ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሸገር ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ሁለት ጋዜጠኞች ታሰሩ
ሦስት የታዋቂው ሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ ጋዜጠኞች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው አንደኛው ሲለቀቅ ሁለቱ ለቀናት በእስር ላይ እንደሚገኙ ባልደረቦቻቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሦስቱ ጋዜጠኞች በፖሊስ የተያዙት ረቡዕ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም. ሲሆን አንጋፋው ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ በዕለቱ ሲለቀቅ አርታኢዋ ትዕግሥት ዘሪሁን እና ሪፖርተር ምንታምር ፀጋው አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።
ረቡዕ ከሰዓት 10፡30 ገደማ የፌደራል ፖሊሶች እና ሲቪል የለበሱ የደኅንነት አባላት ድል በር የሚገኘውን የሸገር ኤፍ ኤም ጣቢያን በር "በጉልበት ጥሰው በመግባት" በሥራ ገበታቸው ላይ የነበሩ ሁለት ጋዜጠኞችን እንዲሁም ሌላኛዋን ጋዜጠኛ ደግሞ ከመኖሪያ ቤቷ እንደወሰዱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጣቢያው ባልደረቦች ተናግረዋል።
በጣቢያው ዋና አዘጋጅ የሆነው እሸቴ አሰፋ፣ አርታኢ ትዕግስት ዘሪሁን እና ሪፖርተር ምንታምር ፀጋው ሜክሲኮ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የተወሰዱ ሲሆን፣ ዋና አዘጋጁ ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ የዚያኑ ዕለት አመሻሹን መለቀቃቸው ተገልጿል።
ነገር ግን ሁለቱ ጋዜጠኞች አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ባልደረቦቻቸው ተናግረዋል።
ጋዜጠኞቹ በምን ተጠርጥረው እንደታሰሩ አልተገለጸም።
ቢቢሲ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ጀይላን አብዲን ቢጠይቅም መረጃ እንደሌላቸው እና እንደሚያጣሩ ተናግረዋል።
ባልደረቦቻቸው እንደገለጹት ጋዜጠኞቹ ከመታሰራቸው በፊት ባለፈው ሳምንት ዓርብ ነሐሴ 23/ 2017 ዓ.ም. በጣቢያው የተላለፈን አንድ ዘገባ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለጣቢያው ደብዳቤ ጽፎ ነበር።
ዘገባው ለወራት የዘለቀውን የጤና ባለሙያዎች የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር የሰጠውን አስተያየት ያካተተ ነበር።
በቅርቡ ሚኒስቴሩ የጤና ባለሙያዎች የሚታከሙባቸው "የሠራተኛ ክሊኒኮች እንዲቋቋሙ" እና "የጤና ተቋማት ለሠራተኞች ተሽከርካሪዎቻቸውን እንዲያቀርቡ" ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።
ሸገርም በዘገባው የጤና ባለሙያዎች ማኅበርን አስተያየት መጠየቁን የተናገሩት የጣቢያው ባልደረቦች፣ የማኅበሩ አመራሮች የተሰጣቸው ምላሽ "የይስሙላ" እንደሆነና ጥያቄያቸው በተገቢው መንገድ ካልተመለሰ ከመስከረም 5/2018 ዓ.ም. ጀምሮ አድማ ሊመቱ እንደሚችሉ የገለጹበት ሃሳብ መካተቱን ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም ይህ ዘገባ "አመፅን የሚያነሳሳ እና አድሏዊ የሆነ ነው" በማለት ከጣቢያው ማኅበራዊ ገጾች እንዲነሳ በደብዳቤው ማዘዙን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባልደረቦች ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ቅዳሜ ነሐሴ 24/ 2017 ዓ.ም. በጣቢያው የዩቲዩብ፣ የፌስቡክ እና የቴሌግራም ገጾች ተጋርቶ የነበረው ይህ ዘገባ መነሳቱን ገልጸዋል።
ከዚያ ግን ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ነሐሴ 28/2017 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ወደ ጣቢያው በማምራት በሥራ ገበታቸው ላይ የነበሩ ሁለት ጋዜጠኞችን እንዲሁም በመኖሪያ ቤቷ የነበረችን አንዲት ጋዜጠኛ ወስደው ማሰራቸውን ገልጸዋል።
በወቅቱ በሥራ ላይ እንደነበሩ የገለጹ አንድ የጣቢያው ባልደረባ "ፖሊሶቹ የግቢውን በር እና የዋና አዘጋጁን ቢሮ በኃይል በርግደው በመግባት በቁጣ እና በማመናጨቅ ነው የወሰዷቸው" ብለዋል።
የፈረቃው አርታኢ የነበረችው ትዕግስት ዘሪሁን ከቢሮ ውጪ ስለነበረች ቤቷ ድረስ በመሄድ ከመኖሪያ ቤቷ እንደተወሰደች እኚሁ የጣቢያው ባልደረባ አክለዋል።
ሐሙስ ሁለቱ ጋዜጠኞች ታስረው በሚገኙበት የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ ሄደው እንዳነጋገሯቸው የተናገሩት ባልደረቦቻቸው፣ ጋዜጠኞቹ የደረሰባቸው ጉዳት ባይኖርም ጋዜጠኛ ምንታምር "የምታጠባውን ሕጻን ልጇን ጥላ በወጣችበት መታሰሯ አስጨንቋታል።" ብለዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ የሆነው ሸገር፣ ስለ ጋዜጠኞቹ እስር እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጋዜጠኞች እስር እየተበራከተ የመጣ ሲሆን በቅርቡ ሁለት ጋዜጠኞች በተለያዩ አካላት ተወስደው ያሉበት ሳይታወቅ ከቆዩ ከአስር ቀናት በኋላ መለቀቃቸው ይታወሳል።
የሪፖርተር ጋዜጣ ባልደረባ ዮናስ አማረ እና አንጋፋው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሐመድ በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር ስለመሆናቸውም ሆነ ፍርድ ቤትም እንዲቀርቡ ስለመደረጉ ምንም መረጃ ሳይገኝ ነበር መለቀቃቸው የተሰማው።
አንጋፋው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሐመድ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ታይቶ የነበረ ቢሆንም የት እንደታሰረ ሳይታወቅ እና ጠበቃም ሆነ ቤተሰብ ሳያገኝ ለቀናት እንደቆየ ተገልጿል።
የጋዜጠኞቹን መሰወር ተከትሎ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሲፒጄ ባወጣው መግለጫ፣ የጋዜጠኞች እስር እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር።
የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ "የፕሬስ ነፃነት ላይ አሉታዊ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ፤ በፍጥነት ለጋዜጠኞች ምቹ ያልሆነች ከባቢ እየሆነች ነው" ብለዋል በመግለጫው።
በጋዜጠኞች አያያዝ እና በፕሬስ ነጻነት ከጥቂት ዓመታት በፊት ከፍተኛ መሻሻልን አስመዝግባ የነበረችው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ደረጃዋ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ነው።
በዘንድሮው በዓለም የፕሬስ ነጻነት መመዘኛ ደረጃም ባለፈው ዓመት ከነበረችበት በአራት ደረጃ ዝቅ ብላ 145ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
በፕሬስ ነጻነት ደረጃ 180 አገራት የተካተቱ ሲሆን ኢትዮጵያ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ከነበረችበት የ141ኛ ደረጃ በዚህ ዓመት በአራት ደረጃዎች መውረዷን ሪፖርቱ አስታውቋል።