በቁጥር ስህተት ምክንያት ከሌላ አባት ተወልዳ በርካታ እህት እና ወንድሞች ያገኘችው ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Hadeya Okeafor
ሃዴያ ነኝ ብላ የማታስበውን እንደሆነች ያወቀችበትን ቀን አትረሳውም።
በወቅቱ የ12 ዓመት ታዳጊ ስትሆን ከእናቷ ጋር ሶፋ ላይ ተቀምጠው ፊልም እያዩ ነበር።
ከዚያ እናቷ "ይህ አንቺ ላይ የደረሰ ነው ብዬ ብነግርሽ ምን ትያለሽ" ስትል ወሬውን ጀመረች።
ለመጀመርያ ጊዜ ሃዴያ የተፀነሰችው በሕክምና ድጋፍ የወንድ ዘር እና የሴቷ እንቁላል በብልቃጥ ውስጥ እንዲዋሃዱ በሚደረግበት በአይቪኤፍ እንደሆነ ሰማች። ግን በአይቪኤፍ ሕክምናው ወቅት ስህተት ተፈጥሮ ነበር።
"የማስታውሰው ምን የተሳከረ ታሪክ ነው እያልኩ እያሰብኩ እነደነበር ነው። ደግሞም እንዴት ይህንን ቀደም ብዬ አላወቅኩም? እያልኩም ነበር። ነገር ግን ልጅ ነበርኩ። ስለዚህ ብዙም ግድ ሰጥቶኝ አለማሰቤ ያሳምን ነበር" ትላለች ሃዴያ።
ሃዴያ ይህንን የሰማችበትን ቅጽበት "ቅጥ አንባሩ የጠፋው ግኝት ነበር" ስትል ነው የምታስታውሰው።
"እንዲህ ሲታይ የሆነ ነገር ልክ እንዳልሆነ ያስታውቃል፤ ግን ደግሞ ጠይቄ አላውቅም። ዝርዝር ጉዳይ ላይ አልገባም በቃ እናቴ ነጭ ስለሆነች ነው እኔም ነጭ የሆንኩት ብዬ አለፍኩት" ትላለች።
የ26 ዓመቷ ሃዴያ የምትኖረው ካናዳ ሲሆን በሙያዋም አርኪዮሎጂስት ነች።
"ስለዚህ ከጋናዊ ቤተሰቦች የተወለድኩ ቅይጥ ነኝ፤ ግን ሳይታሰብበት" ስትል ትገልፀዋለች።
በለንደን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ሆስፒታል የማህፀንና ጽንስ ዶክተር የሆኑት ዶ/ር ዲሚትሮስ ማቨርሎስ አይቪኤፍ በዓለም ላይ ከተዋወቀ ጊዜ አንስቶ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት በዚህ መንገድ ተወልደዋል ይላሉ።
የአንዱን ዘር ከሌላው ጋር መቀየጥ በሕክምናው ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰት ስህተት ቢሆንም፣ ነገር ግን ሕክምናው እንደተጀመረ ያሉ መመሪያዎች በጣም ጥቂት ስለነበሩ በተደጋጋሚ ያጋጥም እንደነበር ይጠቅሳሉ።
'ልጅነቴ ውሸት አልነበረም'

የፎቶው ባለመብት, Hadeya Okeafor
በምሥራቅ የባሕር ዳርቻ በፕሪንስ ኤድዋርድ ደሴት ላይ በምትገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ ያደገችው ሃዴያ ቤተሰቦቿ በከተማዋ ውስጥ "ከሌሎች ተለይተው የሚታወቁ" እንደነበሩ ታስታውሳለች።
ሃዴያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለች የትምህርት ቤት ጓደኞቿ በቆዳ ቀለሟ ይሳለቁባት ነበር።
"ሌሎች ልጆች 'ጥቁር መሆን ነበረብሽ' ይላሉ ወይም አፍሪካዊ መሆን እንዳለብኝ በተመለከተ አስተያየቶች ይሰነዝሩ ነበር" ትላለች።
እናቷ እርሷን በአይቪኤፍ ሕክምና መውለድ ከቻለች በኋላ ሌሎች ልጆቿን በተፈጥሯዊ መንገድ ነው የወለደቻቸው።
እኔ ላይ የሚሰነዘሩ የዘረኝነት ዘለፋዎች ሌሎች እህትና ወንድሞቼ እንደ ደረሰባቸው ዓይነት የከፉ አይደሉም ትላለች።
"በአንዲት ትንሽ የዓሣ አጥማጆች በሚኖሩባት ከተማ ውስጥ እንኖር ስለነበር ከእኔ ጋር የሚገናኝም ይሁን አይሁን ዘረኝነት የተሞላባቸው አስተያየቶች ገጥሟቸው ነበር" ስትል ትናግራለች።
ሃዴያ በተፀነሰችበት ወቅት የተፈጠረውን "ግራ የሚያጋባ" ስህተትን ማወቋ ከአባቷ ጋር የነበራትን ግንኙነት አልለወጠውም፤ በቀላሉ ስለ ሕይወቷ ያለውን አንድ እውነታ ብቻ አረጋግጦላታል።
"ለነበረኝ ጥያቄ መልስ ሰጠኝ፤ ነገር ግን አሁንም ማወቅ ለምፈልገውን የመጨረሻውን መልስ አላገኘሁም" ትላለች።
አሁንም እንዴት ስህተቱ ሊፈጠር እንደቻለ ማወቅ እንደምትፈልግ አክላ ተናግራለች።
"ሁልጊዜም ያሳደገኝ እርሱ አባቴ ነው። እርሱ በተወለድኩበት ቀን እና ከዚያ በፊትም አብሮኝ ነበር። ዛሬም አብሮኝ አለ። ስለዚህ በእውነቱ የተለየ ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም" ትላለች።
"ልጅነቴ ውሸት አልነበረም፤ ሁል ጊዜም የቤተሰቡ አባል ነበርኩ። በምበላው ምግብ፣ በሚነገረው ቋንቋ እንደ ጋናዊ ሆኜ ነው የኖርኩት። በእርግጥ ቋንቋውን መናገር አልችልም እና አንዳንድ ጊዜ የሚያወሩትን ማዳመጥ እፈልጋለሁ።"

የፎቶው ባለመብት, Hadeya Okeafor
የሃዴያ ወላጆች በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በቶሮንቶ ከተገናኙ በኋላ በአንድ ዓመት ውስጥ ተጋቡ።
"አባቴ ያደገው በጋና የባሕር ዳርቻ ከተማ ቴማ ሲሆን፣ በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወደ ካናዳ በመምጣት ቶሮንቶ ውስጥ ይኖር ጀመር። በሰሜን ሩስቲኮ የተወለደችው እናቴን ያገኛት በፕሪንስ ኤድዋርድ ደሴት ነው።"
ለዓመታት ልጅ ለመውለድ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ሲቀር በቶሮንቶ በሚገኘው እና አሁን በሕይወት በሌሉት ዶ/ር ፊሮዝ ካምሲ ወደሚመራው ክሊኒክ በማምራት የአይቪኤፍ ሕክምና ጀመሩ።
አይቪኤፍ ፅንሱ ወደ ሴቷ ማህፀን ውስጥ ከመግባቱ በፊት የሴት እንቁላል በወንዱ የዘር ፍሬ በላብራቶሪ ውስጥ የሚዳብርበት ሂደት ነው።
በኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን (IVF) ሕክምና ከማህፀን ውጪ በላብራቶሪ የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ እና የሴቷ እንቁላል እንዲዋሃዱ ይደረጋል።
ይህ የተገናኘ እንቁላል እና የዘር ፍሬ ከ5 እስከ 6 ቀን በላብራቶሪ ውስጥ እንዲያድግ ይደረግና ተመልሶ ለእንቁላሏ ባለቤት በማህጸኗ ውስጥ እንዲያድግ ይቀመጣል።
እንዲህ ያለው ሳይንሳዊ ጥበብ የሚሞከረው በተፈጥሯቸው አምጠው መውለድ ላልቻሉ፤ እንቁላላቸው ከወንድ ዘር ጋር ለመዋሀድ የማይመች፤ የማህጸን ቱቧቸው (fallopian tube) ችግር ያለበት ሴቶች ናቸው።
በወንዶችም በኩል በቂ የወንድ ዘር ፍሬ ቁጥር ያለመኖር ካልሆነም የዘር ፍሬው ወደ ሴት ልጅ እንቁላል ውስጥ ለመግባት ኃይል እና ጉልበት ሲያጣ ኢንቪትሮ ፈርትላይዜሽን (IVF) ይሞከራል።
"እኔ ከመረገዜ በፊት ለሰባት ዓመታት ያህል ለመፀነስ ሞክረዋል" በማለት "ረጅም የአይቪኤፍ ሕክምና ሂደት ነበር" ስትል ወላጆቿ ያለፉበትን ታስታውሳለች።
ባልና ሚስቱ ለዶክተሩ ግልጽ የሆነ ጥያቄ አቀረቡ። ከሁለቱም ወላጆች ጋር የሚገናኝ ዝምድና ለመፍጠር እንዲቻል ከጥቁር አፍሪካዊ የተለገሰ የወንዴ ዘር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
"እኔ ስወለድ ወላጆቼ በእርግጠኝነት በነጣው ቆዳዬ በጣም ተገረሙ። እና ወደ አይቪኤፍ ክሊኒክ ሲደውሉ አንድ ዓመት ያህል እንዲታገሱ ተነግሯቸው ነበር።"
ነገር ግን ከአንድ ዓመት በኋላ የሃዴያ እናት ክሊኒኩን ጉዳዩን የበለጠ እንዲመለከትላት ጠየቀች እና የወንድ የዘር ፍሬ የለገሰው ግለሰብ የካውካዢያን ዝርያ እና ቀይ ፀጉር ያለው ግለሰብ እንደሆነ ተነገራት።
"አንድ ዓመት ከሞላኝ በኋላ ክሊኒኩ ስህተት መሥራቱን አመነ. . . የወንዴ ዘር የለገሰው ግለሰብ ብልቃጥ ላይ የተጻፈው ቁጥር ስህተት እንደነበር አረጋገጡ" ትላለች።
ሃዴያ ወላጅ አባቷ እንደተነገራት ቀይ ሳይሆን ቡናማ ፀጉር እንዳለው አወቀች።
ዶክተር ካምሲ ከወላጆቿ ጋር በነበረው ንግግር ወቅት "ባገኛችሁት ነገር ማመስገን አለባችሁ፤ ቆንጆ ቤተሰብ አለሽ፣ የምትፈልጊውን አግኝተሻል። ከፈለግሽ ፍርድ ቤት ልትሄጂና ክስ ልትመሰርቺ ትችያለሽ፤ ነገር ግን ኢንሹራንስ የሚያገለግለው ለዚያ ነው" ማለቱን ተናግራለች።

የፎቶው ባለመብት, Hadeya Okeafor
በአውሮፓውያኑ 2003 ወላጆቿ ክሊኒኩን ከስሰው መጠኑ ባለተገለፀ ገንዘብ ከስምምነት ላይ ደረሱ።
"በጣም አስቂኝ ነው፤ ምክንያቱም በፍርድ ቤት ውስጥ የዲኤንኤ ምርመራ ማድረግ ስለሚያስፈልግ እኔ የካውካዢያን ዘር እንዳለብኝ ማረጋገጥ አልቻሉም። ነገር ግን በጣም ግልጽ ነው ብዬ አስባለሁ። ይህ ደግሞ ከሕግ ሂደት ለማምለጥ የተደረገ የሕክምና ጉዳይን ችላ ማለት ነው።"
የእርሷን ክስ ተከትሎ ክሊኒኩ እስኪዘጋ ድረስ "ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳልተወሰደበት" ሃዴያ ትገልጻለች።
ዶክተር ካምሲ በመጋቢት 2011 ከኦንታርዮ የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች ኮሌጅ ሥራ መልቀቃቸውን ተከትሎ የሕክምና ተቆጣጣሪው ከ26 ታማሚዎች እንክብካቤ፣ ሕክምና እና መዝገብ አያያዝ ጋር የቀረበባቸውን ክስ አቋረጠ።
በተጨማሪም በኦንታሪዮ ወይም በሌላ በማንኛውም አካባቢ በሕክምና ሙያ ለመቀጠል ላለመመዝገብ ወይንም ላለማመልከት ተስማምተዋል።
ከአንድ ለጋሽ የተወለዱ 15 ወንድም እና እህቶች
በአውሮፓውያኑ 2019 ሃዴያ ስለ ወላጅ አባቷ የበለጠ ለማወቅ በመፈለግ የዲኤንኤ ምርመራ አደረገች። ነገር ግን ያኔ ምንም ተጨማሪ መረጃ አላገኘችም።
ከአምስት ዓመታት በኋላ ግን ከእርሷ ጋር ተመሳሳይ ዲኤንኤ እንዳለው የሚናገር ሰው አገኘች። ይህም ወደ 12 የሚጠጉ ወንድሞች እና እህቶቿን እንድታውቅ አድርጓታል።
አብዛኞቹ ወንድሞች እና እህቶቿ ከተመሳሳይ ለጋሽ በተገኘ ዘር የተፀነሱት በአውሮፓውያኑ 1994 እና 1998 መካከል ነው።
"በወቅቱ 12 ወንድሞች እና እህቶች እንዳሉኝ ማወቄ በጣም ግራ አጋብቶኝ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሦስት ተጨማሪ እህት እና ወንድም አግኝቻለሁ።
"ልክ ሌላ የሕክምና ሁኔታ እንደሆነ ነው የሚሰማው፤ የሆነ እኔ ላይ ይሆናል ብለዬ የማላስበው ነገር። ዕድለኛ ካልሆኑት 1 በመቶዎቹ መካከል አንዷ እንደሆንኩ ነው የተሰማኝ፤ ያንን መቀበል ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው" ስትል ታክላለች።
"እናም ከወንድም እና እህቶቼ መካከል ስህተት የተፈጠረው እኔ ላይ ብቻ እንዳልሆነም ተረድተናል። ያ ደግሞ ወደ ሌላ ጥያቄ እና ስለራሴ የበለጠ ለመመርመር አነሳስቶኛል።
"ሁሉም እናቶቻችን በሕክምናው ወቅት ከስድስት እስከ ስምንት ሕጻናት በላይ ከአንድ ለጋሽ እንደማይፀነስ ቃል የተገባላቸው ይመስላል" ትላለች።
ነገር ግን የለጋሹ የወንዴ ዘር ቢያንስ ለ15 የአይቪኤፍ ሕክምና ፈላጊዎች ጥቅም ላይ ውሎ አልፏል።
ይህ መረጃ ለሰሙት ሁሉ አስደንጋጭ ነበር፤ በተለይ ደግሞ በአይቪኤፍ ሕክምና በኩል በተገኘ የወንዴ ዘር መፀነሳቸውን ለማያውቁ ወንድም እና እህቶቿ ስሜቱ ከባድ ነበር።
የወንድ ዘር ለጋሹ በአውሮፓውያኑ 1994 ለዩኒቨርስቲ ኦፍ ካልጋሪ ለሕክምና ምርምር መለገሱን ብቻ እንደሚያውቅ በተፈጥሮ መንገድ የወለዳት ልጁ ለሃዴያ ነግራታለች።
ነገር ግን እንዴት እንደሆነ ባላወቀው መንገድ ክሊኒኩ ዘሩን አግኝቶ ተጠቅሞበታል።
በካናዳ የዘር ፍሬን በመለገስ ላይ የተቀመጠ ገደብ ወይም ከለጋሽ በተገኘ የሚወለዱ የልጆች ቁጥር ላይ የተቀመጠ ሕጋዊ ገደብ የለም።
ነገር ግን አንዳንድ ክሊኒኮች ሙያዊ ውሳኔያቸውን በመጠቀም የራሳቸውን ገደብ ይጥላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Hadeya Okeafor
ሁለቱንም ባሕል በማወቄ "ታድያለሁ'
አብዛኞቹ ከተለገሰ ዘር የተወለዱት ወንድሞቿ እና እህቶቿ እርስ በርስ ለመተዋወቅ እና ለመገናኘት እንዲረዳቸው ሲሉ በከፈቱት የቡድን ውይይት መድረክ ላይ ይጻጻፋሉ።
"እኔ በቅርብ ርቀት የሚኖር ወንድም አለኝ፤ ቤታችን ብዙም ባይራራቅም አንተዋወቅም።"
በአጠቃላይ ሃዴያ ከተለያዩ ዝርያዎች በመገኘቷ ራሷን "ዕድለኛ" አድርጋ ትቆጥራለች።
"አባቴ ወደ ካናዳ ከመጡ የመጀመሪያ ትውልዶች መካከል ነው። በባህሉ በጣም የሚኮራ እና ሁሌም የሚናገረው ነገር ነበር። ስለዚህ ከሁለት ባህል የተቀዳሁ በመሆኔ በጣም ዕድለኛ ነኝ። በፕሪንስ ኤድዋርድ ደሴት ላይ የጋና እና የፈረንሣይ የአካዲያን ባህል ያለኝ ሴት ነኝ።"















