ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሲፒጄ በኢትዮጵያ የታሰሩ እና ያሉበት ያልታወቁ ጋዜጠኞች ጉዳይ በእጅጉ አሳስቦኛል አለ
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሲፒጄ ጭምብል ባጠለቁ የፀጥታ ሰዎች የተወሰዱ እና በቁጥጥር ስር የዋሉ ጋዜጠኞች ጉዳይ በእጅጉ እንዳሳሰበው ተናገረ።
ድርጅቱ ትናንት ረቡዕ ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ባልታወቁ ሰዎች የተወሰደው የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነው ዮናስ አማረ ፣ በዘፈቀደ የታሰረው ጋዜጠኛ ከድር ሞሐመድ እስማኤል እና በድብቅ የታሰረው አንጋፋው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ ሞሐመድ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል።
ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም. ጭምብል ያጠለቁ እና ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰዋል የተባሉ ሰዎች ዮናስ አማረ ከሚኖርበት ሸገር ከተማ ጠልፈው መውሰዷቸውን ሲፒጄ የተለያዩ ምንጮችን ጠቅሶ ገልጿል።
የዓይን እማኞች እንደተናገሩት የደንብ ልብስ የለበሱት የፀጥታ ሰዎች በመጀመሪያ በአካባቢው ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመንጠቅ፤ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ እንዲሆኑ ትዕዛዝ እንዳስተላለፉ ጋዜጠኛው የሚሰራበት ሪፖርተር ጋዜጣ ጉዳዩን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
አዲስ አበባ ፖሊስ ጋዜጠኛው በቁጥጥሩ ስር እንዳልሆነ ለሪፖርተር የገለፀ ሲሆን፤ ዮናስ አማረ የት እንዳለ እስካሁን አይታወቅም።
የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ "የፕሬስ ነፃነት ላይ አሉታዊ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ፤ በፍጥነት ለጋዜጠኞች ምቹ ያልሆነች ከባቢ እየሆነች ነው" ብለዋል።
"ባለሥልጣናት የዮናስ አማረን ጠለፋ በአስቸኳይ መመርመር አለባቸው፤ ተጠያቂዎችንም ተጠያቂ ማድረግ አለባቸው። ጋዜጠኛ ከድር ሞሐመድ እስማኤል እና አብዱልሰመድ ሞሐመድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለመንግሥታዊው የሶማሌ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚሰራው ጋዜጠኛ ከድር ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም. በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።
ጋዜጠኛው እስካሁን ይፋዊ ክስ ሳይመሰረትበት በእስር ቤት እንደሚገኝ ቤተሰቦቹ እና የድረ ገፅ መገናኛ ብዙኃን የሆነው 'ቮስ ቲቪ' ገልፀዋል።
ጋዜጠኛው ነሐሴ 3/2017 ዓ.ም. ያለ ጠበቃ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ከእስሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከሶማሌ ክልላዊ ቴሌቭዥን የፌስቡክ ገፅ ላይ ስለተነሳው የክልሉን መንግሥት ስለሚተች ልጥፍ መጠየቁን አንድ የቤተሰቡ አባል ተናግረዋል።
በአሐዱ ሬዲዮ 'ቅዳሜ ገበያ' የተባለ የንግድና ምጣኔ ሀብት ፕሮግራም አቅራቢ እና 'ሳሎን ቲዩብ' በተባለ የዩቲዩብ ገፅ የሚሰራው ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ ሞሐመድ ነሐሴ 5/2017 ዓ.ም. ከሚኖርበት አዲስ አበባ ከተማ መጥፋቱ ተነግሯል።
ጋዜጠኛው የገባበት የጠፋው የመንጃ ፈቃድ ፈተና ወስዶ ከተመለሰ በኋላ መሆኑን ፥ምንጮች ተናግረዋል።
ከቀናት በኋላ ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም. አብዱልሰመድ 22 ማዞሪያ አካባቢ በሚገኘው ቢሮው በፖሊሶች ታጅቦ ሲፈተሽ እንደታየ ቤተሰቦቹ እና ኩባንያው አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ ጋዜጠኛው እስካሁን ድረስ ያለበት አይታወቅም።
ሲፒጄ ለፌደራል ፖሊስ እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ለሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ለመጠየቅ መልዕክት እንደላከ እና ምላሽ እንዳላገኘም ገልጿል።