የምንጠቀማቸው 'የሜክአፕ' ዕቃዎች ምን ያህል አደገኛ እና የተበከሉ ናቸው?

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የምንጠቀመው 'ሜክአፕ' የመገልገያ ጊዜው መች እንደሚያበቃ አጣርተን እናውቃለን? ጊዜያቸው ያለፈባቸው ሜክአፖች ምን ያክል አደገኛ እንደሆኑስ የምናውቀው ነገር አለ?

ሜክአፕ የሚጠቀሙባቸውን ብሩሾች ያፀዳሉ??

ከጓደኛዎ ማስካራ ተበድረው አሊያም ሱቅ ገብተው 'ሊፕስቲክ' ሞክረው ያውቃሉ?

ቦርሳዎ ውስጥ ያለው ሜክአፕ ምን ያህል ባክቴሪያ እንደሚስብስ አስበውታል?

የቢቢሲዋ ናዛኒን ሞታሜዲ የሜክአፕ ዕቃዎቿን ይዛ ወደ ለንደን ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቤተ-ሙከራ አቀናች።

ዶ/ር ማሪያ ፒላር በዩኒቨርሲቲው የሂዩማን ሳይንስ ክፍል የባዮሳይንስ ነባር መምሕር ናቸው።

ጥናቱን እንዲመሩ ተመርጠዋል።

70 የሚሆኑ ቀን ያለፈባቸው 'አይላይነር፣ ሊፕስቲክ፣ ፋውንዴሽን፣ ማስካራ እና ሊፕ ግሎስ' የተባሉ የሜካአፕ ዕቃዎችና ብሩሾችን መርጠው አስቀምጠዋል።

ከእያንዳንዱ ዕቃ የተወሰደ ቅንጣት ምርመራ ይደረግበታል።

የሜካአፕ ዕቃችን ምን ያክል የተመረዘ ነው?

የናዛኒን የሜክአፕ ዕቃዎች ላይ የተገኙት ባክቴሪያዎች እጅግ በርካታ ናቸው።

"በተለይ አይ ፔንሲል [የአይን ኩል] የተባለው የሜክአፕ ዕቃሽ እጅግ የተበከለ ሲሆን ከሌሎቹ ሲነፃፀር ብዙ ባክቴሪያዎች ተገኝተውበታል" ሲሉ ዶ/ር ማሪያ ነገሯት።

ይህ የሆነበት ምክንያት ይህ እርሳስ መሰል የሜክአፕ ዕቃ ከቆዳ ጋር ስለሚገናኝ ብዙ ባክቴሪያ ያገኛል።

በርካቶች የሜካአፕ ዕቃዎቻቸውን መታጠቢያ ቤት ያስቀምጣሉ። አይ ላይነር የተባለው የሜክአፕ ዕቃ ካልተከደነ ባክቴሪያ ሊስብ ይችላል።

"የሜካፕ ዕቃዎቻችን እርጥበት ያለበት የምናስቀምጥ ከሆነ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ከብሩሾች፣ ስፖንጆች እና ማስካራዎች ስታፊሎኮከስ አግኝተናል" ሲሉ ያብራራሉ ዶክተሯ።

ስታፊሎኮከስ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስ የጤና እክል ሊያመጣ የሚችል ነው።

ናዛኒን ትጠይቃለች። ታድያ ይህን ሁሉ ዓመት የተበከሉ የሜክአፕ ዕቃዎችን ስጠቀም እንዴት በሽታ ሊይዘኝ አልቻለም?

ዶ/ር ማሪያ እንደሚሉት "ቆዳችን ድፍን ከሆነ ምን ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ቆዳችን ከተከፈተ አሊያም ቁስል ካለብን እኒህ የተበከሉ የሜክአፕ ዕቃዎች ላይ የሚገኙ ባክቴሪያዎች ወደ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። የተዳከመ በሽታ የመከላከል አቅም ያላቸው ሰዎች በዚህ ምክንያት አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ።"

እጅ መታጠብ

ሜክአፕ ከመጠቀምዎ በፊት እጅዎን ይታጠባሉ? እጃችን በርካታ ጀርም ይይዛል። እኒህ ጀርሞች ወደ መዋቢያ ዕቃዎች ሊዘዋወሩ ይችላሉ። በተለይ ደግሞ አይሻዶው፣ የከንፈር ቅባቶች እና ፋውንዴሽን ጀርም ሊስቡ ይችላሉ።

ዶ/ር ማሪያ "በአንዳንድ የሜክአፕ ዕቃዎች ላይ ኤንቴሮባክተር የተባለ ባክቴሪያ የተገኘ ሲሆን ይህ ባክቴሪያ ለወትሮው አንጀት ውስጥ የሚገኝ ነው" ሲሉ ያብራራሉ።

"ይህ ሊሆን የሚችለው እጃችንን ባለመታጠባች አሊያም ከሽንት ቤት በሚመነጩ ባክቴሪያዎች አማካይነት ነው።"

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሽንት ቤት ውሀ ስንለቅ የሚፈናጠቁ ጠብታዎች እስከ 2 ሜትር ወደላይ ሊፈናጠሩ ይችላሉ። እኒህ ጠብታዎች ኤንትሮባክተር የያዙ ናቸው። የሜክአፕ ዕቃዎች ላይ ካረፉ ባክቴሪያ ሊያስተላልፉ ይችላሉ ማለት ነው።

አንዳንድ ኤንትሮባክተሮች በሽታ አዝለው ሊሆን ይችላል። እኒህ ባክቴሪያዎች የተለያዩ በሽታዎችን የማስተላለፍ አቅም አላቸው።

ከዚህ በፊት የተሠሩ ጥናቶች እንደጠቆሙት ኢ ኮላይ የተባለው ባክቴሪያ የሜክአፕ ዕቃዎች ላይ ሊጣበቅ ይችላል። የሜክአፕ ዕቃዎች ደግሞ ፊታችን ላይ እንዲሁም ዓይናችን አካባቢ ስለምንጠቀማቸው በሽታ የመተላለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።

ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የተሰራው ጥናት ሌላ ያገኘው ነገር ፈንገስ ነው። ይህ ፈንገስ ቆዳን አልፎ መግባት ከቻለ የሴቶች ብልት ላይ እንዲሁም አፍ አካባቢ አደጋ ሊያመጣ ይችላል።

ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው አስተን በርሚንግሀም ዩኒቨርሲቲ 500 የመዋዋቢያ ዕቃዎች ላይ ምርምር አድርጓል። ጥናቱ እንደሚያሳየው ለ79 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ የኮስመቲክ ዕቃዎች ፓራሳይት፣ ባክቴሪያ አሊያም ፈንገስ አለባቸው። አደጋቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ባክቴሪያዎች ጀምሮ ገዳይ ነው እስከሚባለው ኢ ኮላይ ድረስ ተገኝተዋል።

የመጠቀሚያ ቀን መመልከት

የሜክአፕ ዕቃዎች ላይ የሚለጠፉ የመጠቀሚያ አሊያም የመገልገያ ጊዜ ቀናት ዕቃዎቹ ምን እስከመቼ ባክቴሪያ እና ሌሎችን መከላከል እንደሚችሉ የሚጠቁም ነው።

ፈሳሽ ነገር ያላቸው ምርቶች ለባክቴሪያ እና ፈንገስ የተመቹ በመሆናቸው በጥንቃቄ ሊያዙ ይገባል።

እንደ መዋቢያ ዕቃዎች ዓይነት የመጠቀሚያ ቀናቸው ከ3 እስከ 12 ወራት ሊቆይ ይችላል።

የለንደን ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያሳየው ማስካራ እና ፈሳሽ ፋውንዴሽን ባክቴሪያ የማስተላለፍ አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ብሩሽ እና ስፖንጆች ደግሞ አምቀው ሊይዙ ይችላሉ።

ዶ/ር ማሪያ ሱቆች ገብተን የመዋቢያ ዕቃዎች እንዳንሞክር ይመክራሉ። ምክንያት ከኛ በፊት የመጡ ሰዎች እጃቸው ንፁህ ስለመሆኑ የምናውቀው ነገር የለም።

አክለው በየጊዜው የሜክአፕ ዕቃዎቻችንን ከትኩስ ውሀ እና በሳሙና አፅድተን በጥንቃቄ እንድናደርቅ ያሳስባሉ። ይህ ለማድረግ ግዴታ ውድ የሆኑ መሣሪያዎች መጠቀም የለብንም ይላሉ።

ባለሙያዋ እንደሚሉት የሜክአፕ ዕቃዎችን መፀዳጃ ቤት ማስቀመጥ አደጋ አለው። ጨምረው የሜክአፕ ዕቃዎቻችን ከድነን ማስቀመጥ እንዳለብን ይናገራሉ።

የመጨረሻው ምክራቸው የሜክአፕ ዕቃዎቻችን ለሰዎች እንዳናውስ እና የሰዎችን እንዳንጠቀም ነው።