ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 28 ቢሊዮን ብር ያስገኙት የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች "በሂደት እንዲወጡ" እንደሚፈለግ አስታወቀ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2017 በጀት ዓመት ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ያስገኙት የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ፤ "በሂደት እንዲወጡ" የማድረግ ፍላጎት እንዳለው እና ከአሁን በኋላም ለአዲስ የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ፈቃድ እንደማይሰጥ አስታወቀ።
ተቋሙ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ካገኘው 75.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች የተሰበሰበው ገንዘብ 39 በመቶ ድርሻ እንዳለው ተገልጿል።
ከዚህ ዘርፍ የመጣው ገንዘብ በተቋሙ አጠቃላይ ገቢ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሲሆን ለመደበኛ ተጠቃሚዎች የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ከተገኘው ገቢም የሚበልጥ ነው።
ይህም ቢሆን ግን ተቋሙ ከአሁን በኋላ ለአዲስ የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ፈቃድ እንደማይሰጥ እና ያሉትም "በሂደት እንዲወጡ" የመግፋት ፍላጎት እንዳለው ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይህንን አቋም የያዘው፤ ዳታ ማይኒንግ "ተጨማሪ የሰው ኃይል" ለመቅጠር ስለማያስችል እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀርበው "የኢኮኖሚ መነቃቃት ሊፈጥር በሚችል" ዘርፍ ላይ እንዲሆን ስለሚፈለግ መሆኑን ገልጿል።
መንግሥታዊው የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ግንባታ እና ጅምላ ሽያጭ ተቋም፤ ይህንን ያስታወቀው የ2017 አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅዱን አስመልክቶ ትናንት ሐሙስ፣ ነሐሴ 1/2017 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኃይል ሽያጭ እና ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የተገኘው ገንዘብ 75.4 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የተቋሙ መረጃ ያመለክታል።
የኤሌክትሪክ ኃይል የ2017 ገቢ ካለፈው ዓመት ካገኘው 27 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የ48 ቢሊዮን ብር ገደማ ጭማሪ አለው።በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በውጭ ምንዛሬ ያገኘው 338.7 ሚሊዮን ዶላርም ካለፈው ዓመት 135 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።
ተቋሙ ከሁለት እጥፍ በላይ ገቢው ለማደጉ በምክንያትነት ከተጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የታሪፍ ማሻሻያ መደረጉ ነው። ሌሎች ሁለት ምክንያቶች ደግሞ ተቋሙ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኤሌክትሪክ ኃይል እየሸጠላቸው ካሉ የዳታ ማይኒንግ ተቋማት ጋር የተያያዘ ነው።
"የዳታ ማይኒንግ እና የውጭ የኃይል ሽያጭ ገቢ ማደጉ" እንዲሁም በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ኃይል የሚሸጠው በዶላር መሆኑም በምክንያትነት የተነሱት ጉዳዮች ናቸው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያን ተመራጭ መዳረሻቸው እያደረጉ ያሉት የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች፤ በተለይም የዲጂታል ገንዘብ የሆነው ክሪፕቶ ከረንሲ ዝውውር ወሳኝ አካል ናቸው።
እንደ የቢት ኮይን ባሉ ክሪፕቶ ከረንሲዎች የሚደረጉ ዝውውሮችን ማረጋገጥ (verify) የእነዚህ ኩባንያዎች ተግባር ነው።
ኩባንያዎቹ 'ዳታ ማይኒንግ' ተብሎ የሚጠራውን ይህንን ሂደት ማከናወናቸው፤ በአሁኑ ሰዓት ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ የጨመረውን ቢት ኮይን በክፍያ መልክ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ይህንን ሂደት ለማከናወን የሚጠቀሙት የኮምፒውተር ሥርዓት ግን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠይቅ ነው።
በዚህም ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይልን በአነስተኛ ዋጋ የምታቀርበው ኢትዮጵያ የኩባንያዎቹ መዳረሻ ሆናለች። የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና ሌሎች አስፈላጊ መስፈርቶችን ያሟሉ 25 ዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ኃይል ለማግኘት ስምምነት መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፈው ዓመት የካቲት ላይ አስታውቆ ነበር።
እነዚህ ተቋማት ለሚቀርብላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ክፍያ የሚፈጽሙት በዶላር እንደሆነም ተገልጿል። በ2016 ከዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች የተገኘው ገቢ 27 ሚሊዮን ዶላር ነበር።
በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ከእነዚህ ኩባንያዎች የተገኘው ገቢ ግን በእጅጉ ጨምሮ ተስተውሏል። የኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች የተገኘው ገንዘብ ከተቋሙ የ2017 አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 39 በመቶውን ድርሻ ይይዛል።
ለተጠቃሚዎች የኤሌክትሪክ ኃይልን ከሚያከፋፍለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተገኘው ገቢ 35 በመቶ ድርሻን በመያዝ በሁለተኛ ደረጃነት ተቀምጧል። ለኬንያ እና ጅቡቲ ከቀረበው የኃይል ሽያጭ የተገኘው ገንዘብ ደግሞ 20 በመቶው ድርሻ አለው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሽያጭ ላይ ካዋለው ኃይል ውስጥ 27 በመቶውን ያቀረበው ከፍተኛውን ገቢ ላስገኙለት የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ነው። ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቀረበው ኃይል ደግሞ 60 በመቶ ያህሉ ነው።
ተቋሙ ለዳታ ማይኒንግ ካቀረበው ኃይል ያገኘው ገቢ ከፍተኛ ቢሆንም እነዚህን ኩባንያዎች አሁን ባሉበት ሁኔታ እንዲቀጥሉ የማድረግ ዕቅድ እንደሌላው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ በትናንቱ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
እንደ አሸብር ገለጻ ተቋሙ ለዳታ ማይኒንግ ኃይል ማቅረብ የጀመረው ለሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በሚል "የአጭር ጊዜ ዕቅድ" ይዞ ነው።
"በዳታ ማይኒንግ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ። አንደኛው ከዋጋ ጋር በተገናኘ ነው። ዋጋው በጣም ዝቅተኛ ነው። ተቋማት እዚህ መጥተው እየሠሩ ያሉት ከሌሎች ቦታዎች ተባርረው ነው። ኃይል ይሻማሉ የሚለውም ሌላው ሁለተኛ ስጋት ነው" ብለዋል።
ኩባንያዎቹም ቢሆን "ከተወሰነ ዓመት በኋላ እዚህ እንደማይቆዩ" የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ "ወደ ሌላ ቢዝነስ ይቀይራሉ ወይም ጥለው ይወጣሉ" ሲሉ ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በበኩሉ ከዚህ ቀደም እነዚህም ኩባንያዎች ለመሳብ ሲያቀርብ የነበራቸውን ማበረታቻዎች እያነሳ መሆኑን ገልጸዋል። የክፍያ ተመኑን ለማስተካከል የቦርድ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
"እንደ መንግሥት እየተወሰዱ ያሉ በርካታ ማስተካከያዎች አሉ። ከዚህ በፊት ከቀረጥ ነጻ ነበር የሚያስገቡት፤ እሱ እንዲነሳ ተደርጓል። በገንዘብ ሚኒስቴር የተወሰዱ ማሻሻያዎችም አሉ። የታክስ 'ሆሊደይ' [እፎይታ] ነበራቸው እሱም እንዲነሳ ተደርጓል" በማለት አስረድተዋል።
"አሁን ላይ ዳታ ማይኒንግ [ምዝገባ] ሙሉ ለሙሉ አቁመናል። ተጨማሪ የዳታ ማይኒንግ ውል እየፈጸምን አይደለም" ያሉት ባልቻ፤ የተቋሙ ዕቅድ "የነበሩትን ማስቀጠል" እንደሆነ ገልጸዋል። በሥራ ላይ ያሉትን ኩባንያዎችም ቢሆን "ያለማበረታታት (discourage) ዓላማው" መሆኑን ተናግረዋል።
"[ዕቅዳችን] የነበሩትን ማስቀጠል ነው። የተወሰኑትን ደግሞ ዋጋ በማስተካከል፤ ዓላማችን discourage ማድረግ ነው። ምክንያቱም ዳታ ማይኒንግ ብዙውን ጊዜ ኢነርጂ ብቻ ነው የሚጠቀመው። ተጨማሪ የሰው ኃይል፣ ተጨማሪ ግብአት ስለማይሰጥ" ብለዋል።
"ወደፊት ተጨማሪ ዳታ ማይኒንግ ኦፕሬሽን አይፈቀድም፤ የተቋሙ ፍላጎት ያሉትም በሂደት እንዲወጡ ነው" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኤሌክትሪክ ኃይል፤ ይህንን የሚያደርገው የሚያቀርበው አሌክትሪክ ኃይል "የኢኮኖሚ መነቃቃት ሊፈጥር በሚችል ኢንዱስትሪዎች" ላይ እንዲውል የማድረግ ፍላጎት ስላለው እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህም ቢሆን ግን "ገና እቃ በማስመጣት ሂደት ላይ" ነበሩ የዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች ስላሉ፤ በ2018 በጀት ዓመት ከዚህ ዘርፍ የሚገኘው ገቢ ይጨምራል የሚል ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጀመረው የ2018 በጀት ዓመት ይህንን ገቢውን ወደ 109 ቢሊዮን ብር የማሳደግ ዕቅድ እንዳለው ገልጿል።
የውጭ ምንዛሬ ግኝቱንም ወደ 420 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ እንዳቀደ አስታውቋል።