ከአምስት እናቶች አንዷን የሚያጠቃው እና መራመድን አስቸጋሪ የሚያደርገው ሕመም

የፎቶው ባለመብት, Rebecca Middleton
ሬቤካ ሚድልተን ነፍሰጡር ስትሆን ከመውለዷ በፊት ባሉት የመጨረሻዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ በዊልቸር እንደምትንቀሳቀስ አላወቀችም ነበር።
ሬቤካ በእርግዝናዋ የመጀመርያዎቹ ሦስት ወራት ማቅለሽለሽና ሕመምን ተከትሎ አስቸጋሪ ጊዜያት አሳልፋ ነበር፤ እርግዝናዋ አራት ወራት ሲያልፈው ደግሞ ከባድ የዳሌ አካባቢ ሕመም ጀመራት።
"መራመድ አልችልም ነበር፣ በሕይወቴ ውስጥ ሁልጊዜም የታችኛው የጀርባ ሕመም እና ሌሎች ችግሮች ነበሩብኝ። ግን ያን ያህል ጉልህ አልነበረም እና ከእርግዝናዬ በኋላ ግን በፍጥነት ተባባሰ" ትላለች።
ስለ ሕመሙ ከተናገረች በኋላ፣ ወደ ፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ተላከች። እና በመጨረሻም ከፍተኛ የዳሌ መገጣጠሚያ ሕመም (ፒጂፒ) እንዳለባት ታወቀ። ይህም ሲምፊሲስ ፒዩቢክ ዲስፈንክሽን (SPD) በመባልም ይታወቃል።
በእርግዝና ወቅት ከዳሌ መገጣጠሚያዎችዎ ጋር የተያያዙ ችግሮች የተለመዱ ናቸው፤ ከአምስት ነፍሰ ጡር እናቶች አንዷን በተወሰነ ደረጃ ይጠቃሉ።
"እንደገና መራመድ እችል ይሆን? ልጄን እንዴት እወልዳለሁ፣ እንዴት እንከባከበዋለሁ? የሚል ፍርሃት ይዞኝ ነበር።"

የፎቶው ባለመብት, Rebecca Middleton
ሬቤካ ከወለደች በኋላ ብዙም ሕመም አልነበራትም፤ ነገር ግን አሁንም እንደ መራመድ፣ ልጇን ማንሳት ወይም የልጇን ጋሪ መግፋት ባሉ መሠረታዊ ነገሮችን ለማከናወን ትታገል ነበር።
"ለሰባት ወራት የአካል ጉዳተኛ ሆኜ ነበር እና ሁልጊዜ የሚረዳኝ ሰው ማግኘት ነበረብኝ" ትላለች።
"ሕፃንን በመንከባከብ ረገድ ማድረግ የምችላቸውን ነገሮች ማድረግ አልቻልኩም፤ በጣም ፈታኝ ጊዜ ነበር።"
ከማርገዝዋ በፊት፣ ሬቤካ የማታውቀው ችግር ነበር፣ ነገር ግን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሴቶችን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ለመደገፍ የሚረዳ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሆነው በፔልቪክ ፓርትነርሺፕ በበጎ ፈቃደኝነት መሳተፍ ጀመረች።
ይህ ሁኔታ በትክክለኛው እርምጃ ሊታከም እንደሚችል ድርጅቱ ይናገራል።
እንዴት እርዳታ ማግኘት ይቻላል?
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ እናቶች ሕመሙ ምልክት እንደጀመራቸው በቀላሉ የሚሰጥ ሕክምናን ጨምሮ፣ ለእነሱ ተብሎ ተለይቶ የሚታዘዙ ሕክምናዎችን እንዲያገኙ እና ከሐኪምች ጋር እንዲወያዩ ይመክራል።
በዚህ መልኩ አገልግሎት ያላገኘች ነፍሰ ጡር እናት ወደ ጠቅላላ ወይም ማኅፀን እና ጽንስ ሐኪም ተመልሰው በመሄድ ተጨማሪ አስተያየት እንዲያገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ይመክራል።
ከሕመሙ ጋር የመኖር ስሜታዊ ተፅእኖዎችን ለመቆጣጠር እንዲረዳቸው ደግሞ እናቶች የአእምሮ ጤና ድጋፍ ለማግኘት መጠየቅ ይችላሉ።
የሴቶች የጤና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኒጋት አሪፍ፣ ከፍተኛ ግንዛቤ እና አስቀድሞ መመርመር እንደ ሬቤካ ያሉ ታካሚዎችን ከዊልቸር ወይም ክራንች ሊታደጉ እንደሚችሉ ይናገራሉ።
"ስለ ሴት አካል በጣም ጥሩ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ አስቀድሞ መለየት ከሌለ፣ ከእነዚህ ሴቶች መካከል አንዳንዶቹን አብሯቸው ለሚኖር አሉታዊ ተጽዕኖዎች ይዳረጋሉ" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Victoria Roberton
የፔልቪክ ፓርትነርሺፕ አስተባባሪ ቪክቶሪያ ሮበርተን ስለ ህመሙ ግንዛቤ መኖር እንዴት እንደሚረዳ ማሳያ ትሆናለች።
እንደ ሬቤካ፣ በመጀመሪያው እርግዝናዋ ወቅት ሁኔታው ሲያጋጥማች የዳሌ አካባቢ ሕመም (ፒጂፒ) ምን እንደሆነ አታውቅም ነበር።
በተመከረችው መሠረት በተቻለ መጠን ንቁ ለመሆን ሞከረች። በበይነ መረብ እና በስልክ ወደ ሚሰጡ የኤንኤችኤስ የፊዚዮቴራፒ ክፍለ ጊዜዎች ተላከች፤ ነገር ግን እርግዝናዋ እየገፋ ሲሄድ ሕመሙ እየተባባሰ እንደሄደ አስተዋለች።
"ሰውነትን ማሳሳብን ጨምሮ ልናደርጋቸው የሚገቡ እንቅስቃሴዎችን ሰጡን። በዚህ ጊዜ አንዳቸውንም ማድረግ አልቻልኩም። በጣም ያማል" ትላለች።
ለቪክቶሪያ መቀመጥ እንኳን ምቾት የማይሰጣት ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር፤ እና ልጇን እስከምትወልድ ድረስ አብዛኛውን ጊዜዋን በቤት ውስጥ ታሳልፍ ነበር።
ልጇን ከወለደች በኋላ ሕመሙ እየቀነሰ ቢሄድም ነገር ግን ሁለተኛ ልጇን ስትፀንስ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟት ነበር።
ለብዙ እናቶች አማራጭ ባይሆንም ቪክቶሪያ የሕክምና ታሪኳን ከግምት ውስጥ በማስገባት የግል ፊዚዮቴራፒ ከፍላ ለመጠቀም እንደወሰነች ተናግራለች። ምክንያቷ ደግሞ የኤን ኤች ኤስ የሪፈራል ቀጠሮ መጠበቂያው ረጅም ጊዜ ስለነበር ነው።
ፊዚዮቴራፒው ሙሉ የጤና ግምገማ እና የጋራ እንቅስቃሴን ጨምሮ ተግባራዊ ሕክምና ሰጥቷታል። እንዲሁም የዳሌ መገጣጠሚያዎቿን እንዳያባብሱ ሰውነቷን እንዴት ማንቀሳቀስ እንደምትችል የተለያዩ መንገዶችን አሳይተዋታል፤ ይህም ሕመሙን ለማስታገስ ረድቷታል።
ቪክቶሪያ ዛሬ ከአራት ዓመታት በኋላ አሁንም ከዳሌ መገጣጠሚያ ሕመም ጋር ብትታገልም፣ በሁለተኛው እርግዝናዋ ወቅት ሁኔታዋን እና እንዴት መቋቋም እንደምትችል ስለተረዳች ለመቆጣጠር በጣም ቀላል ነበር።
የሬቤካ ሁለተኛ እርግዝና በተመሳሳይ መልኩ የበለጠ አዎንታዊ ተሞክሮ ነበር።
በዚህ ጊዜ ሁሉ የዳሌ መገጣጠሚያ ሕመም ሊያጋጥማት እንደሚችል ታውቃለች፤ ስለዚህ በእርግዝናዋ ወቅት የከፋ ነገር ከማጋጠሙ በፊት ሕክምና ማግኘት ችላለች።
ሁለተኛ ልጇን ከወለደች በኋላ ከዳሌ መገጣጠሚያ ሕመም በሁለት ወራት ጊዜ ማገገም ችላለች። ከመጀመሪያ ልጇ መወለድ በኋላ ግን ለሁለት ዓመታት ማገገም አልቻለችም ነበር።
"ከልጆቼ ሁሉ በፊት ከነበርኩበት የተሻለ ጤንነት ላይ ነኝ፤ ምክንያቱም አሁን የዳሌ መገጣጠሚያ ሕመም ምን እንደፈጠረብኝ አውቃለሁ፤ እና ሙሉ በሙሉ ያለ ማሽን እገዛ በተደረገልኝ ሕክምና ችግሬ ተፈቷል" ትላለች።
"ስለ ጉዳዩ በቂ እውቀትና ግንዛቤ ስለሌለኝ በነበረኝ ሕመም ምክንያት አምስት ዓመታት ሲኦል ሆኖብኝ ነበር።"















