ቻይና ታይዋንን ‘ለመቅጣት’ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመረች

የቻይና ባሕር ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቻይና በታይዋን አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመረች።

ዊልያም ላይ የታይዋን አዲስ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተሾሙ ከሦስት ቀን በኋላ ታይዋንን “ለመቅጣት” በሚል ወታደራዊ ልምምዱ መጀመሩ ተገልጿል።

የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ ወታደራዊ ክንፍ ቃል አቀባይ የሆኑት ሊ ዢ “ለተገንጣይ ኃይሎች ከባድ ቅጣት ነው” ሲሉ ልምምዱን ገልጸውታል።

ወታደራዊ ልምምዱ የተጀመረው ዛሬ ሲሆን በታይዋን አቅራቢያና ምዕራባዊ ክፍል እንዲሁም በታይዋን ቁጥጥር ሥር በሚገኙት ኪንማን፣ ማትሱ፣ ውኩይ እና ዶንጊን ደሴቶችም ነው እየተካሄደ ያለው።

የታይዋን መከላከለያ ባወጣው መግለጫ የቻይናን ድርጊት “ምክንያት አልባ ትንኮሳ” ሲል ገልጾታል።

ታይዋን በምላሹ የባሕር፣ የአየርና የምድር ጦሯን “የደሴቷን ሉዓላዊነት እንዲከላከሉ” ማሰማራቷን ገልጻለች።

የቻይና ጦር እንዳለው ወታደራዊ ልምምዱ ያተኮረው በደሴቱ ውስጥና አካባቢ የባሕርና አየር ተዋጊዎችን ዝግጁ ማድረግና ዒላማ ማስተካከል ላይ ነው።

የቻይና ወታደሮችን “ጥምር የጦር ዝግጁነት” ማረጋገጥ ግቡ እንደሆነም አክሏል።

ተዋጊ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

“ልምምዱ የታይዋን ተገንጣይ ኃይሎች ላይ ያነጣጠረ ጠንካራ ቅጣት ነው። የውጭ ኃይሎች ጣልቃ እንዳይገቡና እንዳይተናኮሱ ጥብቅ ማስጠንቀቂያም ነው” ሲል የቻይና ጦር አሳስቧል።

ራሷን የምታስተዳድረው ታይዋን የግዛቷ አካል እንደሆነች ቻይና ለረዥም ጊዜ ስትገልጽ ቆይታለች። ደሴቷ ግን ይህንን አትቀበልም።

ስለ ታይዋን ነጻነት ከዚህ ቀደም የተናገሩትን አዲስ የተመረጡት የታይዋን ፕሬዝዳንት ቻይና “ገንጣይና ነውጥ አነሳሽ” ስትል ጠርታለች።

በዓለ ሲመታቸው ሲፈፀም ቻይና ታይዋንን “ማስፈራራት ታቁም” ብለዋል።

ቻይና በምላሹ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዋንግ ሊ በኩል ፕሬዝዳንቱን “ማፈሪያ” ስትል ተችታለች።

የፕሬዝዳንቱ ማሸነፍ ይፋ ከሆነ በኋላ ቻይና ታይዋን “የግዛቴ አላል ናት” ብላ የፕሬዝዳንቱን የእንነጋገር ጥሪ ውድቅ አድርጋለች።

ቻይና ባለፉት ዓመታት ታይዋንን በጦር አውሮፕላንና መርከብ ስትከብ ቆይታለች።

በበዓለ ሲመቱ ቀንም ወታደራዊ ኃይሏን አሰማርታ ነበር።

እስካሁን አካባቢውን ከመክበብ ባለፈ ወረራ አልተካሄደም።

ተንታኞች እንዳሉት ወረራ ሳይፈፀም ከበባ ማድረግ ኃይል ማዳከሚያና ግዜ መግዣ ሲሆን፣ ቻይናም ይህንን አካሄድ ታይዋን ላይ እየተጠቀመች ነው።

ቻይና የጀመረችው ወታደራዊ ልምምድ “በጡንቻ የመመካት አዝማሚያዋን” ያሳያል ስትል ታይዋን ተችታለች።

የታይዋን መከላከያ “በጥቂት ዓመታት ውስጥ የቻይና አየር ኃይልና መርከቦች በተደጋጋሚ ትንኮሳ እያካሄዱ ነው። ዓለም አቀፍ ሰላምና መረጋጋትን ያውካል” ብሏል።

አያይዞም “ወታደራዊ ልምምዱ በታይዋን ሰላምና መረጋጋት ከመንሳቱ ባሻገር የቻይናን የጦር ትምክህት ያሳያል” ሲል አክሏል።