ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
'አዶለሰንስ'፡ መርዛማ ወንድነትን የሚያበረታቱ ድረ ገጾችን መነጋገሪያ ያደረገው አዲሱ ፊልም
በቅርቡ በኔትፍሊክስ የተለቀቀው ፊልም 'አዶለሰንስ' አነጋጋሪ ሆኗል። የ13 ዓመት ታዳጊ አብራው የምትማር ሴትን ለምን ይገድላል? የሚል ጥያቄም አጭሯል።
ለዚህ ጥያቄ ከተሰጡ መልሶች አንዱ ወንዶች ትስስር የሚፈጥሩበት የበይነ መረብ ቡድን የሆነው ማኖስፊር ነው። manosphere የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው እአአ በ2009 ነው።
ወንዶች መዋቅራዊ ሀይል አጥተዋል ብለው ከማመን ጀምሮ አክራሪ ፆተኛ የሆኑ አመለካከቶችን በእነዚህ የበይነ መረብ ቡድኖች ያንሸራሽራሉ።
በእነዚህ ድረ ገጾችና የበይነ መረብ አምዶች መርዛማ ወንድነትን (toxic masculinity) የሚያበረታቱና የሴቶች የእኩልነት ጥያቄን የሚያጠለሹ መረጃዎች ይጋራሉ። ፀረ ፌምኒዝም የሆኑ አመለካከቶችንም ያስተላልፋሉ።
ይህ አካሄድ ከበይነ መረብ ወደ ገሃዱ ዓለም ተሻግሮ በርካቶችን እየደረሰ ይገኛል። የማኅበራዊ ሚዲያ አልጎሪዝሞችም ይህንን አክራሪ ይዘት ወደተጠቃሚዎች እየገፉት ነው።
ማኖስፌር ከዚህ ቀደም ከነበረው ተደራሽነት ከፍ እያለ መጥቷል። እንደ አንድሪው ቴት ያሉ ፆተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከማኖስፌር መስፋፋት ጀርባ ይገኛሉ።
'አዶለሰንስ' የተባለው ፊልም ጸሐፊ ጃን ትሮን ነው። በማኖስፌር ድረ ገጾች የሚዘዋወሩ መረጃዎችን ተከታትሏል።
"መረጃው ሰዎችን የሚስብ እንደሆነ ማወቅ ችያለሁ። ጉዳዩ የአንድሪው ቴት ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ቅርጽ የያዘ ነው" ይላል ጸሐፊው።
ተንታኞች እንደሚሉት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስና የምጣኔ ሀብት ውድቀት በመጠቀም ወጣቶች በተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዒላማ እየተደረጉ ነው።
የ1970ዎቹ የፌምኒዝም ንቅናቄ እኩልነት እና መድልዎን በመቅረፍ ላይ ያተኮረ ነው። በወቅቱ የፌምኒስት ወንዶች ንቅናቄ መሪ በመሆን የታወቀው አሜሪካዊው የመብት ተሟጋች ዋረን ፋረል ነው።
የፆታ ሚና እንዲሁም አባታዊ ሥርዓት ወንዶችንም የሚጎዳ ነው በሚል ለወንዶች መብት በመቆምና የፌምኒስት ንቅናቄን በመደገፍ ይታወቅ ነበር።
ሆኖም ግን በወንዶች ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን በመቃወም የሴቶች መብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን ሲያስተጋቡ ሁለቱ ንቅናቄዎች መካከል ክፍተት እንደተፈጠረ ፕ/ር ደቢ ጊንግ ትናገራለች።
ፕ/ር ደቢ ማኖስፌር ላይ ጥናት አድርጋለች።
ዋረን ፋረል የፌምኒስቶች ጥያቄ እኩልነት ሳይሆን ኃያልነት ነው ማለቱ በርካታ ወንድ ተከታዮች እንዲያገኝ አስችሎታል። 'ሜንስ ሊበሬሽን ሙቭመንት' ሲል የጀመረው ንቅናቄ ከፌምኒዝም በተቃራኒው የቆመ ሆኖም ተገኝቷል።
በ1990ዎቹ የጻፋቸው መጻሕፍት ወንዶች ተጨቁነዋል፣ የቤት ውስጥ ጥቃት በሴቶችና በወንዶች ላይም ይደርሳል፣ የወንዶችና የሴቶች እኩል ተከፋይነት ያልተረጋገጠው በሴቶች ምክንያት ነው የሚሉ ይዘቶች አሏቸው።
እነዚህ ይዘቶች ናቸው በበይረ መረብ ላይ ለማኖስፌር መነሻ የሆኑት።
በ1990ዎቹ ኢንተርኔት እየተስፋፋ ሲሄድ የወንዶች መብት ተሟጋቾች የበይነ መረብ ገጾች በመክፈት መገናኘት ጀምረዋል።
መጀመሪያ ላይ እነዚህ የበይነ መረብ ቡድኖች እምብዛም መርዛማ አልነበሩም።
የፍቅር ጓደኛ ፈልጋ ማግኘት ያልቻለች የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሴት የበይነ መረብ ቡድን ፈጥራ ነበር። ያለፈቃዳቸው ከፍቅር ግንኙነት ውጭ የሆኑ ሰዎች (involuntary celibates ወይም incels) የሚነጋገሩበት ነበር።
ገጹን እአአ በ2018 የከፈተችው ተማሪ ለቢቢሲ እንዳለችው፣ ገጹ ለሁሉም ሰዎች ክፍት ነበር። ሆኖም ግን ብዙም ሳይቆይ በገጹ ፆተኛ ምልከታዎች ይሰነዘሩ ጀመር።
የፍቅር ጓደኛ ከማጣት ጋር በተያያዘ ያለውን ፈተና ለመወያየት የተከፈተውን ገጽ በመጠቀም ወንዶች ሴቶችን ለመውቀስና ለማጠልሸት ተጠቅመውበታል።
ወንዶች ሴቶችን 'ለመማረክ' መጠቀም ያለባቸውን መንገድ መነጋገር ጀመሩ። ራሳቸውን Alphas በማለት ወንድነታቸውን እንደ ሀይል መቁጠርም ቀጠሉ።
ዶ/ር ሊሳ ሱጊራ የበይነ መረብ ወንጀል ባለሙያ ናት። በማኖስፌር ታሪክ ላይ መጽሐፍ አሳትማለች።
እነዚህ ድረ ገጾች በጊዜ ሒደት ፆተኛ መሆናቸውን ትናገራለች።
"መጀመሪያ ላይ ሴቶችን ማግኛ መንገዶችን ይወያዩ ነበር። ይሄ ደግሞ ሴቶች በራሳቸው ላይ የመወሰን መብታቸውን የሚገፍ ነው። ሴቶችን እምቢ የማለት መብታቸውንም ይነጥቃል" ትላለች ባለሙያዋ።
በፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ሬዲትና ሌሎችም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መረጃ በመለዋወጥ ማኖስፌር እየተስፋፋና ሥር እየሰደደ መጥቷል።
ወንዶች ፍቅረኛ የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ እንደሆነ በእነዚህ ገጾች ላይ ይነገራል።
'አዶለሰንስ' ፊልምም የሚያሳየው ይሄንን ነው።
80% ሴቶች 20% ወንዶች እንደሚማርኳቸው በእነዚህ ገጾች ላይ ይስተጋባል።
ይህም "80/20 rule [ህግ]" በሚል ይታወቃል።
ይህ አስተሳሰብ መነሻውን ያደረገው በተዛባ ምልከታና ዳሰሳ ላይ ነው።
ፕ/ር ደቢ እንደምትለው፣ እነዚህ ገጾች ፀረ-ፌምኒዝም በማድረግ አደገኛ አካሄድ ጀምረዋል።
"ሴቶች ማለፍ የማይችሉት ድንበር አለ የሚል የተዛባ ምልከታን ያስተጋባሉ" ስትል ታስረዳለች።
እአአ በ2014 የማኖስፌር ገጾች ሴቶች ላይ የጥላቻና ማስፈራሪያ ዘመቻ ከፍተዋል። ጌም መጫወቻና ሌሎችም የበይነ መረብ ገጾች ላይ የነበረው ዛቻ ወደ ገሀዱ ዓለም ተሸጋግሮ ሴቶች ላይ አካላዊ ጥቃት ማድረስ ጀምረዋል።
በካሊፎርያ የ22 ዓመት ወጣት ሴቶች "አልፈልግህም ብለውኛል" በሚልና "ሴቶችን ለመቅጣት" ሲል ስድስት ሰዎችን ገድሎ 14 ሰዎችን አቁስሏል።
የበይነ መረብ ገጾቹ እያደረሱ ያሉት ጉዳት በገሃድ የታየበት ትልቅ ክስተት ነበር።
ዶ/ር ሊሳ እንደምትለው፣ እነዚህ ጥቃቶች የበይነ መረብ ገጾቹ የበለጠ እየተጠናከሩ እንዲሄዱ አድርገዋል።
"ሴቶች ሲገደሉ በእነዚህ ገጾች ደስታቸውን ይገልጻሉ" ትላለች ዶ/ር ሊሳ።
ፆተኛው አንድሪው ቴት በእነዚህ ገጾች የሚዘዋወሩ መረጃዎችን በአጭር ቀንጭቦ በማጋራት ተቀባይነታቸው እንዲጨምር አድርጓል። ግለሰቡ በዩናይትድ ኪንግደም በወሲባዊ ጥቃት ተከሷል።
በማኖስፌር ላይ የሚዘዋወሩ መልዕክቶችን ከአካል ብቃት እንቅስቃሴና የግል ጤና አጠባበቅ ጋር በማስተሳሰር ለመግፋት ይሞከራል።
ውስብስብ ለሆኑ ጉዳዩች ቀላል መፍትሔ በማቅረብ ምርቶች የሚሸጡባቸውም ገጾች ናቸው።
ዶ/ር ሊሳ እንደምትለው፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እነዚህን መርዛማ ምልከታዎች በርካቶች ጋር የሚደርሱት በዚህ መንገድ ነው።
"ማኖስፌር ፆተኛና ሴቶች-ጠል ብቻ አይደለም። ራስን ማሻሻያ እና ራስን መገንቢያ መንገድ ሆኖ ነው የሚቀርበው" ስትል ታስረዳለች።
ማኅበራዊ ትስስር ለሌላቸው ወንዶች እንደ መገናኛ ሆኖ በማገልገል "ወንድ መምሰል ያለበት ይሄንን ነው" የሚል አደገኛ መልዕክት ያስተላልፋል።
ስለ ብቸኝነት፣ ስለ ድባቴ እና ስለ ጭንቀት የሚያወሩበት ቦታ ያጡ ወንዶች ወደእነዚህ ቡድኖች እንዲቀላቀሉም ይገፋፋል።
'አዶለሰንስ' ፊልምን የጻፈው ጃክ ቶርን ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ የፊልሙ ማጠንጠኛ ወንድነትን ማዕከል አድርገው መረጃ የሚገፉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው።
በተለይም ታዳጊ ወንዶች የዚህ መረብ ዒላማ ናቸው። የፊልሙን ዋና ገጸ ባህሪ እንደምሳሌ በመጥቀስም ጸሐፊው ፊልሙን እንዲህ ይገልጻል።
"ወላጆቹ አልተረዱትም። የትምህርት ሥርዓቱ አልደረፈውም። የሚከታተለውን መረጃ የትምህርት ሥርዓቱ አላወቀለትም። ቤተሰቡ እንደማንኛውም ቤተሰብ ነው። ሕይወቱም ከአብዛኞቻችን እውነታ የተለየ አይደለም። ነገሩን የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገውም ይሄ ነው። ማንኛችንም ላይ ሊከሰት የሚችል መሆኑ ያሰጋል።"