ማኔ፣ ኬሲ. . . የአምስቱ ቀዳሚ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ዝውውር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ወደ ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ የሚጠጋ ገንዘብ አውጥተዋል። እንደዚህም ሆኖ ሊጉ ከኮከቦቹ አንዱ የሆነውን ሳዲዮ ማኔን አጥቷል።
የዝውውር እንቅስቃሴው ከኮቪድ በፊት ወደ ነበረበት ተመልሷል። ስም ካላቸው ዝውውሮች በተጨማሪ ብዙ ክለቦች የክፍያ ክብረ ወሰናቸውን ሰባብረዋል።
በዝውውር መስኮተቱ የመጨረሻ ቀን ፒየር-ኤሜሪክ ኦባሚያንግ ወደ ለንደን መመለሱን አረጋግጧል። በባርሴሎና ከነበረው የስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ቼልሲን ተቀላቅሏል።
የዝውውር መስኮቱ ተጠናቋል። ተጫዋቾች ለአዳዲስ ቡድኖቻቸው መፋለም ጀምረዋል። ዛሬ አምስቱን የአፍሪካ ትልልቅ ተጨዋቾችን ዝውውር እንመልከት።
ሳዲዮ ማኔ - ባየር ሙኒክ (35 ሚሊዮን ፓውንድ)
የማኔ ከሊቨርፑል ወደ ባየር መዛወሩ በሴኔጋላዊው የፊት መስመር ተጫዋች ላይ ጫና ፈጥሮ ነበር። አሁን ለለባሎንዶር ዕጩ ለሆነው ተጫዋች ነገሮች ፈር እየያዙ ይመስላል።
ጀርመናዊው ጋዜጠኛ ራፋኤል ሆኒግስቴይን ለቢቢሲ እንደተናገረው ባየርን “ጥሩ ዝውውር ለማከናወን ከፍተኛ ጫና ገጥሞት ነበር።” የ30 ዓመቱ ተጫዋች ወደ ቡንደስ ሊጋው ማቅናቱ ደረጃውን ዝቅ አያደርገውም ይላል።
በየካቲት ወር የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳው ማኔ በመጀመሪያዎቹ ሰባት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን በማስቆጠር ምላሽ ሰጧል። በመጀመሪያዎቹ 4 የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች ተጨማሪ ጎሎችን ቢያስቆጥርም ተሰርዘውበታል።
ሮበርት ሌዋንዶውስኪን እንዲተካ ስለሚጠበቅ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይቆያል። ፖላንዳዊው በ374 የባየር ሙኒክ ጨዋታዎች 344 ጎሎችን አስመዝግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካሊዱ ኩሊባሊ - ቼልሲ (33 ሚሊዮን ፓውንድ)
የሴኔጋል አምበል ካሊዱ ኩሊባሊ ከብዙዎቹ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ ቆይቷል። በማንቸስተር ዩናይትድ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው ተከላካዩ በመጨረሻም ማረፊያው ቼልሲ ሆኗል። በለንደኑ ክለብ የአራት ዓመት ውል ፈርሟል።
ቼልሲ ከቶተንሃም ጋር 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያይ የ31 ዓመቱ ተጫዋች በሜዳቸው ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ጎል አስቆጥሯል። ከናፖሊ የመጣው ተጫዋች በሊድስ 3 ለ 0 ሲሸነፉ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
አንጋፋው ቲያጎ ሲልቫ፣ አዲስ ፈራሚዎቹ ዌስሊ ፎፋና እና ማርክ ኩኩሬላ ጋር እንዴት ተጣጥሞ ውጤታማ እንደሚሆን በጉጉት ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካልቪን ባሲ - አያክስ (19.6 ሚሊዮን ፓውንድ)
ከሁለት ዓመት በፊት ባሲ በሌስተር ሲቲ ተጠባባቂ ቡድን ውስጥ ነበር። አሁን አያክስን ከተቀላቀለ በኋላ በቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታው ለማከናወን እየተዘጋጀ ነው።
የ22 ዓመቱ ናይጄሪያዊ ያለፈው የውድድር ዓመት የዩሮፓ ሊግ ጉዞ ድንቅ ነበር። ከሬንጀርስ ጋር አስከ ፍጻሜው መጓዝ ችሏል። ዋንጫውን በኢንትራክት ፍራንክፈረት መነጠቃቸው ይታወሳል።
ተከላካዩ የኔዘርላንድን ሕይወቱን በአሳዛኝ መልኩ ጀምሯል። በሱፐር ካፕ በፒኤስቪ አይንድሆቨን 5 ለ 2 ተሸንፈው ዋንጫውን አጥተዋል። ቡድኑ ከዚያን በኋላ ያደረጋቸውን ሦስት የኤርዲቪዜ ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፏል።
ያለፈው የውድድር ዘመን ባሲ ምን ማድረግ እንደሚችል ያሳየ ነው። አያክስ ትልልቅ ክለቦች የሚመኟቸውን ተጫዋቾች ለማብቃት እና ለማሻሻል ጥሩ ቦታ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፍራንክ ኬሴ - ባርሴሎና (በነጻ ዝውውር)
ኬሴ ከኤሲ ሚላን ወደ ባርሴሎና በነጻ ነው የተዘዋወረው። ይህም በአይቮሪ ኮስታዊው ተጫዋች በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ፈተና ፈጥሮበታል። ምክንያት ከተባለ ደግሞ የስፔኑ ኃያላን ቡድኖች የገንዘብ ችግር ነው።
የ25 ዓመቱን ተጫዋች ቡድኑ ማስፈረሙን ለማረጋገጥ የውድድር ዘመኑ ማስጀመሪያ ዋዜማን መጠበቅ ከነበረባቸው የባርሳ ፈራሚዎች አንዱ ነበር።
የመጫወት ፈቃድ ያገኘበትን ወረቀት ያገኘው ከራዮ ቫልካኖ ጨዋታ ትንሽ ቀደም ብሎ ነው። በተቀያሪ ወንበር ላይ የጀመረው አማካዩ ከጋቪ፣ ፔድሪ ወይም ሰርጂዮ ቡስኬትስ አንዱን ለማስቀመጥ ይፎካከራል። ባለፉት አራት ጨዋታዎችም ተቀያሪ ወንበር ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።
የመሐል አማካዩ የጨዋታ ዘመኑን በአታላንታ ጀመረ። እአአ በ2019 ሳን ሲሮ ያቆየውን ቋሚ ዝውውር ከማጠናቀቁ በፊት በሚላን ሁለት የውሰት ዓመታትን አሳልፏል። ከሮሶነሪዎች ጋር ባለፈው የውድድር ዓመት የሴሪአውን ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሎታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፒየር-ኤምሪክ ኦባሚያንግ - ቼልሲ (10.3 ሚሊየን ፓውንድ)
የቼልሲ በዝውውር መስኮቱ የመጨረሻ ቀን ፊቱን ወደ ፒየር-ኤምሪክ ኦባሚያንግ ማዞሩ ለሁሉም አካላት ጥሩ ይመስላል። ግን ጋቦናዊው አጥቂ በቦርሺያ ዶርትሙንድ ለቶማስ ቱሄል የተሳካለትን ያህል ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል?
ቱሄል የዶርትሙንድ አሰልጣኝ እያሉ ነበር የፊት አጥቂውን ወደ መሐል አጥቂነት የቀየሩት። ውጤቱ እአአ በ2018 ኦባሚያንግ በ56 ሚሊየን ፓውንድ ወደ መድፈኞቹ እንዲዛወር እገዛ አድርጓል።
የ33 ዓመቱ ተጫዋች በነበረው አለመግባባት በጥር ወር ከሰሜን ለንደኑ ቡድን ለቅቆ ወደ ካታላኑ ክለብ አመራ። ለባርሴሎና በ24 ጨዋታዎች 13 ጎሎችን አስቆጠረ። በኋላም በ10.3 ሚሊየን ፓውንድ ወደ ቼልሲ ተዛወረ።
የኦባሚያንግ የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ስላለው የተከፈለው ዋጋ ጥሩ ነው። ዋናው ጥያቄ ግን ሮሜሉ ሉካኩ እና ቲሞ ወርነር የወደቁበትን ስፍራ እሱ ይሳካት ይሆን የሚለው ነው።












