የተቃጠለ የሰው ጀርባን፣ የወደመ ሕንጻን እና በቦምብ ፍንዳታ የሚፈጠረውን ጭስ የሚያሳይ ፎቶ

ከሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ጥቃት 80 ዓመታት በኋላ፡ የአውቶሚክ ቦምብ ሳይንስ እና በሰው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት

ማስጠንቀቂያ፡ ዘገባው የሚረብሹ ምሥሎች እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ዝርዝር ይዟል

"ሰማኒያ ዓመታት ቢያልፉም፣ ምንም የተቀየረ ነገር የለም።"

ይህ በአውሮፓውያኑ 1945 አሜሪካ በሁለት የጃፓን ከተሞች ላይ የፈጸመቻቸውን ጥቃቶች በተመለከተ ከናጋሳኪው ጥቃት የተረፈ ግለሰብ ስሜቱን የገለጸበት መንገድ ነው።

ማሳኮ ዋዳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ከእኛ ተሞክሮ ምንም ትምህርት አልተወሰደም፤ ስለዚህም ካለፉት ጊዜያት በበለጠ ዛሬ አደጋ ላይ ነን።" በአውሮፓውያኑ 2024 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያገኘው ከአውቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉ ሰዎች ማኅበር የሆነው የኒሆን ሂዳንኪዮ ረዳት ዋና ፀሐፊ የሆኑት የፀረ ኒውክሌር ጦር መሳሪያ አቀንቃኙ ዋዳ እንደ እሳቸው ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ምስክርነት ጆሮ እንዲያገኝ ይሟገታሉ።

በሂሮሺማ ላይ ቦምቡ ሲጣል የስድስት ዓመት ልጅ የነበሩት ቶሺዮ ታናካ እሳቸውም የዋዳ ስጋትን ይጋራሉ።

እንደ ዩክሬን እና መካከለኛው ምሥራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚካሄዱት ግጭቶች የኒውክሌር ጦርነት ስጋትን የሚያስቀጥሉ ናቸው በማለት ያለውን ሁኔታ “በጣም አሳሳቢ ነው” ብለዋል።

በጃፓን ከተሞች ላይ የተፈፀሙት ጥቃቶች 80ኛ ዓመት ሊታሰብ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ታናካ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "በዚህ የጦርነት መንገድ ከቀጠልን ወደ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ልናመራ እና የዓለም ፍጻሜ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

አሜሪካ በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ የአውቶሚክ ቦምቦችን ለመጠቀም ያሳለፈችው ውሳኔ አስከ ዛሬም ድረስ አከራካሪ ነው።

undefined
ጌቲጌቲ

አንዳንድ ተንታኞች ቦምቡን መጠቀም የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ለማብቃት እና የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ አስፈላጊ እርምጃ ነበር ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ሰዎችን የገደለ እጅግ በጣም ኢ-ሞራላዊ ድርጊት እና አላስፈላጊ እርምጃ ነው ብለው ይከራከራሉ።

አከራካሪ ያልሆነው ነገር ግን የአውቶሚክ ቦምቦቹ ጥቃቶች ያደረሱት ዘላቂ ተጽእኖ ነው።

ይህ በዓለም ታሪክ ብቸኞቹ የኒውክሌር ቦምብ ጥቃቶች ያደረሱት እልቂት እና አስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀው ያስከተሉት ጉዳትን የሚቃኝ ዘገባ ነው።

ከጥቃቱ በፊት ሂሮሺማን የሚያሳይ ከአየር ላይ የተነሳ ፎቶ

ሂሮሺማ

የሂሮሺማ ከተማን የሚያሳይ ካርታ

እኤአ ታኅሣሥ 7/1941 ጃፓን በሃዋይ ደሴቶች ላይ በሚገኘው ፐርል ሃርበር በተባለው የአሜሪካ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ የፈጸመችውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እስከ 1945 ክረምት ድረስ አሜሪካ ከጃፓን ጋር ለሦስት ዓመት ተኩል በዘለቀ ጦርነት ውስጥ ነበረች።

በጦርነቱ ተሳታፊ ያልበረችው አሜሪካ በተፈጸመባት ጥቃት ምክንያት በጃፓን ላይ ጦርነት እንድታውጅ እና ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንድትገባ ምክንያት ሆኗታል።

ጦርነቱ እየተባባሰ ሲሄድ አሜሪካ በጃፓን ላይ የአውቶሚክ ቦምቦችን ለመጠቀም ወሰነች።

በሐምሌ 26/1945 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማን ጃፓን “ያለ ቅድመ ሁኔታ እጅ እንድትሰጥ” ይህ ካልሆነ ግን “ፈጣን እና ፍፁም ውድመት” እንደሚጠብቃት ማስጠንቀቂያ አወጡ።

ነገር ግን የትሩማን ማስጠንቀቂያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ስለመጠቀም ምንም ያለው ነገር አልነበረም።

ይሁን እንጂ እነዚህ የአውቶሚክ ቦምቦች አሜሪካ ጦርነቱን ለማብቃት በያዘችው ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት የጦር መሳሪያዎች ውስጥ ነበሩ።

የሊትል ቦይ ቦምብ የተለያዩ ክፍሎችን የሚያሳይ ሥዕል

የመጀመሪያዋ ኢላማ ከዚህ ቀደም በተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶች ያልተነካችው እና የጃፓን የጦር ሰፈር የነበረባት ሂሮሺማ ከተማ ነበረች። ብዙ ባለሙያዎች እንደሚሉት ሂሮሺማ የቦምቡ አጥፊ ኃይል ማሳያ የሙከራ ስፍራ ሆነች።

በኮሎኔል ፖል ቲቤትስ የሚበረው ኢኖላ ጌይ የተባለው ቢ-29 ቦምብ ጣይ አውሮፕ ነበር ወደ ሂሮሺማ የተላከው። አውሮፕላኑ በከተማዋ ሰማይ ላይ በ9.5 ኪሎ ሜትር ከፍታ በመብረር 'ሊትል ቦይ' የሚል ስያሜ የተሰጠውን ዩራኒየም-235 ቦምብ ከመሬት በ600 ሜትር ከፍታ በአየር ላይ አፈነዳው።

"ጠዋት 2:15 ላይ ወደ ትምህርት ቤት እየሄድኩ ሳለ አንድ ሰው 'የጠላት ቦምብ ጣይ!' በማለት ጮኸ" ሲል ቶሺዮ ታናካ ያስታውሳል። "ወደ ሰማይ ቀና ብዬ ስመለከት ግዙፍ ብልጭታ አየሁ፣ አንድ ሚሊዮን መብራቶች ነበር የሚመስለው፣ ከዚያ ሁሉም ነገር ነጭ ሆነ።"

የሊትል ቦይ ቦምብ ውስጣዊ አሠራር ልክ እንደ ሽጉጥ የተዘጋጀ ሲሆን፣ አንድ ነጠላ ዩራኒየም 235 በሌሎች ተመሳሳይ ይዘት ላይ በመተኮስ የሚሠራ ነው።

እነዚህ ይዘቶች ሲጋጩ፣ የአተሞቹ ማዕከላዊ ክፍል እርስ በርስ እየተቀጣጠሉ በመከፋፈል ከፍተኛ ኃይል ይፈጥራሉ።

ይህ ኃይልም እርስ በርሱ እየተባዛ ኃይል በመሆን ፍንዳታ እንዲፈጠር ያደርጋል።

ሊትል ቦይ 64 ኪሎ ግራም የሚመዝን ዩራኒየም 235 ያለው ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 1.5% ብቻ ነው የሚከፋፈለው።

ነገር ግን ፍንዳታው ከ15 ሺህ ቶን ቲኤንቲ ጋር የሚመጣጠን ጉልበት አለው።

ለማነጻጸር አንድ ኪሎ ግራም ቲኤንቲ አንድ መኪናን ለማውደም የሚሆን በቂ አቅም አለው።

በሂሮሺማ ላይ የአውቶሚክ ቦምብ ሲፈነዳ

ፍንዳታው በ4.5 ኪሜ ርቀት ውስጥ ባሉ ቦታዎች ላይ ከ4 ሺህ ሴሊሺየስ በላይ መጠን ያለው ከባድ ሙቀት ፈጥሯል።

"ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት የተቃጠለ ልብሳቸው ላያቸው ላይ ተበጣጥሶ ከሞላ ጎደል ራቁታቸውን ነበሩ። የተቃጠለው ቆዳቸው በጣታቸው ጫፍ ላይ ተንጠልጥሎ እጃቸውን ዘርግተው በፀጥታ ይራመዱ ነበር" ሲሉ ታናካ ያስታውሳል።

"መናፍስት ወይም የሚንቀሳቀሱ በድኖች ነበር የሚመስሉት።"

በተፈጸመው የአውቶሚክ ቦምብ ፍንዳታ ከ50 ሺህ አስከ 100 ሺህ ሰዎች በዕለቱ መሞታቸው ይገመታል።

undefined

በከተማዋ ከነበሩ ሕንጻዎች መካከል ሁለት ሦስተኛው ወይም 60 ሺህ የሚደርሱት ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።

የወደመችው የሂሮሺማ ከተማ የአየር ላይ ምሥል
ወታደሮች በሂሮሺማ ላይ የደረሰውን ውድመት ሲመለከቱ
በሂሮሺማ ከወደመ ሕንጻ ፊት ለፊት የቆመ ሰው

ነገር ግን ጃፓን እጇን አልሰጠችም።


ከሦስት ቀናት በኋላ ደግሞ አሜሪካ ሁለተኛውን ቦምብ ጣለች።

የናጋሳኪ ከተማን ከአየር ላይ የሚያሳይ ፎቶ

ናጋሳኪ

ናጋሳኪ እና ኮኩራ ከተሞችን የሚያመለክት ካርታ

በመጀመሪያ ላይ ናጋሳኪ ለሁለተኛው ዙር የአውቶሚክ ቦምብ ጥቃት ከተመረጡ ቀዳሚ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ አልነበረችም።

ባላት ወጣ ገባ መልክዓ ምድር እና የሕብረቱ ኃይሎች የጦር እስረኞች ካሉበት ካምፕ ጋር ካላት ቅርበት የተነሳ ናጋሳኪ በቀዳሚነት ከተለዩት ዒላማዎች ውስጥ አልነበረችም።

ቀዳሚ ዒላማ ከተደረጉት መካከል በአንፃራዊነት ሜዳማ አቀማመጥ ያላት የኢንዱስትሪ ከተማዋ ኮኩራ ትገኝበት ነበር።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ቀን ግን የኮኩራ ከተማ ሰማይ በጭስ እና በጭጋግ ተሸፍኖ እንደነበር የቦምብ ጣይ አውሮፕላኑ አብራሪዎች አስታውቀዋል።

ከዚያም የቦምቡን የጥፋት አቅም ከፍ የሚያደርግ አማራጭ ዒላማ ከአየር ላይ በሚኖራቸው ዕይታ እንዲመርጡ ለአብራሪዎቹ ትዕዛዝ ተሰጠ።

እነሱም ፊታቸውን ወደ ናጋሳኪ አዞሩ።

በካፒቴን ቻርለስ ስዊኒይ የሚበረው ቦክስካር የተባለው ቢ-29 ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ፋት ማን የሚል ስያሜ የተሰጠውን አውቶሚክ ቦምብ ከመሬት 500 ሜትር ከፍታ ላይ ናጋሳኪ ከተማ ላይ አፈነዳው።

የፋት ማን ቦምብን የተለያዩ ክፍሎች የሚያሳይ ሥዕል

ቦምቡ የተሠራው በፕሉቶኒየም-239 ነበር።

ምንም እንኳን ፕሉቶኒየም-239 ከዩራኒየም-235 ይልቅ ማግኘት ቀላል ቢሆንም፣ ቦምቡ በውስጡ የያዘው በጣም ያነሰ መጠን ነው። ፋት ማን ቦምብ ከሊትል ቦይ ቦምብ የበለጠ ውስብስብ ሥርዓትን የሚፈልግ ነው።

ፕሉቶኒየም-239 የተጣራ ባለመሆኑ ቦምቡ ቀድሞ ሊቀጣጠል እና የማውደም አቅሙን ሊቀንሰው ይችላል።

ድንገተኛ መቀጣጣል ከመከሰቱ በፊትም ቦምቡን ለማፈንዳት ውስጣዊ ፍንዳታ እንዲፈጠር የሚያደርግ ዘዴ ጥቅም ላይ ውሏል።

ቦምቡ በውስጡ 6ኪግ የሚመዝን ፕሉቶኒየም ያያዘ ቢሆንም፣ 1ኪግ የሚሆነው ብቻ ነው የተቀጣጠለው።

ይህም ከ21 ሺህ ቶን ቲኤንቲ ጋር የሚመጣጠን ኃይል ለማውጣት በቂ ነበር።

የናጋሳኪ ቦምብ ፍንዳታ ቪዲዮ

ጥቃቱ የተፈጸመበትን 70ኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት ከናጋሳኪው አውቶሚክ ቦምብ የተረፉት ሱሚቴሩ ታኒጉቺ "የሰው አካል በቃጠሎ ጠቁሯል፣ ከፈራረሱ ሕንፃዎች እርዳታ የሚጠይቁ ድምፆች፣ ሥጋ ከአካላቸው ላይ የሚወድቅ እና ሆድ እቃቸው የተዘረገፈ ሰዎች በየቦታው ነበሩ። ይህ ቦታ የእሳት ባሕር፣ ሲኦል ሆኖ ነበረ" ሲሉ አስታውሰዋል።

ፍንዳታው በሂሮሺማ ከደረሰው የበለጠ ከፍተኛ ነበረ፤ ነገር ግን የናጋሳኪ ተራራማ አቀማመጥ እና በሁለት ሸለቆዎች መካከል መገኛቷ ውድመቱ የደረሰበትን አካባቢ ስፋትን ገድቦታል።

በናጋሳኪ የደረሰውን ውድመት የቦታ ስፋት የሚያሳይ ካርታ

ቦምቡ በናጋሳኪ ውስጥ 7.7 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን አካባቢን የወደመ ሲሆን፣ በዚህም 40% የከተማዋ ክፍል ፈራርሷል።

ከናጋሳኪው ጥቃት የተረፉት እና የኒሆን ሂዳንኪዮ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ቴሩሚ ታናካ በ2024 የኖቤል ሽልማት ንግግራቸው ላይ “በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሰቃዩ ነበር፣ ምንም ዓይነት የሕክምና ድጋፍ ሊደረግላቸው አልቻለም” ሲሉ አስታውሰዋል።

"በጦርነት ውስጥ እንኳን ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ ግድያ እና አካል ማጉደል ፈጽሞ ሊፈቀድ እንደማይገባ በጽኑ አምናለሁ።"

ቦምቡ ከተፈነዳ በኋላ በናጋሳኪ ላይ የደረሰውን ውድመት የሚያሳይ የአየር ምሥል
በናጋሳኪው የቦምብ ጥቃት የፈረሰ ሕንጻ
ሃውልቶች በናጋሳኪ ፍርስራሾች ውስጥ

በሁለቱ የአውቶሚክ ቦምብ ጥቃቶች ምክንያት እና ፈንዳታውን ተከትሎ ወዲያውኑ ወይም በቀጣዮቹ ወራት በአካል ጉዳት እና በጨረር ተፅእኖ ምክንያት የሞቱ ሰዎች አጠቃላይ ትክክለኛ ቁጥር የለም።

በዝቅተኛ ግምቶች መሠረት በአውቶሚክ ቦምቦቹ ጥቃቶች ምክንያት በሁለቱም ከተሞች በታኅሣሥ 1945 የሟቾች ቁጥር ወደ 110,000 አካባቢ ደርሶ ነበር።

ሌሎች ጥናቶች እንደሚያሳዩት አጠቃላይ የተጎጂዎች ቁጥር በዓመቱ መጨረሻ ላይ ከ210 ሺህ ሊበልጥ እንደሚችል አመልክተዋል።

የጃፓንን እጅ መስጠት ስምምነት ሲፈረም የሚያሳይ ምሥል

ቶኪዮ

ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በአውቶሚክ ቦምብ መመታታቸውን ተከትሎ ጃፓን እጅ መስጠቷን አስታወቀች።

ነሐሴ 15/1945 የጃፓኑ ንጉሥ ሂሮሂቶ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር፣ ጃፓናውያን "የማይቻለውን ችለው" ሽንፈታቸውን እንዲቀበሉ ጠይቀዋል።

ይፋዊው የጃፓን እጅ መስጠት ስምምነት የተፈረመው መስከረም 2/1945 በቶኪዮ የባሕር ዳርቻ ላይ ቆማ በነበረችው በአሜሪካዋ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ሚሱሪ ላይ ነበር።

በዚህም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ሆነ።

የቦምቡ አሰቃቂ ውጤት

ከፍንዳታው በኋላ በሚኖር የሰከንድ ሽራፊ ውስጥ ከአውቶሚክ ቦምቡ ጋማ ጨረሮች፣ ኒውትሮኖች እና ጨረሮች ወጥተው እስከ 3 ኪሎ ሜትር የሚጓዙ የማይታዩ ቅንጣቶች የሰውን አካል ጨምሮ ያገኙትን ነገር ሁሉ ያወድማሉ።

ለምሳሌ በሂሮሺማ ላይ የተጣለው ቦምብ ከፈነዳበት በ600 ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኙ 92% የሚሆኑ ሰዎችን ገድሏል።

ሂባኩሻ በመባል ከሚታወቁት ከአውቶሚክ ቦምብ ፍንዳታዎቹ የተረፉት ሰዎች በከባድ ሙቀት እና በጨረሮች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ብዙዎቹ ቆዳቸውን ከአካላቸው ላይ የሚገፍ ከባድ ቃጠሎ ደርሶባቸዋል።

በአንዲት ሴት ክንድ ላይ የደረሰ ቃጠሎን የሚያሳይ ፎቶ
ጌቲጌቲ

ለራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር መጋለጥ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ደም መፍሰስ እና የፀጉር መርገፍን ያስከትላል።

ከጊዜ በኋላም አንዳንድ ሰዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ እና አደገኛ ዕጢዎች ይፈጠርባቸዋል።

ከጥቃቱ በኋላ በነበሩት አምስት ዓመታት ውስጥ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ለረጅም ጊዜ የሚዘልቁ የጤና ችግሮች አጋጥሟቸዋል። በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ነዋሪዎች ላይም የደም ካንሰር ክስተት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

አንድ ዶክተር በኒውክሌር ቦምብ ምክንያት የተጎዳ ሕጻንን ቁስል ሲያጸዳ የሚያሳይ ምሥል
ጌቲጌቲ

ከአውቶሚክ ቦምብ ጥቃቱ ከአስር ዓመታት በኋላ በብዙ በሕይወት የተረፉ ሰዎች ላይ የእንቅርት፣ የጡት እና የሳንባ ካንሰር የመከሰቱ ዕድል ከመደበኛው ሁኔታ ከፍ ያለ ነበር።

የሥነ ልቦና ጉዳቱም ቢሆን ከፍተኛ ነበር። ብዙዎቹ ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች በተመለከቱት አሰቃቂ ሁኔታ፣ የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት በማጣታቸው እና በጨረር ምክንያት የሚመጡ በሽታዎች እንዳይከሰቱባቸው በመፍራታቸው ምክንያት ከባድ ሰቆቃ ገጥሟቸዋል።

ጨረር በሰው ላይ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚያስከትላቸው ተጽእኖዎችን የሚያሳይ ምሥል፡ የጡት ካንሰር፣ የሳንባ ካንሰር፣ የታይሮይድ ካንሰር፣ የፀጉር መርገፍ፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ።

ብዙዎች ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ባላቸው አካላዊ ገጽታ እና ተላላፊ በሽታዎችን ይኖርባቸዋል በሚል የተሳሳተ ግምት መድልዎ ደርሶባቸዋል።

ሌሎች ደግሞ ሌሎችን ለመርዳት አልቻልንም ከሚል ጥልቅ የጥፋተኝነት ስሜት ጋር ኖረዋል።

ሕይወት ከአውቶሚክ ቦምብ ጥቃት በኋላ

ከሂሮሺማው ጥቃት የተረፈው የሹንታሮ ሂዳ ፎቶ

"ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ ምናልባትም 10 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን አክሜያለሁ። ከዚያ በኋላ ግን በዶክተርነት ሥራዬ መቀጠል አልፈለግሁም ነበር። ያከምኳቸው ሰዎች እየተከታተሉ ሲሞቱ አይቻለሁ። እኔ ማዳን የቻልኩት አንድም ሰው አልነበረም።"

ሹንታሮ ሂዳ፣ ሂሮሺማ

ከናጋሳኪው ጥቃት የተረፈው የያሱአኪ ያማሺታ ፎቶ

"በሕይወት ከተረፍነው አብዛኞቻችን አሁን ድረስ በአካላዊ እና አእምሯዊ ስቃይ ውስጥ ነን ብዬ አስባለሁ።"

ያሱአኪ ያማሺታ፣ ናጋሳኪ

ከሂሮሺማው ጥቃት የተረፈው የኬይኮ ኦጉራ ፎቶ

"ሁሉም ማለት ይቻላል 'ውሃ' እና 'እርዳኝ' እያሉ ሲጠይቁኝ ነበር። እኔ በፍጥነት የጉድጓድ ውሃ ወዳለበት ቤቴ ገብቼ ውሃ አመጣሁላቸው። አመሰገኑኝ፤ ነገር ግን አንዳንዶቹ ውሃ እየጠጡ ደም እያስታወካቸው ዓይኔ እያየ ይሞቱ ነበር። ጸጸት ተሰማኝ እና በጣም ፈራሁ። ምናልባት እኔ ይሆን የገደልኳቸው? እኔ ነኝ የገደልኳቸው?"

ኬይኮ ኦጉራ፣ ሂሮሺማ

ከሂሮሺማው ጥቃት የተረፈው የቶሺዮ ታናካ ፎቶ

"70 ዓመት ሲሞላኝ ስለዚህ አሰቃቂ ገጠመኝ ብቻ ነበር መናገር የቻልኩት። ከዚያ በፊት በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ስለነበርኩ የሚረዳኝ ያለ አይመስለኝም ነበር።"

ቶሺዮ ታናካ፣ ሂሮሺማ

በአሁኑ ወቅት ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የጃፓን ወሳኝ የኢንዱስትሪ እና የንግድ ከተሞች ናቸው።

በሁለቱም ከተሞች የአውቶሚክ ቦምቦቹ ጥቃት ሰለባዎችን የሚዘክሩ አደባባዮች እና ሙዚየሞች አሏቸው።

ከጥቃቱ ከተረፉት መካከል አንዳንዶቹ የጦርነቱ አሰቃቂ ውጤት እንዳይዘነጋ ታሪካቸውን በመናገር የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች እንዳይስፋፉ የሚቀሰቅሱ አክቲቪስቶች ሆነዋል።

ቴሩሚ ታናካ በኖቤል ሽልማታቸው ወቅት ያደረጉት ንግግር ዋነኛ መልዕክት "የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች በአስቸኳይ እንዲወገዱ" የሚጠይቅ ነበር።

ታናካ የአውቶሚክ ቦምቦችን "ከሰብአዊነት የራቁ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች በመሆናቸው፣ ከሰው ልጆች ጋር አብረው እንዲኖሩ መፍቀድ የለበትም" ሲል ጥሪ አቅርበዋል።

የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ከዓለም እንዲወገዱ ዘመቻ የሚያደርገው ቡድን እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ወደ 12,300 የሚጠጉ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አረሮች ይገኛሉ።

የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረት እና መታጠቅ የአጸፋ ጥቃትን ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋት የታጠቁ አገራት በሌሎች ላይ ጥቃት ከመፈጸም ይታቀባሉ የሚለውን የመከላከያ ፅንሰ-ሀሳብን ከኒውክሌር ቦምቦቹ ጥቃቶች የተረፉት ሰዎች አይቀበሉትም።

ማሳኮ ዋዳ የእንደዚህ ዓይነቱን የውድመት ስጋት አጥብቀው ከሚቃወሙት መካከል አንዱ ናቸው።

"ሰዎችን ለመቆጣጠር እና ለመጉዳት የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን መጠቀም የሚለውን ሀሳብ በፍጹም አልቀበልም" ይላሉ።

"ይህ ማለት የሂሮሺማ እና የናጋሳኪ ዓይነት ክስተቶች እንደገና ሊከሰቱ ይችላሉ ማለት ነው።"

ዋዳ እንደሚሉት ከ100 ሺህ ያነሰ ቁጥር ያላቸው ከአውቶሚክ ቦምቦቹ ጥቃቶች የተረፉ እና ዕድሜያቸው ወደ 90 ዓመት አካባቢ የሚሆኑት በአሁኑ ወቅት በሕይወት አሉ።

"ከመካከላቸውም 10 ሺህ የሚሆኑት በየዓመቱ ይሞታሉ። ስለዚህ በ10 ዓመታት ውስጥ ሁሉም ከዚህ ዓለም ስለሚያልፉ ማንም የሚቀር አይኖርም።"

የዋዳ ጭንቀት ግን ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ህያው ምስክርነት እና ትውስታን ከማጣት በላይ ነው።

"የእኔ ስጋት ከአውቶሚክ ቦምቡ የተረፉት ሰዎች ከዚህ ዓለም ከማለፋቸው በፊት፣ ሌሎች የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሰለባዎች ሊኖር ይችላል የሚል ነው።"

ይህ ጽሑፍ በመጀመሪያ የታተመው በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 6/2020 ሲሆን፣ ለ80ኛው የሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የአውቶሚክ ቦምብ ጥቃት መታሰቢያ አዳዲስ ቃለመጠይቆች ተካተውበት ማሻሻያ ተደርጎበታል።