ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከቁም እስር ሊያመልጡ ሞክረዋል የተባሉት የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት በቁጥጥር ሥር ዋሉ
በቁም እስር ላይ የነበሩት የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት ጃይር ቦልሶናሮ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ቀኝ ዘመሙ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ያሳለፍነው መስረከም ላይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ በማሴር ጥፋተኛ ተብለዋል።
የ27 ዓመት እስራት ቢፈረድባቸውም ይግባኝ በማለታቸው በቁም እስር ላይ ነበሩ።
የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አሌክሳንድሬ ደ ሞራይስ እንዳሉት፤ ቦልሶናሮ እንዲታሰሩ የተወሰነው "አዲስ መረጃ" መገኘቱን ተከትሎ ነው።
ቦልሶናሮ በቁም እስር ላይ ሳሉ ከተወሰነ ርቀት ውጭ ሲጓዙ ለፖሊስ ጥቆማ የሚሰጥ የእግር ሰንሰለት ተደርጎላቸው ነበር። ይህንን የእግር ሰንሰለት ለማውለቅ ሞክረዋል ቢባልም እሳቸው ግን ሰንሰለቱን ለመክፈት ብቻ ጥረት እንዳደረጉ ገልጸዋል።
ከቁም እስር ሊያመልጡ ይችላሉ የሚል ስጋት ስለተፈጠረ እንዲታሰሩ መወሰኑን ፖሊስ አስታውቋል።
በቤታቸው አቅራቢያ እየተካሄደ የነበረን ተቃውሞ እንደ ሽፋን በመጠቀም ለማምለጥ መሞከራቸው ተገልጿል።
"ቤታቸው አቅራቢያ ተቃውሞ እንዲጀመር ልጃቸው አስተባብሯል። ከዚያም ኤሌክትሮኒክ የእግር ሰንሰለቱን አውልቀው ሊያመልጡ ሞክረዋል" ሲሉ ዳኛው ተናግረዋል።
የሕዝብ እንደራሴ የሆነው ልጃቸው ፍላቮ ቦልሶናሮ የአባቱ ደጋፊዎች ተቃውሞ እንዲያካሂዱ አነሳስቷል።
"ለአገራችሁ አትታገሉም? ሶፋ ላይ ተቀምጣችሁ ስልካችሁ ላይ ትግሉን መመልከት ይሻላችኋል? ኑ አመጹን ተቀላቀሉ" በማለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ጥሪ አቅርቧል።
የቦልሶናሮ ልጅ የአባቱ ደጋፊዎች የተሰባሰቡት "ስለ ጤናው እና ዴሞክራሲ ለመጸለይ" እንደሆነ ተናግሯል።
ዳኛው ግን ተቃውሞው የተቀነባበረው ቦልሶናሮ አምልጠው በውጭ አገራት ኤምባሲዎች ከለላ እንዲጠይቁ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ከቦልሶናሮ ቤት 13 ኪሎሜትር ይርቃል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቦልሶናሮ የተላለፈውን ብይን በመቃወም ብራዚል ላይ 50% ታሪፍ ለመጣል ወስነዋል።
በመዲናዋ ብራዚሊያ የታሰሩት ቦልሶናሮ ዛሬ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። የተፈረደባቸውን 27 ዓመታት በቁም እስር እንዲያሳልፉ ጠበቆቻቸው ከዚህ ቀደም ጠይቀዋል።
ቦልሶናሮ እአአ በ2022 ምርጫ ሲሸነፉ ከሥልጣን ላለመውረድ ሲሉ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክረዋል በሚል ነበር የተከሰሲት።
ቦልሶናሮን ያሸነፉት ግራ ዘመሙ ሉዊዝ ኢንሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ናቸው።
የቦልሶናሮ የመፈንቅለ መንግሥት ውጥን ሉላን እንዲሁም ምክትላቸው ጄራልዶ አልክሚንን መግደልን ያካተተ እንደነበር የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ተናግረዋል።
ዕቅዱ በብራዚል ወታደሮች እና በአየር ኃይሉ ድጋፍ ስላላገኘ ሳይሳካ ቀርቷል። የሉላን በዓለ ሲመት ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የቦልሶናሮ ደጋፊዎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጥሰው ገብተዋል። ነውጥ አስነስተዋል በሚል 1,500 የሚሆኑት ታስረዋል።
ቦልሰናሮ ተቃውሞን ያነሳሱት ወታደራዊ ኃይሉ ወደ ሥልጣን እንዲመልሳቸው ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።
ቦልሶናሮ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለው የ27 ዓመታት እስራት ሲፈርባቸው ጠበቆቻቸው "በጣም የተጋነነ ነው" ብለው ተከራክረዋል።
ከእስር ሲፈቱ ማለትም እአአ በ2060 በሚኖረው ምርጫ እንዳይሳተፉም በፍርድ ቤት ታግደዋል።