሲሆን በስፍራው ያለውን የትራፊክን ፍሰትን በማስተጓጎል ይተቻሉ።

በካይሮ የሚገኘው የዩኬ ኤምባሲ በአውሮፓውያኑ 2013 እና 2014 ከጸጥታ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በጊዜያዊነት ተዘግቶ ነበር።