ፊፋ ከፍጻሜው ጨዋታ በኋላ ሳልት ቤይ እንዴት ወደሜዳ እንደገባ እየመረመርኩ ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፊፋ ከኳታር የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ጨዋታ በኋላ ታዋቂው ሼፍ ሳልት ቤይ እና ሌሎች ሰዎች እንዴት ወደ ሜዳ መግባት እንደቻሉ እየመረመርኩ ነው አለ።
በትክክለኛ መጠሪያ ስሙ ኑስሬት ጎክሴ የተባለው ቱርካዊው ምግብ አብሳይ ሳልት ቤይ የአርጀንቲና ተጫዋቾች ፈረንሳይን ካሸነፉ የዓለም ዋንጫን ሲስም እና ደስታውን ሲገልጽ ታይቷል።
በፊፋ ሕግ መሠረት ግን ዋንጫው ሊነኩ የሚችሉት “የተመረጡ" ግለሰቦች ብቻ ነው።
ዋንጫውን መንካት የሚችሉት የውድድሩ አሸናፊዎች፣ የፊፋ ባለስልጣናት እና የአገራት መሪዎች ናቸው።
ሳልት ቤይ ግን ዋንጫውን ይዞ ሲስም እና ከአሸናፊዎቹ የአርጀንቲና ተጫዋቾች ዋንጫውን እየተቀበለ ፎቶ ለመነሳት ሲጥር ታይቷል። ሼፉ ከዋንጫ ስነስርዓት በኋላ የሜሲ ትኩረት ለመሳብ ሲሞክር ተጫዋቹ ችላ ብሎት ሲሄድም ታይቷል።
የፊፋ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ስፖርት በሰጡት መግለጫ “በሉሳይል ስታዲየም ከተካሄደው የመዝጊያ ስነስርዓት በኋላ ግለሰቦች እንዴት ተገቢ ያልሆነ ፈቃድ አግኝተው ሜዳ ላይ እንደተገኙ ፊፋ ለማረጋገጥ እየሠራ ነው።“
“ተገቢው የውስጣው እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል።
ሳልት ቤይ የቅንጦት ስቴክ ሬስቶራንቶች ባለቤት ነው። እአአ በ2017 ስጋውን የሚያዘጋጅበት እና የጨው አጨማመር ዘዴው በማህበራዊ ሚዲያ ዝነኛ አድርጎታል።
ይህ ጽሑፍ በInstagram. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የInstagram ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ Instagram ይዘት መጨረሻ
የፊፋ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ፣ ሜሲ፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ዴቪድ ቤካምን ጨምሮ በርካታ በእግር ኳሱ ዕውቅ የሆኑ ግለሰቦች በሳልት ቤይ ሬስቶራንቶች ተመግበዋል።
የዓለም ዋንጫ እየተከናወነ የፊፋውን ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖን ሲያቅፍ የሚያሳይ ቪዲዮ አውጥቷል።
በኋላም ሳልት ቤይ የክብር አንግዶች በሚቀመጡበት ስፍራ ኢንፋንቲኖን ጨምሮ ከብራዚላዊያኑ ሮናልዶ፣ ሮቤርቶ ካርሎስ እና ካፉ ጋር ፎቶ ተነስቷል።












