ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሴቶች ላይ መካንነትን የሚያስከትለው ሊታከም የሚችለው ከብልት ባክቴሪያ መጠን ጋር የተያያዘው ቢቪ ምንድን ነው?
በእንግሊዝኛው ባክቴርያል ቫጅኖሲስ ወይም ቢቪ በሚል የሚታወቀው የጤና ሁኔታ በዓለም አንድ ሦሰተኛ ያህል ሴቶች ይገጥማቸዋል።
የዩናይትድ ኪንግድም ብሔራዊ የጤና አገልግሎት እንደሚለው ቢቪ የሚከሰተው በሴቶች የመራቢያ አካል ውስጥ ያለው ተፈጥሯዊ የባክቴሪያ መጠን ሲለወጥ ነው።
በግብረ ሥጋ ግንኙነት ምክንያት ቢቪ ሊቀሰቀስ ቢችልም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ውስጥ አይካተተም።
ቢቪ ሴቶች መካን እንዲሆኑ ወይም ልጆች ያለ ጊዜያቸው ቀድመው እንዲወለዱ ከማድረጉ በተጨማሪ ለጨቅላ ሕጻናት ሞት መንስዔም እንደሚሆን የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ቢቪ ሊስፋፋ ይችላል።
በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜድስን ላይ የታተመው እና በአውስትራሊያ የተሠራው ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ኢንፌክሽኑን ለማጥፋት መታከም ያለባት ቢቪ የተያዘች ሴት ብቻ ሳትሆን የወሲብ አጋሯም ጭምር ነው።
ቢቪ ከተለመደው ውጪ የሆነና ጠረን ያለው ፈሳሽ ከብልት እንዲወጣ ያደርጋል።
ቀለሙ ሊለዋወጥ ይችላል። አንዳንዴ ግራጫ ወይም ነጭ ሲሆን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀጭን ውሃ መሰል ፈሳሽ ይሆናል።
ቢቪ ካለባቸው ሴቶች ግማሹ ምልክት አያሳዩም። የብልት ህመም ወይም ማሳከክ አያስከትልም።
አንቲባዮቲክስ በመውሰድ አልያም በጄል ወይም በክሪም ይድናል።
አውስትራሊያ በተደረገው ምርምር 164 ቢቪ ያለባቸው ጥንዶች ተሳትፈዋል።
ተመራማሪዎቹ ቢቪን በወሲብ እንደሚተላለፍ በሽታ በመውሰድ ለሴቶች ብቻ አንቲባዮቲክስ ከመስጠት ይልቅ ሁለቱንም ጥንዶች ሲያክሙ የተሻለ ውጤት አግኝተዋል።
ከተመራማሪዎቹ አንደኛዋ ፕሮፌሰር ካትሪዮና ብራድሻው "ከወሲብ አጋር ጋር በሚኖር ግንኙነት በድጋሚ ቢቪ በሴቶች ላይ ሊከሰት እንደሚችል ጥናታችን ያሳያል።
"ይህም ቢቪ በወሲብ የሚተላለፍ በሽታ እንደሆነ ይጠቁማል" ብለዋል።
"ቢቪ በወሲብ የሚተላለፍ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመወሰን አስቸጋሪ የሚሆነው የትኛው ባክቴርያ ቢቪን እንደሚያስከትል ባለመታወቁ ነው። የዘረ መል ምርምር መቀጠላችን ግን የትኛው ባክቴሪያ ቢቪን እንደሚያስከትል እንድናውቅ ይረዳናል" ሲሉም አክለዋል።
ጥናቱ የተሠራው በሞናሽ ዩኒቨርስቲ፣ ሜልበርን ሴክሽዋል ኸልዝ ሴንተር እና በአልፍሬድ ኸልዝ ተመራማሪዎች ነው።
በምርምሩ ወቅት ግማሾቹ ወንዶች የሚዋጥ አንቲባዩቲክ እና ቆዳ ላይ የሚቀባ አንቲባዮቲክ ቅባት ተሰጥቷቸዋል። ምንም ሕክምና ካልተሰጣቸው ወንዶች ጋርም ውጤታቸው ተነጻጽሯል።
ዘ ብሪትሽ አሶሴሽን ፎር ሴክሽዋል ኸልዝ ኤንድ ኤችአይቪ እንዳለው በዚህ ጥናት የተገኘው ውጤት ጠቃሚ ነው።
"ከቢቪ ጋር የሚያያዘው ባክቴሪያ በወሲብ የሚተላለፍ መሆኑን ቀድሞም እንገምት ነበር። ጥናቱ ይህንን አረጋግጦልናል" ብሏል ተቋሙ።
ጥናቱ ስለ ቢቪ ያለውን ዕውቀት ያሰፋ እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል። ለሕክምና የሚውሉ መንገዶችን በተሻለ መንገድ ያሳየም ነው ሲል አክሏል።