ስቲንሄዘን: ደቡብ አፍሪካን 'ለማዳን' ቃል የገቡት ግለሰብ

የደቡብ አፍሪካ ተቃዋሚ መሪ ጆን ስቲንሄዘን ፕሬዝዳንት ለመሆን አስፈላጊውን ነገር በሙሉ አሟላለሁ ብለው ያምናሉ።

ይህንን የሚሉት አስቸጋሪውን የዘር ጉዳይ እና የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ የ30 ዓመት የስልጣን ዘመን በመጋፈጥ ነው።

ለደቡብ አፍሪካ ዕድገት ቁልፉ ያለው በፓርቲያቸው ዴሞክራቲክ አሊያንስ (ዲኤ) ዘንድ መሆኑን ላመታት ሲከራከሩ ቆይተዋል።

ፓርቲው ከአሮጌው በአፓርታይድ ፓርላማ ነጭ ሊበራሎች የተመሠረተ ሲሆን ራሱን እንደሊበራል እና የኤኤንሲ አማራጭ አድርጎ የመጣ ነበር።

ስቲንሄዘን በ1990ዎቹ ገደማ ነበር እንደ አክቲቪስት ሆነው በ19 ዓመታቸው ፓርቲውን የተቀላቀሉት።

እአአ በ2020 በሰጡት ቃለ መጠይቅ “ወደ ፖለቲካ ለመግባት የወሰንኩት ደቡብ አፍሪካ ያላት ግዙፍ አቅም በመንግስት እጅ እየወደመ በመሆኑ በመበሳጨቴ ነው” ብለዋል።

ወጣቱ ስቲንሄዘን ፖለቲካ እና ሕግ ለማትናት ዩኒቨርሲቲ ቢመዘገቡም አልተመረቁም። ይህም በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እና በሌሎች ፖለቲከኞች ዘንድ መሳለቂያ አድርጓቸዋል።

ስቲንሄዘን ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር “የገንዘብ ጉዳይ እና የሥራ ጫናዎች” ትምህርቱን እንዲያቋርጡ እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል።

"በዚህ አላፍርም ምክንያቱም ከልጅነቴ ጀምሮ የህዝብ ተወካይ መሆን እንደምፈልግ ስለማውቅ ነው" ብለዋል።

ስቲንሄዘን በእርግጠኝነት ፖለቲከኛ ለመሆን ጥልቅ ምኞት አሳይተዋል። በትውልድ ከተማቸው ደርባን የምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡት በ 22 ዓመታቸው ነው። ይህንም በትንሽ ዕድሜ አባል ከሆኑት አንዱ አድርጓቸዋል።

ከዚህ በመነሳት በፖለቲካው እርከን ከፍ እያሉ ሄዱ። እአአ በ 2010 ከጾታዊ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ኩዋዙሉ-ናታል የዲኤ መሪነታቸውን ለመልቀቅ ተገደዱ።

ባለትዳር የነበሩት ስቲንሄዘን ከፓርቲው ቃል አቀባይ ቴሪ ካስ ቤውሞንት ጋር በፍቅር ግንኙነት ነበራቸውው። ቤውሞንትም ከኩዋዙሉ ናታል የዲኤ አመራር ጋር በትዳር የተሳሰሩ ነበሩ።

የስቲንሄዘን በትዳራቸው ታማኝ አለመሆናቸው በሥራቸው ላይ “ምንም ዓይነት ጉዳት አላመጣም” ሲል የደቡብ አፍሪካው ሜይል እና ጋርዲያን ጋዜጣ ባልደረባ ፓዲ ሃርፐር ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሃርፐር አክለውም ስቲንሂሰን ቤውሞንትን በማግባታቸው ጉዳዩ በተቃዋሚ መሪው ስም ላይ ጠባሳ አንዳይፈጠር አድርጎት ሊሆን ይችላል።

እአአ በ2011 ስልጣን ከለቀቁ ብዙም ሳይቆይ ነበር ስቲንሄዘን በህዝብ እንደራሴነት የተመረጡት። ከሦስት ዓመታት በኋላ የዲኤ ዋና ኃላፊ ሆኑ።

በዚህ ወቅት ፓርቲው ትልቅ ለውጥ ለማምጣት በዝግጅት ላይ ነበር። ዲኤ የነጮችን፣ የእስያ እና ከነጭ እና ከጥቁር የተወለዱትን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሠራ ፓርቲ ነው ተብሎ ለረዥም ጊዜ ይታሰብ ነበር። እነዚህ ህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ከጠቅላላው 18 በመቶውን ብቻ የሚሸፍኑ ናቸው።

ተቀባይነቱን ለማስፋት በመሞከር፣ ዲኤ የመጀመሪያውን ጥቁር መሪ ሾመ።

በግርማ ሞገሱ የሚታወቀው ምሙሲ ማይማኔ ፓርቲውን ወክለው ለፕሬዚዳንትነት ይወዳደራሉ ተብሎ ተገምቶ ነበር። ነገር ግን ከአራት ዓመታት በኋላ ኃላፊነታቸውን ለቀቁ።

ፓርቲው የነጭ አናሳ አገዛዝ ካበቃ ከ30 ዓመታት በኋላም በዘር ተከፋፍላ የምትኖረውን ደቡብ አፍሪካን አንድ ለማድረግ የማይችል “አካል” ነው ሲሉ ማይማኔ የዲኤ ኃላፊነታቸውን ከለቀቁ በኋላ ተናግረዋል።

በቀጣዩ ወር ስቲንሄዘን በጊዜያዊ መሪነት ተሾሙ። ይህ ለቀንደኛው የዲኤ አባል የማያጠያይቅ ሹመት ሊሆን የሚገባው ነገር ጥያቄዎች ተነስተውበታል።

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የዲኤ አመራር ሙሉ በሙሉ በነጮች ስር ወድቋል ማለት ጀመሩ። ከማይማኔ ጋር ኃላፊነታቸውን የለቀቁ የዲኤ ባለስልጣናት ፓርቲው ወደ ቀኝ ዘመምነት እየተመለሰ መሆኑን አስጠነቀቁ።

ባለፈው ዓመት ዲኤ "በመሠረቱ የነጭ ፓርቲ" መዋቅር ነው ወይ ተብለው የተጠየቁት ስቲንሄዘን "ሰዎች ከዘር በላይ ወደ ብቃት ይመለከታሉ። ነገሮችን መከወንን እና መፈጸምን መቻልን የሚመለከቱት። በሚቀጥለው ምርጫ ጨዋታው ይህ ይሆናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሥራ ቦታ የዘር ኮታዎች መተግበራውን ይቃወማሉ። በደቡብ አፍሪካ ያለውን ዘር ተኮር የኢኮኖሚ ክፍተት ለማጥበብ በኤኤንሲ የቀረበውን ሃሳብም “ያልበሰለ” እና ያልተሳካ በማለት ይቃወማሉ።

የስቲንሄዘን የዘር ጉዳይ በተመለከተ ደቡብ አፍሪካዊ የፖለቲካ ተንታኝ ሪቻርድ ካላላንድ “እሱ ከዕድሉ ተጠቃሚ ሆኖ ነው የኖረው። አብዛኛዎቹ ደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ ያለውን እውነታ የማያውቅ ሰው ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ ከነጭ ህዝብ ይልቅ በድህነት ውስጥ የመኖር ዕድላቸው ከፍተኛ ለሆኑት ጥቁር መራጮች ሃሳባቸው ለመሸጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ደቡብ አፍሪካ እአአ በ 2022 በዓለም እኩልነት የሌለባት አገር ነበረች። ለዚህ አንደኛው ምክንያት ዘር ነው ሲል የዓለም ባንክ አስታውቋል።

ስቲንሄዘን ዲኤ ውስጥ ግልጽ ድጋፍ አላቸው። 80 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ድምጽ በማግኘት ሁለት ጊዜ የፓርቲው መሪ ሆነው ተመርጠዋል።

አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ የስቲንሄዘን ትልቅ ድጋፍ ከሄለን ዚሌ የመጣ ነው። ሄለን የዲኤ የቀድሞ መሪ ሲሆኑ አሁንም በደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ስፍራ አላቸው።

"ዚል ከዙፋኑ በስተጀርባ ያለው ሰው ሆነው ቀጥለዋል። የእርሷ አመለካከት ለዲኤ ብቻ ሳይሆን ለደቡብ አፍሪካ የወደፊት ዲሞክራሲም አስፈላጊ ነው" ሲሉ ካልላንድ ተናግረዋል።

"እኔ እንደማስበው ስቲንሂሰን እሷን በትልቁ ይመለከታል። ለእሱ መሪ መሆንም የእሷ ድጋፍ አስፈላጊ ነበር።”

ከግንቦቱ ምርጫ በፊት በተደረገ የሕዝብ አስተያየት የዲኤ ድጋፍ 21.9 በመቶ ሆኗል። 40.2 በመቶ ድምጽ ያገኘውን ኤኤንሲን ለማሸነፍ በቂ አይደለም። ሆኖም ከ1994 የነጮች የበላይንት ማብቃት በኋላ ቢያንስ 50 በመቶ ድምጽ ላሸነፈው ኤኤንሲ ይህ ከፍተኛ መንሸራተት ነው።

ስልጣን ለመያዝ የሚያስፈልገው ከግማሽ በላይ የሆነ ድምጽ ለማግኘት ስቲንሄዘን ከትናንሽ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት ፈጥረዋል።

አብላጫ ድምጽ ማግኘት ካልቻሉ ከገዥው ፓርቲ ኤኤንሲ ጋር ጭምር ስምምነት በማድረግ ከጥምረት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የፓርቲ ትብብርን ጥቅም ቢገነዘቡም፣ ስቲንሂሰን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ቡጢ ለመወራወርም ወደኋላ አይሉም።

ምዕራብ ኬፕ የፓርቲያቸው የበላይነት የተረጋጋጠበት አካባቢ ነው። በአካባቢው የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ትናንሽ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ ለማግኘት መፈለጋቸውን "ትልቁ የባንክ ዝርፊያ” ሲሉ መክሰሳቸውን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በኤኤንሲ እና በአክራሪው ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ መካከል ሊፈጠር የሚችለው ጥምረት ወደ “የምጽአት ቀን” የሚያመራ ሲሉ አንዳንድ ደቡብ አፍሪካውያንን ላስቆጣውን እና የሚቃጠል የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማን በመጠቀም ያደረጉትን የምርጫ ቅስቀሳ በተመለከተ ተሟግተዋል።

ካላንድ የስቲንሄዘን ሃሳብ “ብዙውን ጊዜ በጣም ጨከን ያለ” ነው ሲሉ ይገልጹታል። የመናገራቸውን ያህልም የዲኤ መሪው በፓርቲያቸው ላይ ለሚሰነዘሩ ትችቶች ስሜታዊ ሊሆኑ ይችላሉ ብሏል።

“ፓርቲውን አጥብቆ ይከላከላል። በዚህ ረገድ በጣም ስሜታዊ ነው… አንድ ነገር ከጻፉ እሱ ካልወደደው ፊት ለፊት ይጋፈጣል” ሲሉ ሃርፐርም በሃሳቡ ተስማምተዋል።

እንዲህ ያለው “ጉዳይ” በጋዜጣዊ መግለጫዎች ወይም ከተንታኞች ወይም ከጋዜጠኞች ጋር በተደረጉ የስልክ ልውውጦች ወቅትም ተደርገዋል ሲሉ ሃርፐር ይናገራሉ።

“በማህበራዊ አካባቢ” ግን ስቲንሂሰን “ዘና ሊያደርግ ይችላል” ብለዋል።

እአአ በ 2022 በታዋቂው የኮሜዲ ትርኢት ፖድካስት ኤንድ ቺል ዊዝ ማክጂ ላይ መቅረባቸው ያንን አሳይቷል።

ስቲንሄዘን ከወጣቶቹ ጋር ጂን እየጠጡ እና በሳቅ የሚያፈርሱ ቀልዶች እየተናገሩ ታይተዋል።

የፖድካስቱ አድናቂዎች በስቲንሂሰን በመገረም “አስቂኝ”፣ "አሪፍ" እና "በጣም ብልህ" ሲሉ እያሞካሹ በዩቲዩብ ላይ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

ግርማ ሞገስ አላቸው፤ ፖለቲካዊ ብቃታቸው ካለማጠያየቁም በላይ ለደቡብ አፍሪካ ሁለት ሚሊዮን አዳዲስ ሥራዎች “ለመፍጠር” ቃል ገብተዋል።

ተቺዎች ግን በጣም አስፈላጊ ወደሆነው የዘር ጉዳይ ሲመጣ እና እንደ አምባገነን የፓርቲ መሪ የመታየት ጥቁር ነጥብ አለባቸው ይላሉ። ለዚህ ምርጫ ቁልፍ የሆኑትን ወጣት ጥቁር መራጮችን ቀልብ ለመሳብ የሚያስችል ነገር አላቸው?

እሳቸው አለኝ ይላሉ። ደቡብ አፍሪካ ለነጭ ፕሬዝዳንት ዝግጁ ነች ብለው ያምኑ እንደሆነ በሜይል እና ጋርዲያን የተጠየቁት ስቲንሂሰን “አሜሪካ ለባራክ ኦባማ ዝግጁ ነበረች? እንግሊዝስ ለሪሺ ሱናክ ዝግጁ ነበረች? ሁለቱም በአገራቸው ካሉ አናሳ ቡድኖች የመጡ ቢሆኑም ሁለቱም የሚያስደንቅ ሥራ ያከናወኑ ይመስለኛል” ብለዋል።