በሂሮሽማ የአቶሚክ ቦምብ የተጣለበት 80ኛ ዓመት ተዘከረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በጃፓኗ ሂሮሽማ ከተማ ላይ አቶሚክ ቦምብ የጣለችበትን 80 ዓመት ለማስታወስ ረቡዕ፣ ሐምሌ 30/ 2017 ዓ.ም የጸሎት ስነ ስርዓት ተካሄደ።
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺገሩ ኢሺባ ከዓለም ዙሪያ ከተሰባሰቡ ባለስልጣናት ጋር በመሆን በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
የሂሮሺማ ከንቲባ ካዙሚ ማትሱይ፤ በከተማዋ በሚገኘው የሰላም መታሰቢያ ፓርክ ባደረጉት ንግግር፤ "በጦርነት ወቅት የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የደረሰባት ብቸኛዋ ሀገር ጃፓን ናት" ብለዋል።
"የጃፓን መንግስት እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላም የሚፈልግ ህዝብን ይወክላል" ሲሉም ተደምጠዋል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀው ጃፓን በቀናት ልዩነት በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ ከተጣሉባት ቦምቦች በኋላ እጅ በመስጠቷ ነው።
የአሜሪካ ቦምቦች ከ200,000 በላይ ሰዎችን የገደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ በፍንዳታው ሌሎች ደግሞ በጨረር በሽታ እና ቃጠሎ ሞተዋል።
የጦር መሳሪያ መዘዝ ዛሬም ላይም በህይወት የተረፉ ጃፓናያውያንን እረፍት የሚነሳ ጉዳይ ነው።
ከሂሮሺማው ጥቃት የተረፈው ሺንጎ ናይቶ፤ "አባቴ በጥቃቱ ክፉኛ ተቃጥሎ እና ታውሮ ነበር። ቆዳው ሰውነቱ ላይ ተንጠልጥሎ ነበር፤ እጄን እንኳ መያዝ አልቻለም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል። አባቱን እና ሁለት ታናናሽ ወንድሞቹን የገደለው ቦንብ በከተማው ላይ ሲጣል የስድስት ዓመት ልጅ ነበር።
ናይቶ ይህንን አስከፊ ታሪኩን ወደ ስነ ጥበብ ስራዎች እየቀየሩ ላሉ የሂሮሽማ ተማሪዎች ሲያካፍል ቆይቷል።
"ኒሆን ሂዳንኪዮ" የተባለው እና የጃፓን ከአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉ ሰዎች ቡድን ከኒውክሌር መሳሪያዎች ከዓለም ለማስወገድ ላደረገው ጥረት በ2024 የኖቤል የሰላም ሽልማትን አግኝቷል።
የሂሮሺማ ከንቲባ ማትሱይ ረቡዕ ዕለት ባደረጉት ንግግር፤ "በዓለም ዙሪያ ወታደራዊ ግንባታ እየተፋጠነ መምጣቱን" እና "የኒውክሌር መሳሪያዎች ለአገር መከላከያ አስፈላጊ ናቸው የሚለውን ሃሳብ" በማንሳት አስጠንቅቀዋል።
"እነዚህ ለውጦች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከአሳዛኝ የታሪክ ክስተቶች መማር የነበረበትን ትምህርት በግልጽ ችላ ያሉ ናቸው ብለዋል" ብለዋል። "ብዙዎች ለመገንባት የለፉባቸውን የሰላም ግንባታ ማዕቀፎች እንዳያፈርሱ ያሰጋል" ሲሉም አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ስርጭትን ለመከላከል እና የኒውክሌር ኃይል ሰላማዊ አጠቃቀምን ለማዳበር ያለመዉን የኒውክሌር አለማስፋፋት ስምምነት፤ "ጥቅም አልባ ሊሆን አፋፍ ላይ" መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የጃፓን መንግሥት፤ በ2021 ተግባራዊ የሆነውን የኑክሌር መሳሪያዎችን የሚከለክል ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲያጸድቅ ጥሪ አቅርበዋል።
ከ70 በላይ ሀገራት ስምምነቱን ቢያፀድቁም እንደ አሜሪካ እና ሩሲያ ያሉ ሀገራት የኒውክሌር መሳሪያ መኖር ይህንን አይነቱን ጥቃት ያስቀራል በማለት ተቃውመውታል።
ጃፓንም በአሜሪካ የኒውክሌር መሳሪያዎች የተነሳ ደህንነቷ መጠናከሩን በማንሳት እገዳውን ውድቅ አድርጋለች።
ጃፓን ውስጥ የኒውክሌር ብዙዎችን የሚከፋፈል ጉዳይ ነው። ወደ ሰላም መታሰቢያው ፓርክ በሚወስዱ ጎዳናዎች ላይ የኒውክሌር መሳሪያ እንዲወገድ የሚጠይቁ አነስተኛ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ከጨረር ጋር በተያያዘ በበርካታ የካንሰር በሽታዎች የተሰቃየው ሌላኛው የአቶሚክ ቦምብ ተጠቂ ሳይቶሺ ታናካ፤ በአሁኑ ወቅት በጋዛ እና በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ደም መፋሰስ መመልከት የራሱን ስቃይ እንደሚያስታውሰው ገልጿል።
"የፍርስራሽ ክምሮች፣ የወደሙ ከተሞች፣ በፍርሃት የተዋጡ ህጻናት እና ሴቶች ሲሸሹ ማየቴ ያለፍኩባቸውን ነገሮች ያስታውሰኛል" በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል። "የሰው ዘር ብዙ ደጋግሞ ሊያጠፋ ከሚችል የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ጋር አብረን እየኖርን ነው" ሲልም አክሏል።
"በአስቸኳይ ቅድሚያ የሚሰጠው፤ የኑክሌር የጦር መሳሪያ ባለቤት የሆኑትን ሃገራት መሪዎች ላይ ግፊት የማድረግ ጉዳይ ነው። የዓለም ህዝብ የበለጠ መበሳጨት፣ ድምፁን ከፍ ማድረግ እና ከፍተኛ እርምጃ መውሰድ አለበት" በማለት ተናግሯል።














